ዝግጅት በማድረግ ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
1 ለአገልግሎት ጥሩ ዝግጅት ማድረጋችን ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት እንድናሳይ ይረዳናል። እንዴት? በደንብ ከተዘጋጀን ስለ መግቢያችን እምብዛም ስለማንጨነቅ ለቤቱ ባለቤት የበለጠ ትኩረት መስጠት እንችላለን። በተጨማሪም ፍርሃታችንን እንድናሸንፍ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ከልብ በመነጨ ስሜት እንድንናገርም ያስችለናል። ታዲያ ውጤታማ መግቢያ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ተስማሚ የሆነ መግቢያ ተጠቀም:- በጥር 2006 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ከሰፈሩት የናሙና አቀራረቦች መካከል ለአካባቢያችሁ ተስማሚ የሆነውን አንድ መግቢያ ከመረጥክ በኋላ ሐሳቡን በራስህ አባባል እንዴት እንደምትናገር አስብበት። እንዲሁም እንደ ክልሉ ሁኔታ ለውጥ አድርግበት። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙውን ጊዜ ተመሳሳይ ሃይማኖት አሊያም ብሔር ያላቸውን ሰዎች በተደጋጋሚ የምታገኝ ከሆነ መግቢያህን ትኩረታቸውን የሚስብ አድርገህ ማቅረብ የምትችለው እንዴት እንደሆነ አስብ። አቀራረብህን እንደምታናግራቸው ሰዎች ሁኔታ መለዋወጥህ ከልብህ እንደምታስብላቸው ያሳያል።—1 ቆሮ. 9:22
3 መግቢያህን ተጠቅመህ ውይይት ከጀመርክ በኋላም እንኳ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግህን ቀጥል። በአገልግሎት ላይ የምትናገራቸው የመክፈቻ ቃላት በጣም ወሳኝ በመሆናቸው ሰዎች ለመግቢያህ የሚሰጡትን ምላሽ ማጤን ይኖርብሃል። ርዕሰ ጉዳዩ ትኩረታቸውን ስቦታል? ላነሳኸው ጥያቄስ መልስ ሰጥተውሃል? ካልሆነ መግቢያህ ውጤታማ እስኪሆንልህ ድረስ ማስተካከያ ልታደርግበት ትችላለህ።
4 ለማስታወስ የሚረዱ ዘዴዎች:- ብዙ አስፋፊዎች በር ካንኳኩ በኋላ ሊናገሩት ያሰቡትን መግቢያ ማስታወስ ይቸግራቸዋል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥምህ ከሆነ መግቢያህን ለሌላ ሰው እየተናገርክ ለምን አትለማመድም? እንዲህ ማድረግህ ሐሳቡን በአእምሮህ እንድትይዘው የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ በቀላሉና በሚገባ መንገድ እንድታቀርበው ያስችልሃል። ከዚህም በላይ ሰዎች የሚሰነዝሯቸውን የተለያዩ ሐሳቦች በዘዴ ለማስተናገድ እንድትችል ዝግጁ ያደርግሃል።
5 ለማስታወስ የሚረዳን ሌላው ዘዴ ደግሞ አጠር ያሉ የመግቢያ ሐሳቦችን በትንሽ ወረቀት ላይ ጽፎ መያዝ ነው። ከዚያም ወደምናንኳኳው ቤት ከመድረሳችን በፊት ወረቀቱን አየት ማድረግ እንችላለን። አንዳንዶች እንዲህ ያለውን አጭር ማስታወሻ መያዛቸው ይበልጥ ዘና እንዲሉና ከሰዎች ጋር የተሻለ ውይይት እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል። በእነዚህ መንገዶች ጥሩ ዝግጅት ማድረጋችን ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት እንድናሳይ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ምሥራቹን ለመናገር የምንጠቀምበትን መግቢያ ያሻሽልልናል።