በቅርብ አስቀምጡት
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ይህ አባሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት ስለሚቻልባቸው መንገዶች በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ በተከታታይ ሲወጡ ከነበሩት ክፍሎች የተሰባሰቡ ቁልፍ ነጥቦችን የያዘ ነው። በቅርብ አስቀምጣችሁት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመሩበት ወቅት እንድትከልሱት ሁላችሁንም እናበረታታችኋለን። በተጨማሪም በስምሪት ስብሰባ ላይ ነጥቦቹን ማጉላት ይቻላል፤ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቾችም የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖችን ሲጎበኙ ለንግግራቸው እንደ መሠረት አድርገው ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
ክፍል 1፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሪፖርት የሚደረገው ከመቼ ጀምሮ ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ከምንጠቀምባቸው ጽሑፎች በአንዱ በመጠቀም ቅደም ተከተሉን በጠበቀ መንገድ ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ከአንድ ሰው ጋር ቋሚ የሆነ ውይይት ካደረግን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየመራን ነው። ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ካሳየናቸው በኋላ ሁለት ጊዜ ካስጠናናቸው እንዲሁም ጥናቱ እንደሚቀጥል ከተሰማን ጥናት ብለን ሪፖርት ማድረግ እንችላለን።—የመንግሥት አገልግሎታችን 7/04 ገጽ 1 ለማስጠናት የምንጠቀምባቸው ጽሑፎች
◼ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
◼ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
◼ እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
◼ የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ! በትምህርት ብዙም ያልገፉ ወይም የማንበብ ችሎታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎችን ለማስጠናት ልንጠቀምበት እንችላለን።
ክፍል 2፦ ጥናቱን ለመምራት መዘጋጀት
ትምህርቱን የተማሪውን ልብ በሚነካ መንገድ ማቅረብ ይኖርብናል። ይህ ደግሞ የተማሪውን ሁኔታ በአእምሮ ይዞ በሚገባ መዘጋጀትን ይጠይቃል።—የመንግሥት አገልግሎታችን 8/04 ገጽ 1
መዘጋጀት ያለብህ እንዴት ነው?
◼ ዋናውን ርዕስ፣ ንዑስ ርዕሶቹንና ሥዕሎቹን በመመልከት የትምህርቱን አጠቃላይ ይዘት ተመልከት።
◼ የጥያቄዎቹን መልሶች ፈልገህ ካገኘህ በኋላ ቁልፍ በሆኑት ቃላትና ሐረጎች ላይ ብቻ ምልክት አድርግ።
◼ በጥናቱ ወቅት የምታነቧቸውን ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱ ጥቅሶች ምረጥ። በጽሑፉ ኅዳግ ላይ ጥቅሶቹን በሚመለከት አጠር ያሉ ማስታወሻዎች ጻፍ።
◼ በጥናቱ ወቅት ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች በአጭሩ መከለስ እንድትችል ተዘጋጅ።
ትምህርቱን ለተማሪህ እንደሚስማማ አድርገህ አቅርበው
◼ ስለ ተማሪውና ስለሚያስፈልጉት ነገሮች ጸልይ።
◼ ተማሪው ለመረዳት ወይም ለመቀበል ሊከብዱት የሚችሉ ሐሳቦችን አስቀድመህ ለመገመት ሞክር።
◼ መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ እንዲችል ሊያስተውለው የሚገባው ነጥብ ወይም ማሻሻል ያለበት ጉዳይ ምንድን ነው? ልቡን መንካት የምችለው እንዴት ነው? ብለህ ራስህን ጠይቅ።
