አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን በማፍራቱ ሥራ ሁሉም አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል
1 አዲስ ደቀ መዝሙር የሚገኘው አንድ ሰው ብቻውን በሚያደርገው ጥረት አይደለም። ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ከእርሱ ጋር ‘አብረው የሚሠሩትን’ ሁሉ ሊጠቀም ይችላል። (1 ቆሮ. 3:6-9) አዲሶችን በግለሰብ ደረጃ መርዳት የምንችለው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የታሰበበት ሐሳብ በመስጠት ብቻ ሳይሆን የአምላክ መንፈስ በሕይወታችን እየሠራ እንዳለ በግልጽ የሚያሳየውን መልካም ባሕርይ በማንጸባረቅ ጭምር ነው። (ዮሐ. 13:35፤ ገላ. 5:22, 23፤ ኤፌ. 4:22, 23) አዲሶችን ለመርዳት ምን ተጨማሪ ነገር ማድረግ እንችላለን?
2 በጉባኤ ደረጃ:- አዲሶች በስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲጀምሩ ሁላችንም ቅድሚያውን ወስደን ሞቅ ባለ መንፈስ ሰላም ልንላቸው እንዲሁም ከስብሰባው በፊትም ሆነ በኋላ ቀርበን በማጫወት ትኩረት ልንሰጣቸው እንችላለን። አንድ ሰው በጉባኤ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘበትን ጊዜ አስታውሶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ባደግሁበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ አይቼው የማላውቀው ሁኔታ አጋጠመኝ፤ ከዚያ በፊት የማላውቃቸውን ከልብ አፍቃሪ የሆኑ ሰዎች በአንድ ቀን አገኘሁ። እውነትን እንዳገኘሁ ግልጽ ሆኖ ታየኝ።” ይህ ሰው በስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመረ ከሰባት ወር በኋላ ተጠመቀ።
3 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለሚያደርገው መንፈሳዊ እድገት ከልብ አመስግኑት። የሚያጋጥመውን ተቃውሞ በጽናት እየተቋቋመ ነው? በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ ይገኛል? የሚሰማውን ፍርሃት አሸንፎ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ሐሳብ መስጠት ጀምሯል? በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዝግቧል? አገልግሎት ጀምሯል? በየጊዜው ለሚያደርገው እድገት አመስግኑት። እንዲህ ማድረጋችሁ ሊያነቃቃውና ብርታት ሊሰጠው ይችላል።—ምሳሌ 25:11
4 አስጠኚዎችስ ምን ማድረግ ይችላሉ? አንዳንድ አስፋፊዎች ሌሎች ወንድሞች በጥናቱ ላይ እንዲገኙ በመጋበዝ ጥናቶቻቸው ከጉባኤው አባላት ጋር በግለሰብ ደረጃ በቅርብ እንዲተዋወቁ መርዳት ችለዋል። ጥናት ያስጀመራችሁትን ሰው ቶሎ ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ጋብዙት። በስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲጀምር ከሌሎች ጋር አስተዋውቁት። ጥናታችሁ ሲጋራ እንደማጨስ ያሉ መጥፎ ልማዶችን ለማሸነፍ እየታገለ ነው? ከቤተሰቡ አባላት መካከል ማጥናቱን የሚቃወም ሰው አለ? ተመሳሳይ የሆኑ ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውት ማሸነፍ ከቻለ አስፋፊ ጋር መጫወቱ ሊጠቅመው ይችላል።—1 ጴጥ. 5:9
5 አዲሶች ከጉባኤው መንፈሳዊ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ሁላችንም ልባዊ አሳቢነት በማሳየት እድገት እንዲያደርጉ ልንረዳቸው እንችላለን።