የስብከቱ ሥራ እንድንጸና ይረዳናል
1 የአምላክ ቃል “በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት [እንድንሮጥ]” ይመክረናል። (ዕብ. 12:1) አንድ ሯጭ ውድድሩን በድል ለመጨረስ ጽናት እንደሚያስፈልገው ሁሉ እኛም የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ጽናት ያስፈልገናል። (ዕብ. 10:36) በታማኝነት እስከ መጨረሻው ለመጽናት ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን እንዴት ሊረዳን ይችላል?—ማቴ. 24:13
2 በመንፈሳዊ ያጠነክረናል:- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘውን ጽድቅ ስለሰፈነበት አዲስ ዓለም የሚገልጽ ግሩም ምሥራች ማወጃችን ተስፋችን ብሩህ ሆኖ እንዲቀጥል ይረዳናል። (1 ተሰ. 5:8) አዘውትረን በመስክ አገልግሎት ስንካፈል ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርነውን እውነት ለሌሎች የማሳወቅ አጋጣሚ እናገኛለን። ስንሰብክ ስለ እምነታችን ማስረጃ ለማቅረብ አጋጣሚ የምናገኝ ሲሆን ይህም በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንድንሆን ይረዳናል።
3 ሌሎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስተማር እኛ ራሳችን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሚገባ እንዲገባን ያስፈልጋል። ይህም በትምህርቱ ላይ ምርምር ማድረግና ማሰላሰልን ይጠይቃል። የምናደርገው ከፍተኛ ጥረት እውቀታችን ጥልቀት እንዲኖረው፣ እምነታችን እንዲጠነክርና መንፈሳዊነታችን እንዲታደስ ያደርግልናል። (ምሳሌ 2:3-5) በዚህ መንገድ ሌሎችን ለመርዳት በምንጥርበት ጊዜ ራሳችንን እናጠናክራለን።—1 ጢሞ. 4:15, 16
4 ‘የእግዚአብሔር ሙሉ የጦር ዕቃ’ ዋነኛ ክፍል በሆነው በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መሳተፋችን ዲያብሎስንና አጋንንቱን ለመቋቋም ያስችለናል። (ኤፌ. 6:10-13, 15) በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ራሳችንን ማስጠመዳችን አእምሯችን በሚያንጹ ነገሮች ላይ እንዲያተኩርና በሰይጣን ዓለም እንዳንበከል ይረዳናል። (ቈላ. 3:2) ሌሎችን ስለ ይሖዋ መንገዶች በምናስተምርበት ጊዜ እኛ ራሳችን ቅዱስ ምግባር ማሳየት እንዳለብን ዘወትር እናስታውሳለን።—1 ጴጥ. 2:12
5 ከአምላክ ኃይል እናገኛለን:- በመጨረሻም በወንጌላዊነት ሥራ መሳተፍ በይሖዋ ላይ መመካትን ያስተምረናል። (2 ቆሮ. 4:1, 7) ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው! እንዲህ ዓይነት እምነት ማዳበራችን አገልግሎታችንን እንድንፈጽም ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ውስጥ ምንም ዓይነት ሁኔታዎች ቢያጋጥሙን እንድንጸና ያስችለናል። (ፊልጵ. 4:11-13) እውነት ነው፣ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ መደገፍን መማር ለጽናት ዋነኛው ቁልፍ ነው። (መዝ. 55:22) የስብከቱ ሥራ እንድንጸና በብዙ መንገዶች ይረዳናል።