ለድሆች ተስፋ ፈንጥቁላቸው
1 ኢየሱስ ለድሆች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። የሰዎችን ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላትና የታመሙትን ለመፈወስ ሲል ተአምራትን የፈጸመባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ትኩረቱ ያረፈው ለድሆች “የምሥራች” በመስበኩ ላይ ነበር። (ማቴ. 11:5) ዛሬም ክርስቲያኖች የሚያከናውኑት አገልግሎት ዝቅተኛ ኑሮ ላላቸውም ሆነ ለሌሎች ጥቅም እያስገኘ ነው።—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20
2 እውነተኛ ተስፋ:- ብዙውን ጊዜ የሕዝበ ክርስትና አገልጋዮች፣ ድሆች ለቤተ ክርስቲያን ሳይሰስቱ የሚሰጡ ከሆነ እንደሚበለጽጉ ተስፋ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ድህነትን የሚያስወግደውም ሆነ ለሰው ልጆች ችግሮች በሙሉ መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ያስተምራል። (መዝ. 9:18፤ 145:16፤ ኢሳ. 65:21-23) ለድሆች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በማስተማር ተስፋ ልንፈነጥቅላቸውና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን እንዲያረኩ ልንረዳቸው እንችላለን።—ማቴ. 5:3
3 በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ፈሪሳውያን ድሆችን ዝቅ አድርገው በመመልከት አምሃሬትስ ወይም “የመሬት ሰዎች” ብለው በንቀት ይጠሯቸው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ‘ደማቸውን’ ወይም ሕይወታቸውን “ክቡር” አድርጎ ተመልክቶታል። (መዝ. 72:13, 14) እኛም የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለን እንዲህ ላሉ ሰዎች የደግነትና የአዘኔታ ተግባሮችን በማከናወን ‘እንደምንራራላቸው’ ማሳየት እንችላለን። (ምሳሌ 14:31) ጎስቋላ በሆኑ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን በሚያቃልል መንገድ መናገር ወይም ለእነሱ ለመመሥከር ማቅማማት በፍጹም አንፈልግም። ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ ከሚሰጡት መካከል ብዙዎቹ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ናቸው።
4 ከአሁን ጀምሮ እንርዳቸው:- የምናስተምረው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በክልላችን ውስጥ የሚገኙ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ዛሬም እንኳ ድህነትን የሚያባብሱ ነገሮችን እንዲያስወግዱ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስካርን፣ ቁማርን፣ ስንፍናን፣ ሲጋራ ማጨስንና ለድህነት ሊያጋልጡ የሚችሉ ሌሎች ድርጊቶችን ያወግዛል። (ምሳሌ 6:10, 11፤ 23:21፤ 2 ቆሮ. 7:1፤ ኤፌ. 5:5) ቅዱሳን መጻሕፍት ሐቀኝነትንና ‘በሙሉ ልብ’ መሥራትን ያበረታታሉ። እነዚህ ከአንድ ሠራተኛ የሚጠበቁ ባሕርያት ናቸው። (ቈላ. 3:22, 23፤ ዕብ. 13:18 NW) እንዲያውም አንድ ጥናት እንደሚያሳየው አብዛኞቹ አሠሪዎች ይበልጥ የሚፈልጉት ሐቀኛና ታማኝ የሆኑ የሥራ አመልካቾችን ነው።
5 ይሖዋ በድሆች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በግዴለሽነት አይመለከትም። በቅርቡ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ለእርዳታ የሚጮኸውን ችግረኛ ይታደገዋል።’ (መዝ. 72:12) እስከዚያው ድረስ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው ተስፋ ያዘለ መልእክት አማካኝነት ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን ጨምሮ ሌሎችን የማጽናናት ልዩ አጋጣሚ አለን።