◼ አስፈላጊ ከሆነ ተማሪው አንድን ነጥብ ወይም ጥቅስ በሚገባ ለማስተዋል እንዲችል ለመርዳት ምሳሌ፣ ማብራሪያ ወይም የተለያዩ ጥያቄዎች አዘጋጅ።
ክፍል 3፦ ጥቅሶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም
ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናበት ዓላማ የአምላክን ቃል ተረድተውና ተቀብለው በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ “ደቀ መዛሙርት” እንዲሆኑ ለመርዳት ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ተሰ. 2:13) ስለሆነም ጥናቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተደገፈ መሆን አለበት።—የመንግሥት አገልግሎታችን 11/04 ገጽ 6
ከአምላክ ቃል አስተምር
◼ ከግል መጽሐፍ ቅዱሱ ላይ እንዴት ጥቅስ ማውጣት እንደሚቻል አሳየው።
◼ ለእምነታችን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ የሚሆኑትን ጥቅሶች አውጥታችሁ ተወያዩበት።
◼ በጥያቄዎች ተጠቀም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አንተ ከምታብራራለት ይልቅ እርሱ ራሱ ያብራራልህ።
◼ ትምህርቱን አታንዛዛው። እያንዳንዱን ጥቅስ ከተለያየ አቅጣጫ ለማብራራት መሞከር አይኖርብህም። እየተጠና ያለውን ትምህርት ግልጽ ለማድረግ የሚረዳውን ሐሳብ ብቻ ጥቀስ።
◼ የተማረውን በሥራ ላይ እንዲያውል እርዳው። ተማሪው የተነበበውን ጥቅስ በራሱ ሕይወት እንዴት ተግባራዊ ሊያደርገው እንደሚችል እንዲያስተውል እርዳው።
ክፍል 4፦ ጥናቶቻችን እንዴት እንደሚዘጋጁ ማሠልጠን
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ትምህርቱን በቅድሚያ የሚያነብ፣ መልሶቹ ላይ የሚያሰምርና በራሱ አባባል ለመመለስ የሚሞክር ከሆነ በመንፈሳዊ ፈጣን እድገት ማድረግ ይችላል። ስለዚህ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከጀመራችሁ በኋላ እንዴት መዘጋጀት እንደሚችል ለማሳየት ከተማሪው ጋር አንድ ላይ ተዘጋጁ። ከአብዛኞቹ ጥናቶቻችን ጋር አንድ ሙሉ ምዕራፍ ወይም ትምህርት አብረናቸው መዘጋጀቱ ጠቃሚ ነው።—የመንግሥት አገልግሎታችን 12/04 ገጽ 1
ምልክቶችና ማስታወሻዎች
◼ ለአንቀጾቹ ለተዘጋጁት ጥያቄዎች እንዴት ቀጥተኛ መልስ ማግኘት እንደሚችል አስረዳው።
◼ እየተጠና ካለው ጽሑፍ ላይ ቁልፍ ቃላትንና ሐረጎችን ብቻ ለይተህ ያሰመርክበትን የግል ቅጂህን አሳየው።
◼ ተማሪው እያንዳንዱ ጥቅስ በአንቀጹ ውስጥ ያለን አንድ ነጥብ እንደሚደግፍ እንዲያስተውል እርዳው። እንዲሁም በጽሑፉ ኅዳግ ላይ አጠር ያለ ማስታወሻ መያዝ እንደሚችል አሳየው።
አጠቃላይ ይዘቱን መቃኘት እና መከለስ
◼ ተማሪው የሚያጠናውን ጽሑፍ በጥልቀት መዘጋጀት ከመጀመሩ በፊት ዋናውን ርዕስ፣ ንዑስ ርዕሶቹንና ሥዕሎቹን በመመልከት የትምህርቱን አጠቃላይ ይዘት እንዴት መረዳት እንደሚችል አሳየው።
◼ ዝግጅቱን ከመደምደሙ በፊት በትምህርቱ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ነጥቦች እንዲከልስ አበረታታው።
ክፍል 5፦ ምን ያህል ትምህርት እንደምንሸፍን መወሰን
የሚሸፈነው ትምህርት መጠን በአስ ጠኚውም ሆነ በጥናቱ ችሎታና ሁኔታ ላይ የተመካ ነው።—የመንግሥት አገልግሎታችን 1/05 ገጽ 1
ጠንካራ እምነት ገንቡ
◼ አሳሳቢው ነገር ተማሪው ትምህርቱን በግልጽ መረዳቱ እንጂ በፍጥነት መጨረሱ አይደለም።
◼ ተማሪው የተማረው እንዲገባውና እንዲቀበለው ለማድረግ የሚያስፈልገውን ያህል ጊዜ መመደብ ይኖርብሃል።
◼ ለትምህርቱ መሠረት በሆኑት ቁልፍ ጥቅሶች ላይ ለመወያየት በቂ ጊዜ መድብ።
