በመጠበቂያ ግንብ ላይ የተደረጉ አስደሳች ለውጦች!
1 በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ጉባኤዎች አንድ አስደሳች ማስታወቂያ ደርሷቸው ነበር። ማስታወቂያው ከጥር 2008 ጀምሮ መጠበቂያ ግንብ ሁለት የተለያዩ እትሞች እንደሚኖሩትና የመጀመሪያው እትም የሚበረከት ሁለተኛው ደግሞ ለወንድሞች ታስቦ የሚዘጋጅ መሆኑን የሚገልጽ ነበር! ‘ሁለቱን መጽሔቶች የተለያዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? የተለያዩ እትሞችን ማዘጋጀቱ ምን ጥቅሞች አሉት? መጽሔቶቹ አዳዲስ ገጽታዎች ይኖሯቸው ይሆን?’ ብላችሁ ጠይቃችሁ ይሆናል።
2 በመጽሔቶቹ መካከል ያሉት ልዩነቶች:- የወሩ የመጀመሪያ እትም የሚበረከት እትም ተብሎ ይጠራል። በዚህ እትም ውስጥ የሚገኙት ርዕሶች በሙሉ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት የሚዘጋጁ ይሆናሉ። የወሩ ሁለተኛ እትም ደግሞ የጥናት እትም ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህ እትም በአገልግሎት ላይ አይበረከትም። እትሙ በአንድ ወር ውስጥ የሚጠኑትን የጥናት ርዕሶች በሙሉ የሚያካትት ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ ክርስቲያኖችን የሚጠቅሙ ሌሎች ርዕሶችንም ይይዛል። ለማበርከት ታስቦ የሚዘጋጀው የመጠበቂያ ግንብ እትም የይሖዋ ምሥክሮችን ብቻ ሳይሆን በተለይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ያላቸው ሌሎች ሰዎችን የሚማርኩ ርዕሶች ይኖሩታል። በሌላ በኩል ደግሞ ንቁ! መጽሔት ተጠራጣሪዎችንና ከክርስትና ውጭ የሚገኙ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ አንባቢያንን ለመርዳት ታስቦ መዘጋጀቱን ይቀጥላል።
3 መለያየቱ ጥቅሙ ምንድን ነው? በጥናት እትም ላይ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች “አቅኚ” እንደሚሉት ያሉ ቃላትን በቀላሉ እንዲረዱ ለማስቻል ተጨማሪ መግለጫ መስጠቱ አስፈላጊ አይሆንም። በተጨማሪም ይህ እትም የይሖዋ ምሥክሮችንና መንፈሳዊ እድገት እያደረጉ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን የሚመለከቱ ትምህርቶችን ሊይዝ ይችላል። ለማበርከት ታስቦ የሚዘጋጀውን እትም በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? በዚህ እትም ውስጥ የሚካተቱት ርዕሰ ጉዳዮችም ሆኑ የአጻጻፍ ስልቱ በሌሎች ሰዎች ላይ ያተኮረ እንደመሆኑ መጠን የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች መጽሔቱን ከዳር እስከ ዳር ለማንበብ ይገፋፋሉ የሚል እምነት አለን። እርግጥ ነው፣ ማንኛውም የይሖዋ ምሥክር ይህን እትም ቢያነብ ጥቅም ማግኘቱ አይቀርም። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት ላይ የምናበረክተው አንድ የንቁ! እና አንድ የመጠበቂያ ግንብ እትም ብቻ መሆኑ ውጤታማ መግቢያዎችን ለመጠቀም የሚያስችል ሰፊ ጊዜ ይሰጠናል።
4 አዳዲስ ገጽታዎች:- ለሕዝብ ለማበርከት ታስቦ በሚዘጋጀው የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ አንዳንድ ማራኪ ገጽታዎችን ለማካተት ታቅዷል። ለምሳሌ መጽሔቱ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረተ ትምህርቶች ቀለል ባለ መንገድ የሚያብራራ ይሆናል። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብ ሕይወትን በተመለከተ በሚሰጠው ምክር ላይ የሚያተኩር ይሆናል። ወጣቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጨማሪ ምርምር እንዲያደርጉ የሚያነሳሱ ርዕሶችም ይኖራሉ። ከዚህም ሌላ እያንዳንዱ እትም ስለ ይሖዋ ባሕርያት የሚያስተምሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የሚያብራራ ርዕስ ይኖረዋል።
5 በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ የተደረገውን ይህንን አዲስ ለውጥ ይሖዋ እንዲባርከው እንጸልያለን። መጠበቂያ ግንብም ሆነ ንቁ! መጽሔቶች ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ የሚረዱ ግሩም መሣሪያዎች እንዲሆኑ እንመኛለን።—ማቴ. 10:11