ሕይወት የሚያስገኝ ትምህርት
1 ሰዎች ከአምላክ ቃል እውነትን ተረድተው ሲፈነድቁ ማየት እንዴት ያስደስታል! በእርግጥም የአምላክን እውቀትና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ለሌሎች ማካፈል እርካታ ያስገኛል። እንዲህ ያለው ትምህርት አንድን ሰው ወደ ዘላለም ሕይወት ሊመራው ይችላል።—ዮሐ. 17:3
2 ከሁሉ የላቀ የሆነበት ምክንያት:- በዛሬው ጊዜ ትምህርት በብዙ መንገዶች የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ የማይዳስሰው ርዕስ የለም። (መክ. 12:12) ሆኖም ይህ ዓይነቱ እውቀት ‘ከአምላክ ታላቅ ሥራ’ ጋር ሊወዳደር አይችልም። (ሥራ 2:11) በዓለም ላይ የሚሰጠው ትምህርት የሰው ልጆችን ወደ ፈጣሪያቸው እንዲቀርቡና ዓላማውን እንዲያውቁ አድርጓል? ከሞትን በኋላ ምን እንደምንሆን እንዲሁም መከራ ይህን ያህል የበዛው ለምን እንደሆነ ሰዎች እንዲያውቁ ረድቷል? ለሰው ልጆች ተስፋ ሰጥቷል? የቤተሰብን ዝግጅት ለማሻሻልስ አስችሏል? በጭራሽ። በሕይወት ውስጥ ለሚነሱት እጅግ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የምንችለው ከአምላክ ዘንድ ከሚመነጨው ትምህርት ብቻ ነው።
3 መለኮታዊ ትምህርት፣ በዛሬው ጊዜ በዓለም ዘንድ የጠፋው የሥነ ምግባር አቋም እንዲሻሻል ያደርጋል። የአምላክ ቃል የተማሩትን ተቀብለው በሥራ ላይ ከሚያውሉት ሰዎች ልብ ውስጥ ዘረኝነትን፣ የጎሣ ልዩነትንና ብሔርተኝነትን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። (ዕብ. 4:12) ብዙዎች ማንኛውንም ዓይነት ዓመጽ ትተው ‘አዲሱን ሰው እንዲለብሱ’ ገፋፍቷቸዋል። (ቈላ. 3:9-11፤ ሚክ. 4:1-3) ከዚህም በተጨማሪ መለኮታዊ ትምህርት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክን የማያስደስቱ ሥር የሰደዱ ልማዶችንና ባሕርያትን ማስወገድ እንዲችሉ ብርታት ሰጥቷቸዋል።—1 ቆሮ. 6:9-11
4 ትምህርቱ አሁን መሰጠቱ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? ታላቁ አስተማሪያችን አሁን ባለንበት ጊዜ የሚፈጸሙትን ነገሮች ትርጉም እንድናስተውል ይረዳናል። የፍርድ መልእክት የያዘው ትንቢታዊ ቃሉ በዓለም ዙሪያ መሰበክ ያለበትን ወቅታዊ ሐሳብ ይዟል። (ራእይ 14:6, 7) ክርስቶስ በሰማይ እየገዛ ሲሆን የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ደግሞ በቅርቡ ትጠፋለች፤ እንዲሁም የአምላክ መንግሥት ምድራዊ መንግሥታትን ለማጥፋት ተዘጋጅቶ በመጠባበቅ ላይ ነው። (ዳን. 2:44፤ ራእይ 11:15፤ 17:16) ስለዚህም ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በመግዛት ላይ የሚገኘውን በአምላክ የተሾመውን ንጉሥ ማወቃቸው፣ ከታላቂቱ ባቢሎን መውጣታቸውና በእምነት የይሖዋን ስም መጥራታቸው ከምንጊዜውም በላይ አጣዳፊ ነው። (መዝ. 2:11, 12፤ ሮሜ 10:13፤ ራእይ 18:4) እንግዲያው ወደ ሕይወት የሚመራውን ትምህርት ለሌሎች በማካፈል ረገድ የተቻለንን ያህል ሙሉ ተሳትፎ እናድርግ።