የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ጥቅም የሚያስገኝልን እንዴት ነው?
1. በሳምንት ውስጥ የምናደርጋቸው አምስት ስብሰባዎች ምን ጥቅም ያስገኙልናል?
1 በሳምንት ውስጥ የምናደርጋቸው አምስት ስብሰባዎች በአቀራረብም ሆነ በዓላማ አንዳቸው ከሌላው ይለያሉ። ያም ሆኖ ሁሉም ስብሰባዎች ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ’ በመርዳት ረገድ ጠቃሚ ድረሻ ያበረክታሉ። (ዕብ. 10:24, 25) የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ያሉት አንዳንድ ልዩና ጠቃሚ ገጽታዎች ምንድን ናቸው?
2. የመጽሐፍ ጥናት ተሰብሳቢዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ምን ጥቅሞች አሉት?
2 መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ይረዳናል:- በጥቅሉ ሲታይ በመጽሐፍ ጥናት ላይ የሚገኙት ተሰብሳቢዎች ቁጥር በሌሎቹ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከሚገኘው እጅግ አነስተኛ ነው። ይህ ደግሞ በመንፈሳዊ እንድናድግ የሚረዳንን ወዳጅነት ለማጠናከር ሁኔታውን ቀላል ያደርገዋል። (ምሳሌ 18:24) በመጽሐፍ ጥናትህ ውስጥ ከሚገኙት ወንድሞችና እህቶች ጋር በደንብ ለመተዋወቅ ጥረት አድርገሃል? አብረውህ እንዲያገለግሉስ ጠይቀሃቸው ታውቃለህ? ይህ ዝግጅት፣ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ በቡድኑ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ግለሰብ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ስለሚረዳው በግል ማበረታቻ ለመስጠት ያስችለዋል።—ምሳሌ 27:23
3. የመጽሐፍ ጥናት፣ ጥናቶች በስብሰባ ላይ እንዲገኙና ተሰብሳቢዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የሚያበረታታው እንዴት ነው?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ በመጽሐፍ ጥናት ላይ እንዲገኙ ጋብዛችኋቸዋል? በሌሎቹ ስብሰባዎቻችን ላይ ለመገኘት የሚያመነቱ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አነስ ባለ ስብሰባ በተለይም ደግሞ በግል መኖሪያ ቤት ውስጥ በሚደረግ ስብሰባ ላይ መገኘት ላያስፈራቸው ይችላል። በስብሰባው ላይ የሚታየው ሞቅ ያለ የወዳጅነት መንፈስ ልጆችና አዳዲስ ሰዎች ሐሳብ በመስጠት በጥናቱ ላይ እንዲካፈሉ ያበረታታቸዋል። እንዲሁም ቡድኑ አነስ ያለ ስለሆነ ሐሳብ የምንሰጥባቸው በርካታ አጋጣሚዎች እናገኛለን፤ በዚህ መንገድ ይሖዋን ማወደስ እንችላለን።—መዝ. 111:1
4. የመጽሐፍ ጥናትን አመቺ የሚያደርጉት አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
4 በጥቅሉ ሲታይ መጽሐፍ ጥናቶች የሚካሄዱት ለሁሉም አስፋፊዎች አመቺ በሆኑ ቦታዎች ላይ ነው። በመሆኑም፣ ሁሉም ሰው በአቅራቢያው በሚገኝ መጽሐፍ ጥናት ውስጥ ይመደባል ማለት ባይሆንም እንኳ ከሌሎች የጉባኤ ስብሰባዎች አንጻር ሲታይ መጽሐፍ ጥናት ወደምናደርግበት ቦታ ለመድረስ ብዙ መጓዝ አይጠይቅብን ይሆናል። በተጨማሪም መጽሐፍ ጥናቱ የሚካሄድበት ቤት የስምሪት ስብሰባ ለማድረግ አመቺ ሊሆን ይችላል።
5. የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቻችን በአገልግሎት ረገድ እንዴት ሊረዳን ይችላል?
5 ለአገልግሎት ይጠቅመናል:- የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ በቡድኑ ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ አስፋፊ በአገልግሎት አዘውታሪ፣ ውጤታማና ደስተኛ እንዲሆን የመርዳት ፍላጎት አለው። በመሆኑም በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ በግል እርዳታ ለመስጠት በቡድኑ ውስጥ ከሚገኝ ከእያንዳንዱ አስፋፊ ጋር አብሮ ለማገልገል ጥረት ያደርጋል። አንድ የአገልግሎት ዘርፍ፣ ለምሳሌ ያህል ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ የሚከብድህ ከሆነ ሁኔታውን ለመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካችህ ንገረው። የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ ምናልባት በቡድኑ ውስጥ ከሚገኝ ልምድ ካለው አስፋፊ ጋር አብረህ እንድታገለግል ዝግጅት ሊያደርግልህ ይችላል። የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ መጽሐፍ ጥናቱን ሲመራ የሚጠቀምባቸውን ግሩም የማስተማርያ መንገዶች በትኩረት መከታተልህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችህን የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል ይረዳሃል።—1 ቆሮ. 4:17
6. ከመጽሐፍ ጥናት የተሟላ ጥቅም ለማግኘት መጣር ያለብን ለምንድን ነው?
6 የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት እንዴት ያለ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው! ይሖዋ ያቋቋመልን ይህ ፍቅራዊ ዝግጅት በምንኖርበት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ አስተማማኝ የሆነ መንፈሳዊ መሠረት ይዘን እንድንቀጥል ይረዳናል።—መዝ. 26:12