‘ብዙ ፍሬ ማፍራታችሁን’ ቀጥሉ
1 ኢየሱስ ራሱን እንደ እውነተኛ የወይን ተክል፣ አባቱን እንደ አትክልተኛ፣ በመንፈስ የተቀቡ ተከታዮቹን ደግሞ እንደ ፍሬያማ የወይን ተክል ቅርንጫፎች አድርጎ በምሳሌያዊ ሁኔታ ተናግሯል። ኢየሱስ የምሳሌያዊውን አትክልተኛ ሥራ ሲገልጽ ከወይኑ ግንድ ጋር ተጣብቆ የመቆየትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ጠቅሷል። (ዮሐ. 15:1-4) ይህ ምሳሌ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ የግል ዝምድና ያለው እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ “እውነተኛው የወይን ተክል” ቅርንጫፍ ፍሬ ማፍራት እንደሚኖርበት የሚገልጽ ትምህርት ያስተላልፋል። ‘የመንፈስን ፍሬም’ ይሁን የመንግሥቱን ፍሬ በብዛት ማፍራታችንን መቀጠል አለብን።—ገላ. 5:22, 23፤ ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20
2 የመንፈስ ፍሬ:- መንፈሳዊ እድገታችን በአብዛኛው የመንፈስ ፍሬን በምናሳይበት መጠን ሊለካ ይችላል። የአምላክን ቃል አዘውትረህ በማጥናትና በማሰላሰል የመንፈሱን ፍሬ ለማፍራት ጥረት እያደረግህ ነው? (ፊልጵ. 1:9-11) ለይሖዋ ውዳሴ እንድታመጣ እንዲሁም የማያቋርጥ መንፈሳዊ እድገት እንድታደርግ የሚያስችሉህን ባሕርያት እንድታፈራ የሚረዳህን መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት ከመጸለይ ወደ ኋላ አትበል።—ሉቃስ 11:13፤ ዮሐ. 13:35
3 የመንፈስ ፍሬ ማፍራታችን ይበልጥ ቀናተኛ አገልጋዮች እንድንሆንም ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ፍቅርና እምነት ፕሮግራማችን የተጣበበ ቢሆንም እንኳ በአገልግሎት አዘውትረን ለመካፈል የሚያስችለንን ጊዜ እንድንመድብ ይገፋፋናል። እንደ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት ያሉት ባሕርያት ለተቃዋሚዎቻችን በተገቢው መንገድ ምላሽ እንድንሰጥ ይረዱናል። ደስታ ደግሞ ሰዎች ጥሩ ምላሽ በማይሰጡበት ጊዜም እንኳ ከአገልግሎታችን እርካታ እንድናገኝ ያስችለናል።
4 የመንግሥቱ ፍሬ:- ከመንፈስ ፍሬ በተጨማሪ የመንግሥቱን ፍሬም ማፍራት እንፈልጋለን። ይህ ደግሞ “የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ [ለይሖዋ ስም] የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” ማቅረብን ይጨምራል። (ዕብ. 13:15) ይህን የምናደርገው ምሥራቹን በቅንዓትና በጽናት በማወጅ ነው። አገልግሎትህን በማሻሻል የመንግሥቱን ፍሬ በብዛት ለማፍራት ጥረት እያደረግህ ነው?
5 ኢየሱስ ታማኝ ተከታዮቹ የሚያፈሩት ፍሬ መጠን ሊለያይ እንደሚችል ጠቁሟል። (ማቴ. 13:23) በመሆኑም ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር አይኖርብንም፤ ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ምርጣችንን ልንሰጠው ይገባል። (ገላ. 6:4) በአምላክ ቃል ተጠቅመን የግል ሁኔታዎቻችንን በሐቀኝነት መመርመራችን ‘ብዙ ፍሬ በማፍራት’ ይሖዋን ማወደሳችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።—ዮሐ. 15:8