ትኩረታችሁን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ነገሮችን አስወግዱ
◼ ተማሪው ስለ ግል ጉዳዮቹ ሊነግርህ የሚፈልገው ብዙ ነገር ካለ ጥናቱን ስታበቁ ለመወያየት ዝግጅት ማድረግ ይኖርብሃል።
◼ በጥናቱ ወቅት ብዙ አታውራ። ተጨማሪ የሆኑ ሐሳቦችና ተሞክሮዎች ተማሪው መሠረታዊ ስለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ትክክለኛ እውቀት ሳይቀስም እንዲቀር እንዳያደርጉት ገደብ ልናበጅላቸው ይገባል።
ክፍል 6፦ ጥናቶቻችን ጥያቄ ሲያነሱ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
መደበኛ በሆነ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት ከጀመርን በኋላ የተለያዩ ርዕሶችን እያነሱ ከመወያየት ይልቅ ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ጥናቱን መምራት የተሻለ ይሆናል። እንዲህ ማድረጋችን ተማሪው ለሚያገኘው ትክክለኛ እውቀት ጽኑ መሠረት እንዲኖረውና መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ያስችለዋል።—የመንግሥት አገልግሎታችን 2/05 ገጽ 6
አስተዋይ ሁን
◼ እየተጠና ባለው ክፍል ላይ ጥያቄ ከተነሳ አብዛኛውን ጊዜ ወዲያውኑ ምላሽ መስጠት ይቻላል።
◼ የተነሳው ጥያቄ ከጥናት ርዕሱ ጋር ምንም ግንኙነት ከሌለው ወይም ተጨማሪ ምርምር ማድረግ የሚጠይቅ ከሆነ ሌላ ጊዜ መወያየት ትችላለህ። ጥያቄውንም በማስታወሻህ ላይ ማስፈር ጠቃሚ ነው።
◼ ጥናቱ አንዳንድ ትምህርቶችን አምኖ መቀበል ቢያዳግተው ስለጉዳዩ በጥልቀት የሚያብራሩ ጽሑፎችን ተጠቅመህ ተጨማሪ ውይይት ማድረግ ትችላለህ።
◼ እንደዚህ ካደረግህም በኋላ ተማሪው በቀረቡት ማስረጃዎች ማመን ካልቻለ ጉዳዩን ለሌላ ጊዜ በማቆየት መደበኛ የሆነውን ጥናታችሁን ቀጥሉ። ትሑት ሁን
◼ ለተነሳው ጥያቄ በእርግጠኝነት ምላሽ መስጠት የማትችል ከሆነ የራስህን አስተያየት አትስጥ።
◼ ለተማሪው ምርምር ማድረግ እንዴት እንደሚችል በሂደት አሳየው።
ክፍል 7፦ በጥናቱ ወቅት መጸለይ
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የይሖዋ እርዳታ የግድ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ጥናቱን ከመክፈታችንና ከመደምደማችን በፊት መጸለያችን ተገቢ ነው።—የመንግሥት አገልግሎታችን 3/05 ገጽ 4
ስለ ጸሎት መንገር
◼ የምታስጠናው ሰው ስለ ጸሎት የሚያውቅ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ መጸለይ ትችላለህ።
◼ ለሌሎች ጥናቶችህ ደግሞ ስለ ጸሎት መቼ ብታወያያቸው የተሻለ እንደሚሆን በማስተዋል ወስን።
◼ ጸሎት የምናቀርብበትን ምክንያት ለማስረዳት መዝሙር 25:4, 5ን እና 1 ዮሐንስ 5:14ን መጠቀም ትችላለህ።
◼ እንዲሁም ወደ ይሖዋ ስንጸልይ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መቅረባችን አስፈላጊ መሆኑን ለመግለጽ ዮሐንስ 15:16ን መጠቀም ይቻላል።
በጸሎቱ ውስጥ ምን መካተት አለበት
◼ ይሖዋ የትምህርቱ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ሊወደስ ይገባዋል።
◼ ለተማሪው ያለህን ልባዊ አሳቢነት መግለጽ ትችላለህ።
◼ ይሖዋ እየተጠቀመበት ላለው ድርጅት አመስጋኝነትህን መግለጽ ትችላለህ።
◼ ጥናትህ የተማረውን በሥራ ላይ ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት ይሖዋ እንዲባርከው መጸለይ አለብህ።
ክፍል 8፦ ተማሪዎችን ወደ ድርጅቱ መምራት
መጽሐፍ ቅዱስን ስናስጠና ግባችን መሠረተ ትምህርቶችን ማስተማር ብቻ ሳይሆን ጥናቶቻችን የክርስቲያን ጉባኤ አባል እንዲሆኑ መርዳትም ጭምር መሆን አለበት። በእያንዳንዱ የጥናት ወቅት ጥቂት ደቂቃዎች ወስደህ ስለ ይሖዋ ድርጅት አንድ ሐሳብ አካፍላቸው።—የመንግሥት አገልግሎታችን 4/05 ገጽ 6
