በአደራ የተሰጠን ውድ ሀብት
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ከአምላክ የተሰጠውን የስብከት ሥራ ከፍ አድርጎ ይመለከተው ስለነበር “የከበረ ነገር” ወይም ውድ ሀብት እንደሆነ አድርጎ ገልጾታል። (2 ቆሮ. 4:7) ይህን ተልእኮውን ለመወጣት ሲል የተለያዩ ችግሮችን እንዲሁም ስደትን በጽናት ተቋቁሟል። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ለሚያገኘው ሰው ሁሉ ሰብኳል፤ እንዲሁም በባሕርም ሆነ በየብስ ላይ በርካታ አስቸጋሪና አደገኛ ጉዞዎችን አድርጓል። የጳውሎስን ምሳሌ በመኮረጅ አገልግሎታችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሮሜ 11:13) አገልግሎታችንን ተወዳዳሪ የሌለው ሀብት የሚያደርገው ምንድን ነው?
2 የላቀ ዋጋ ያለው ውድ ሀብት:- አብዛኛውን ጊዜ ቁሳዊ ሀብት ማካበት ሐዘን የሚያስከትል ሲሆን የሚያስገኘውም ጥቅም ቢሆን ውስን ወይም ጊዜያዊ ነው። በሌላ በኩል ግን አገልግሎታችን ለእኛም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ዘላቂ ጥቅሞችን ያመጣል። (1 ጢሞ. 4:16) ቅን ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ፣ በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊ ለውጦችን እንዲያደርጉና እርግጠኛ የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። (ሮሜ 10:13-15) እኛም ለአገልግሎታችን ከፍ ያለ ግምት የምንሰጥ ከሆነ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራትና ዘላቂ እርካታ ማግኘት የምንችል ከመሆኑም ሌላ ለወደፊቱ ጊዜ አስደሳች ተስፋ ይኖረናል።—1 ቆሮ. 15:58
3 ለዚህ ውድ ሀብት ትልቅ ግምት እንደምትሰጡ አሳዩ:- አብዛኛውን ጊዜ ለአንድ ነገር የምንከፍለው ዋጋ ለዚያ ነገር ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ የሚያሳይ ነው። ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ይሖዋን ለማወደስ መጠቀማችን እንዴት ያለ መብት ነው! (ኤፌ. 5:16, 17) ጊዜያችንን የምንጠቀምበት መንገድ ለቁሳዊ ነገሮች ሳይሆን ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ የሚያሳይ መሆን አለበት። ለሌሎች የምናካፍለው በጣም ውድ ነገር ያለን እንደመሆኑ መጠን በቅንዓት እንሰብካለን እንዲሁም በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን ለሌሎች ለመናገር ንቁዎች እንሆናለን።
4 ብዙውን ጊዜ እጅግ ውድ የሆኑ ዕቃዎች ሌሎች ሊያዩአቸው በሚችሉ ቦታዎች ይቀመጣሉ እንጂ አይደበቁም። እኛም አገልግሎታችንን እንደ ውድ ሀብት አድርገን የምንመለከተው ከሆነ የሕይወታችን ዋነኛ ክፍል ይሆናል። (ማቴ. 5:14-16) በአድናቆት በተሞላ ልብ ተነሳስተን ምንጊዜም ሐዋርያው ጳውሎስን በመኮረጅ እያንዳንዱን አጋጣሚ ለአገልግሎታችን ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ በሌላ አነጋገር አገልግሎታችንን እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንደምንመለከተው እናሳይ።