ለዘመዶቻችን ምሥራቹን እንዴት መንገር እንችላለን?
1. ለዘመዶቻችን ስንመሰክር ዘዴኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
1 ከዘመዶቻችን ጋር ይሖዋን እያመለክን ወደ አዲሱ ዓለም እጅ ለእጅ ተያይዘን ከመግባት የበለጠ ምን የሚያስደስት ነገር አለ! ምሥራቹን ለእነርሱም በማካፈል ይህን አስደሳች ተስፋ እውን ማድረግ ይቻላል። ሆኖም አስደሳች በሆነ መንገድ ምሥራቹን ለዘመዶቻችን መንገር ዘዴኛ መሆንን ይጠይቃል። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች “የዘመዶቻቸውን ትኩረት የሚስቡ ርዕሰ ጉዳዮችን አልፎ አልፎ እያነሱ ፍላጎታቸውን ለመቀስቀስ የሚሞክሩ አስፋፊዎች የተሻለ ውጤት ያገኛሉ” ብሎ ነበር። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
2. ዘመዶቻችንን ይበልጥ ለሚያሳስቧቸው ነገሮች ትኩረት መስጠታችን ፍላጎታቸውን ለመቀስቀስ የሚረዳን እንዴት ነው?
2 ፍላጎታቸውን ቀስቅስ:- የዘመዶችህን ፍላጎት እንዴት መቀስቀስ እንደምትችል አስቀድመህ በጥንቃቄ አስብበት። (ምሳሌ 15:28) በጣም የሚያሳስባቸው ጉዳይ ምንድን ነው? ምን ችግር አጋጥሟቸዋል? ትኩረታቸውን ስለሚስበው ጉዳይ የሚያብራራ አንድ ርዕስ ልታሳያቸው ወይም አንድ ልብ የሚነካ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ልታነብላቸው ትችላለህ። ራቅ ባለ ቦታ የሚኖሩ ከሆነም በደብዳቤ ወይም በስልክ እንዲህ ልታደርግ ትችላለህ። ይሖዋ እንደሚያሳድገው ተስፋ በማድረግ የእውነትን ዘር በትንሽ በትንሹ በልባቸው ውስጥ ለመዝራት ጥረት አድርግ።—1 ቆሮ. 3:6
3. ዘመዶቻችን ስለ እኛ ለማወቅ የሚፈልጓቸው ነገሮች ምሥራቹን ለመንገር አጋጣሚ የሚከፍቱልን እንዴት ነው?
3 ኢየሱስ በርካታ አጋንንት ያስወጣለትን ሰው “ወደ ቤትህ ሂድ፣ ለዘመዶችህም ጌታ ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ያሳየህን ምሕረት ንገራቸው” ብሎት ነበር። (ማር. 5:19) ሰውየው ለዘመዶቹ ሄዶ ሲነግራቸው ምን ሊሰማቸው እንደሚችል ገምት! አንተም እንደዚህ ያለ አስገራሚ ነገር ባያጋጥምህም ዘመዶችህ አንተ ወይም ልጆችህ ስለምታደርጓቸው ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ለማወቅ ይፈልጉ ይሆናል። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ስላቀረብከው ክፍል፣ በቅርብ ስለተገኘህበት ትልቅ ስብሰባ፣ በቤቴል ስላደረግኸው ጉብኝት ወይም በግልህ የነካህን አንድ ክንውን ብትነግራቸው ስለ ይሖዋና ስለ ድርጅቱ ተጨማሪ ነገሮችን ለመንገር የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትልህ ይሆናል።
4. ለዘመዶቻችን ስንመሰክር ጥንቃቄ ልናደርግባቸው የሚገቡን ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
4 ዘዴኛ ሁን:- ለዘመዶችህ ስትመሰክር በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ከመናገር ተቆጠብ። አንድ ወንድም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረበትን ጊዜ አስታውሶ እንዲህ ብሏል:- “በዚያን ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩትን ሁሉንም ነገር ለማለት ይቻላል ለእናቴ ለረጅም ሰዓታት እነግራት ነበር። ይህ ደግሞ በተለይ ከአባቴ ጋር ብዙ ጊዜ አጋጭቶናል።” አንድ ዘመድህ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመስማት ፍላጎት በሚያሳይበት ጊዜ እንኳን የምትሰጠው መልስ ይበልጥ ለማወቅ እንዲጓጓ የሚያደርገው መሆን አለበት። (ምሳሌ 25:7) በአገልግሎት ከምታገኛቸው አዳዲስ ሰዎች ጋር ስትወያይ እንደምታደርገው ሁሉ ለዘመዶችህም አክብሮት፣ ደግነትና ትዕግሥት ይኑርህ።—ቆላ. 4:6
5. ለዘመዶቻችን ምሥራቹን ስንነግራቸው ጥሩ ምላሽ ካልሰጡን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
5 በአንድ ወቅት የኢየሱስ ዘመዶች አብዷል ብለው አስበው ነበር። (ማር. 3:21) ከጊዜ በኋላ ግን አንዳንዶቹ አማኞች ሆነዋል። (ሥራ 1:14) ለዘመዶችህ እውነትን ለማካፈል ያደረግከው የመጀመሪያ ጥረት ካልተሳካ ተስፋ አትቁረጥ። ዝንባሌያቸውና ሁኔታቸው በጊዜ ሂደት ሊለወጥ ይችላል። ፍላጎታቸውን ሊቀሰቅስ የሚችል ነጥብ ለማካፈል የሚያስችልህን አጋጣሚ በንቃት ተከታተል። ዘመዶችህ የዘላለም ሕይወት በሚያስገኘው ጎዳና መጓዝ እንዲጀምሩ የመርዳት አስደሳች መብት ልታገኝ ትችላለህ።—ማቴ. 7:13, 14