የጉባኤ ስብሰባዎች
◼ ስለ ሁሉም ሳምንታዊ ስብሰባዎች ንገራቸው። ጥናት ከጀመራችሁበት ጊዜ አንስቶ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ጋብዛቸው።
◼ በስብሰባ ወቅት የቀረቡትን ጥሩ ነጥቦች ንገራቸው።
◼ ለኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል፣ ለትልልቅ ስብሰባዎችና ለወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት ጉጉት እንዲያድርባቸው አድርግ።
◼ በጽሑፎቻችን ላይ ያሉትን ፎቶ ግራፎች በማሳየት በስብሰባው ላይ ምን እንደሚካሄድ የተወሰነ ግንዛቤ እንዲያገኙ እርዳቸው።
◼ እንደ አንድ አካል ሆነው በዓለም ዙሪያ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን ብሮሹር እንዲያነቡ አበረታታቸው።
አድናቆታቸውን ለማነሳሳት የቪዲዮ ፊልሞችን መጠቀም
◼ የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት
◼ መላው የወንድማማች ማኅበር
◼ በመለኮታዊ ትምህርት አንድ መሆን
◼ እስከ ምድር ዳር ድረስ
ክፍል 9፦ ጥናቶቻችን መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር እንዲችሉ ማሠልጠን
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በተማሩት ነገር ላይ እምነት ሲያዳብሩ ያወቁትን ነገር ለሌሎች ለመናገር ይገፋፋሉ።—የመንግሥት አገልግሎታችን 5/05 ገጽ 1
ምሥክርነት እንዲሰጡ አበረታታቸው
◼ በሚያጠኑበት ወቅት ጓደኞቻቸውን ወይም የቤተሰባቸውን አባላት በጥናቱ ላይ እንዲገኙ ሊጋብዟቸው ይችሉ ይሆን?
◼ ከሥራ ባልደረቦቻቸው፣ አብረዋቸው ከሚማሩት ልጆች ወይም ከሌሎች ወዳጆቻቸው መካከል ለምሥራቹ ፍላጎት ያሳዩ አሉ?
እምነታቸውን ለሌሎች መናገር እንዲችሉ አሠልጥኗቸው
◼ በጥናቱ ወቅት በአንዳንድ ነጥቦች ላይ “ይህንን እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመህ ለቤተሰቦችህ እንዴት ማስረዳት ትችላለህ?” ብለህ ተማሪውን ጠይቀው።
◼ ተማሪው ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ለሌሎች በሚናገርበት ጊዜ አክብሮትና ደግነት ማሳየቱ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘብ እርዳው።
◼ እንደ አንድ አካል ሆነው በዓለም ዙሪያ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን ብሮሹር ለወዳጆቻቸው ወይም ለቤተሰባቸው አባላት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው እምነታችንና ሥራችን ለማስረዳት ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
ክፍል 10፦ ጥናቶቻችን ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት እንዲካፈሉ ማሠልጠን
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ብቃቱን እንዳሟላ ሽማግሌዎች ሲወስኑ ግለሰቡ ከጉባኤ ጋር ሆኖ በስብከቱ ሥራ ሊሳተፍ ይችላል።—የመንግሥት አገልግሎታችን 6/05 ገጽ 1
አብሮ መዘጋጀት
◼ ለአዲሱ አስፋፊ የናሙና አቀራረቦችን ከየት ማግኘት እንደሚችል አሳየው።
◼ ለአገልግሎት ክልሉ ተስማሚ የሆነ ቀላል መግቢያ እንዲመርጥ እርዳው።
◼ ገና ከጅምሩ በአገልግሎት ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲጠቀም አበረታታው።
◼ አብረኸው ተለማመድ። ሰዎች በአብዛኛው ለሚሰነዝሯቸው ሐሳቦች እንዴት በጥበብ መልስ መስጠት እንደሚችል አሳየው። አብሮ ማገልገል
◼ አብራችሁ ሆናችሁ የተዘጋጃችሁትን መግቢያ በአገልግሎት ላይ ስትጠቀምበት እንዲመለከት አድርግ።
