ወደር የለሽ ለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት አድናቆት እንዲያሳዩ እርዷቸው
1 በምናገለግልበት ወቅት ሰዎች መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንዲማሩ ከማድረግ ያለፉ ነገሮችንም እናከናውናለን። ሰዎች ይሖዋ እውን ሆኖ እንዲታያቸውና ወደር የለሽ ለሆኑት ባሕርያቱ ያላቸውን አድናቆት እንዲያሳድጉ እንረዳቸዋለን። ልበ ቅን ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን መማራቸው ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል፤ እንዲሁም ‘ለጌታ እንደሚገባ ለመኖርና በሁሉ ነገር እርሱን ደስ ለማሰኘት’ ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።—ቈላ. 1:9, 10፤ 3:9, 10
2 አዲሱ የማስጠኛ መጽሐፍ:- የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ሰዎች ትኩረታቸውን በይሖዋ ባሕርያት ላይ እንዲያደርጉ ለመርዳት ያስችላል። ምዕራፍ አንድ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል:- አምላክ በእርግጥ ስለ አንተ ያስባል?፣ አምላክ ምን ዓይነት አምላክ ነው? እንዲሁም ወደ አምላክ መቅረብ ይቻል ይሆን? ከዚህም በተጨማሪ ይህ ምዕራፍ ይሖዋ ቅዱስ (አን. 10)፣ የፍትሕ ባሕርይና የሐዘኔታ ስሜት ያለው (አን. 11)፣ አፍቃሪ (አን. 13)፣ ኃያል (አን. 16)፣ ርኅሩኅ፣ ቸር፣ ይቅር ባይ፣ ታጋሽና ታማኝ (አን. 19) አምላክ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። አንቀጽ 20 ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ “ስለ ይሖዋ ይበልጥ በተማርክ መጠን ይበልጥ እውን እየሆነልህ ይሄዳል እንዲሁም ይበልጥ እየወደድከውና እየቀረብከው ትሄዳለህ” ይላል።
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ጥናቶቻችን ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ለመርዳት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ባሕርይ ጎላ ተደርጎ በተገለጸበት አንድ አንቀጽ ላይ ስንወያይ ጥናታችንን “ይህ ስለ ይሖዋ ማንነት ምን ያስተምርሃል?” ወይም ደግሞ “አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ የሚያሳየው እንዴት ነው?” በማለት ልንጠይቀው እንችላለን። በጥናቱ ወቅት አልፎ አልፎ እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ጥናቶቻችን በተማሯቸው ነገሮች ላይ እንዲያሰላስሉና ወደር የለሽ ለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ያላቸውን አድናቆት ከፍ እንዲያደርጉ ልንረዳቸው እንችላለን።
4 የክለሳ ሣጥኑን ተጠቀሙ:- እያንዳንዱን ምዕራፍ አጥንታችሁ ከጨረሳችሁ በኋላ ተማሪው “መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት” የሚለው ሣጥን ውስጥ ባሉት ሐሳቦች ላይ በራሱ አባባል አስተያየት እንዲሰጥ ጋብዙት። በጥቅሶቹ ላይ ትኩረት አድርጉ። ተማሪው ምን አመለካከት እንዳለው ለማወቅ አንዳንድ ጊዜ “መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጠውን ትምህርት እንዴት ትመለከተዋለህ?” የሚል ጥያቄ ልታቀርቡለት ትችላላችሁ። እንዲህ ማድረግ የምዕራፉን ፍሬ ሐሳብ ለማጉላት ብቻ ሳይሆን ተማሪው በእርግጥ ምን ብሎ እንደሚያምን ለማስተዋልም ይረዳችኋል። ይህም ተማሪው ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና እንዲመሠርት ይረዳዋል።