የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት —ታላቅ የሥራ በር
1 ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት “[ሕዝቦቼን] የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፤ ከእንግዲህም አይፈሩም፤ አይደነግጡም ከእነርሱም አንድ እንኳ አይጐድልም” የሚል ትንቢት አስነግሮ ነበር። (ኤር. 23:4) በዛሬው ጊዜ እንደዚህ ያለው የእረኝነት ሥራ በአሥር ሺዎች በሚቆጠሩ የጉባኤ ሽማግሌዎች አማካኝነት በዓለም ዙሪያ እየተከናወነ ነው። ከእነዚህም በተጨማሪ ብዛታቸው እንደ ንጋት ጠል የሆኑ ወጣቶች ለይሖዋ አገልግሎት ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። (መዝ. 110:3) እነዚህ ትሑት ወንድሞች ለአምላክ ሕዝቦች ጉባኤዎች እንዴት ያለ በረከት ናቸው! መንፈሳዊው የመከር ሥራ በቀጠለ መጠን ወንድሞቻቸውን ለማገልገል ራሳቸውን የሚያቀርቡ ብቃት ያላቸው ወንዶች ያስፈልጋሉ።
2 የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ያላገቡ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን ለተጨማሪ ኃላፊነት ለማሠልጠን የሚያስችል ግሩም ዝግጅት ነው። ትምህርት ቤቱ በ1987 ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በተካሄዱት 999 ክፍሎች ውስጥ 140 ገደማ ከሚሆኑ አገሮች የመጡ ከ22, 000 የሚበልጡ ተማሪዎች ሥልጠና አግኝተዋል። ለእነዚህ ወንድሞች ትምህርት ቤቱ “ታላቅ የሥራ በር” ከፍቶላቸዋል።—1 ቆሮ. 16:9
3 የትምህርት ቤቱ ዓላማ፦ የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ዓላማ ወንድሞች በድርጅቱ ውስጥ በተፈለጉበት ቦታ ኃላፊነት ወስደው ማገልገል እንዲችሉ ማሠልጠንና ብቁ እንዲሆኑ መርዳት ነው። ትምህርት ቤቱ በወንጌላዊነቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት በመካፈል፣ ለመንጋው እረኝነት በማድረግ እንዲሁም ጉባኤውን በማስተማር ረገድ ችሎታቸውን ያሳድገዋል። ከምረቃው በኋላ አንዳንድ ተማሪዎች በትውልድ አገራቸው ወይም በሌሎች አገሮች በልዩ አቅኚነት አሊያም በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንዲያገለግሉ ይመደባሉ። ሌሎች ደግሞ በትምህርት ቤቱ ከመካፈላቸው በፊት በነበሩበት ጉባኤ ወይም በአገራቸው ባለው ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ያገለግላሉ።
4 ለስምንት ሳምንታት በሚቆየው በዚህ ሥልጠና ወቅት ተማሪዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ያጠናሉ። ብዛት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በስፋት የሚመረምሩ ከመሆኑም በላይ ከእረኝነት ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶችንና በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መወጣት ስለሚቻልበት መንገድ ትምህርት ይሰጣቸዋል። ቅዱሳን ጽሑፎች አስተዳደርን፣ ፍርድ ነክና ድርጅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚሰጡትን ሐሳብም ይማራሉ። ለሕዝብ ተናጋሪነት ለየት ያለ ሥልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን መንፈሳዊ እድገታቸውን ለማፋጠን በግለሰብ ደረጃ እርዳታ ይደረግላቸዋል።
5 ከአመልካቾች የሚፈለገው ብቃት፦ በትምህርቱ ቤቱ ለመካፈል ከፍተኛ ብቃቶችን ማሟላት እንደሚያስፈልግ ጥያቄ የለውም። አመልካቾች ቢያንስ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆነው ያገለገሉ እንዲሁም ያላገቡና ከ23 እስከ 50 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆን አለባቸው። አመልካቾች ትምህርት የሚሰጥበትን ቋንቋ ማለትም እንግሊዝኛ አጣርተው የሚያነቡ፣ የሚጽፉና የሚናገሩ እንዲሁም ጥሩ ጤንነት ያላቸውና የተለየ እንክብካቤ ወይም የአመጋገብ ሥርዓት የማያስፈልጋቸው ሊሆኑ ይገባል። የዘወትር አቅኚ ለሆኑ አመልካቾች ቅድሚያ ይሰጣል።
