ሌሎች የአምላክ ወዳጅ እንዲሆኑ እርዷቸው
1 በዛሬው ጊዜ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች የይሖዋን መንገዶች እየተማሩ ነው። (ኢሳ. 2:2, 3) ሆኖም እነዚህ ሰዎች “በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ” እንዲሆኑ ይሖዋን መውደድ አለባቸው። (ሉቃስ 8:15፤ ማር. 12:30) ይህ ዓይነቱ ፍቅር ከሌላቸው መጥፎ ተጽዕኖዎችን የመቋቋም ጥንካሬ ወይም ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግ ድፍረት አይኖራቸውም። ሌሎች ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ማዳበር እንዲችሉ መርዳት የሚቻልበት አንደኛው መንገድ ለይሖዋ ባሕርያት ያላቸውን አድናቆት እንዲያሳድጉ ማድረግ ነው። ወደ ይሖዋ ቅረብ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ባለው ሐሳብ ላይ በጥሞና እንዲያስቡበት አበረታቷቸው።
2 ምሳሌ በመሆን:- ተግባራችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ልብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ከፍተኛ ቦታ ስትሰጡት እንዲሁም ይህ ወዳጅነት በሕይወታችሁ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ሲመለከቱ እነርሱም እንዲህ ዓይነቱን ወዳጅነት ለማዳበር ሊነሳሱ ይችላሉ። (ሉቃስ 6:40) በእርግጥም ከምንናገረው ይበልጥ ምሳሌነታችን በሌሎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።
3 ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ ለማስተማር የሚረዳቸው ዋነኛው መንገድ ራሳቸው ምሳሌ ሆነው መገኘታቸው ነው። (ዘዳ. 6:4-9) ልጆቻቸውን በእውነት ውስጥ ለማሳደግ የሚፈልጉ አንድ ባልና ሚስት በዚህ ረገድ የተሳካላቸውን ወላጆች ምክር ጠይቀው ነበር። ባልየው እንዲህ ብሏል:- “የጠየቅኳቸው ሰዎች በሙሉ የወላጆች ምሳሌነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነግረውኛል።” በመሆኑም ወላጆች ‘የይሖዋ ወዳጅ’ መሆን ምን ማለት እንደሆነ በመላ አኗኗራቸው በማሳየት ለልጆቻቸው ምሳሌ መሆን ይችላሉ።—ያዕ. 2:23
4 ከልብ የመነጨ ጸሎት:- በተጨማሪም ሌሎች ከልባቸው እንዲጸልዩ በማስተማር ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት እንዲያዳብሩ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። ኢየሱስ ያስተማረውን የናሙና ጸሎት እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበው የሚገኙትን በርካታ ልባዊ ጸሎቶች ልታሳዩአቸው ትችሉ ይሆናል። (ማቴ. 6:9, 10) ልጆቻችሁንም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁን እናንተ በምታቀርቡት ጸሎት አማካኝነት እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ልታስተምሯቸው ትችላላችሁ። የምታቀርቡትን ከልብ የመነጨ ጸሎት ሲሰሙ ለይሖዋ ያላችሁን ስሜት ይረዳሉ። ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ‘በጸሎት እንዲጸኑ’ አበረታቷቸው። (ሮሜ 12:12) በችግራቸው ጊዜ የይሖዋን እርዳታ ሲያገኙ አምላክን እንደ ልብ ወዳጃቸው በመቁጠር በእርሱ መታመንና እርሱን መውደድ ይጀምራሉ።—መዝ. 34:8፤ ፊልጵ. 4:6, 7