◼ የጥናትህን ባሕርይና ችሎታ ግምት ውስጥ አስገባ። አንዳንድ ጊዜ ምናልባት የመግቢያውን የተወሰነ ክፍል ብቻ እንዲናገር ልታደርግ ትችላለህ።
◼ አዲሱ አስፋፊ በአገልግሎት የሚሳተፍበት ቋሚ ፕሮግራም እንዲኖረው እርዳው።
ክፍል 11፦ ጥናቶቻችን ተመላልሶ መጠየቅ እንዲያደርጉ መርዳት
ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ዝግጅት መደረግ ያለበት በመጀመሪያው ውይይት ወቅት ነው። ጥናትህ ያነጋገራቸውን ሰዎች የመርዳት ልባዊ ፍላጎት እንዲያድርበት አበረታታው። ተማሪው የሚያነጋግራቸውን ሰዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ መጋበዝ፣ የሚሰጡትን ሐሳብ በጥሞና ማዳመጥና የሚያሳስባቸውን ጉዳይ መረዳት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ቀስ በቀስ አሠልጥነው።—የመንግሥት አገልግሎታችን 7/05 ገጽ 1
ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ መዘጋጀት
◼ የመጀመሪያውን ቀን ውይይት ከከለሳችሁ በኋላ ተማሪው የቤቱን ባለቤት ሊማርክ የሚችል ትምህርት እንዴት መምረጥ እንዳለበት አሳየው።
◼ ከማስጠኛ ጽሑፍ ላይ በአንድ አንቀጽና በዚያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ የተመሠረተ አጠር ያለ ውይይት ለማድረግ እንዲችል ተዘጋጁ።
◼ በውይይቱ መደምደሚያ ላይ የምታነሷቸውን ጥያቄዎች ተዘጋጁ። ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ትጉዎች ሁኑ
◼ ጥናትህ ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች በሙሉ ወዲያውኑ ተመልሶ እንዲያናግር አበረታታው።
◼ ቤታቸው ያላገኛቸውን ሰዎች ለማግኘት ሳይሰለች ጥረት ማድረጉ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘብ እርዳው።
◼ አዲሱ አስፋፊ ካነጋገራቸው ሰዎች ጋር በድጋሚ ለመገናኘት እንዴት ቀጠሮ መያዝ እንዳለበትና ቃል በገባው መሠረት ተመልሶ የመሄድን አስፈላጊነት እንዲያስተውል እርዳው።
ክፍል 12፦ ተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያስጀምሩና እንዲመሩ መርዳት
እንደ ኢየሱስ አንተም በምታከናውነው አገልግሎት ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆንህ በጣም አስፈላጊ ነው። ጥናትህ በመስክ አገልግሎት ላይ የምታደርገውን ትጋት የታከለበት እንቅስቃሴ ማየቱ ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግበት ዓላማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር መሆኑን እንዲገነዘብ ይረዳዋል።—የመንግሥት አገልግሎታችን 8/05 ገጽ 1
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ግብዣ ማቅረብ
◼ ስለ አጠናኑ ሁኔታ ዝርዝር መግለጫ መስጠት ያን ያህል አስፈላጊ አለመሆኑን ለጥናትህ ንገረው።
◼ ብዙውን ጊዜ ከሚጠናው ጽሑፍ ላይ አንድ ወይም ሁለት አንቀጾችን ተጠቅሞ ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ማሳየቱ ብቻ በቂ ነው።
◼ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት ማስጀመር እንደሚቻል ከቀረቡት ሐሳቦች አንዱን አብራችሁ ከልሱ።—የመንግሥት አገልግሎታችን 8/05 ገጽ 8፤ የመንግሥት አገልግሎታችን 1/02 ገጽ 6 ተማሪዎች አስተማሪ እንዲሆኑ ማሠልጠን
◼ ተማሪዎቹ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እንዲመዘገቡ አበረታቷቸው።
◼ በሌላ ሰው ጥናት ላይ እንዲገኙ በመጋበዝ የተወሰነ ሐሳብ እንዲሰጡ አድርጉ።