6 ራሳቸውን ለዚህ ሥልጠና የሚያቀርቡ ወንዶች በተፈለጉበት ቦታ ለማገልገል ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውና ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። ይህም ለየት ያለ ሥራ ሲሰጠው “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” በማለት ራሱን በፈቃደኝነት እንዳቀረበው እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ያለ መንፈስ ማዳበርን ይጠይቃል። (ኢሳ. 6:8) ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ በሕይወቱ ሙሉ ትሕትናን አሳይቷል። በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመግባት ራሳቸውን የሚያቀርቡ ወንዶች ይህን የሚያደርጉት ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት ብለው ሳይሆን ለወንድሞቻቸው ባላቸው ፍቅርና እነርሱን ለማገልገል ባላቸው ፍላጎት ተገፋፍተው ሊሆን ይገባል። ተመራቂዎቹ እንዲህ ያለ ግሩም ሥልጠና ካገኙ በኋላ የተማሩትን ተግባራዊ በማድረግ ወንድሞቻቸውን የሚጠቅም ሥራ እንዲያከናውኑ ይጠበቅባቸዋል።—ሉቃስ 12:48
7 ትምህርት ቤቱ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች፦ ተመራቂዎቹ ጥልቀት ያለው ሥልጠና በሚያገኙባቸው ስምንት ሳምንታት ውስጥ ‘በእምነት ቃልና በመልካም ትምህርት ይታነጻሉ።’ (1 ጢሞ. 4:6) ይህም በተመደቡባቸው ጉባኤዎችና ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችን ለመርዳትና ለማበረታታት ብቁ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ከአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ ወንዶች በተመደቡባቸው በአብዛኞቹ ቦታዎች ወንድሞች በመስክ አገልግሎት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጨምሯል፣ ብዙ አስፋፊዎች በተለይም ወጣቶች አቅኚ ለመሆን ተገፋፍተዋል እንዲሁም ከአምላክ ሕዝቦች ጋር መተባበር ለጀመሩት አዳዲሶች በግለሰብ ደረጃ የበለጠ ትኩረት ለመስጠት ተችሏል።
8 ከ23 እስከ 50 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ያላገባህ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ነህ? በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል ለምን አታመለክትም? በይሖዋ አገልግሎት ስለምታደርገው ተሳትፎ ግብ እያወጣህ ያለህ ወጣት ነህ? ሕይወትህን ቀላል በማድረግ በዚህ “ታላቅ የሥራ በር” ለመግባት ለምን አትሞክርም? ከፍተኛ ደስታና እርካታ ታገኛለህ። በእርግጥም የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለተመራቂዎቹ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤዎችም በረከት ሆኗል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]
ከሥልጠናው ያገኙት ጥቅም
“ሥልጠናው አገልግሎቴን እንዳሻሽልና በመጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም በጥበብ እረኝነት የማድረግ ችሎታዬን እንዳሳድግ በጣም ረድቶኛል።”
“ ትምህርት ቤቱ በጉባኤ ውስጥ ያሉኝን በርካታ ኃላፊነቶች በልበ ሙሉነት ለመወጣት እንድችል ረድቶኛል።”
“ሥልጠናው ስለ ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶችና ስለ አምላክ ድርጅት ያለኝን አመለካከት ጨምሮ ያልነካው የሕይወቴ ክፍል የለም ማለት እችላለሁ።”
“ያገኘሁት ሥልጠና እርዳታ በሚያስፈልግበት ጊዜ ራሴን የማቅረብን አስፈላጊነት አስገንዝቦኛል።”