የመንግሥቱን ተስፋ ለሌሎች እንናገራለን
1 አስጨናቂ በሆነው በዚህ የመጨረሻ ዘመን የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ተስፋ የሚያደርጉበት ነገር የላቸውም። (ኤፌ. 2:12) ሌሎች ደግሞ እምነታቸውን በቁሳዊ ሀብት፣ በሰብዓዊ ገዥዎች፣ በዘመናዊ ሳይንስና በመሳሰሉት ነገሮች ላይ ይጥላሉ። ይህ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው። እኛ ግን ስለ ወደፊቱ ጊዜ “የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ” ተስፋ በማግኘታችን ምንኛ ደስተኞች ነን!—ዕብ. 6:19
2 በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች። በሞት የተለዩን እናፈቅራቸው የነበሩ ሰዎች ትንሣኤ ያገኛሉ። (ሥራ 24:15) ከዚያ በኋላ ድህነት፣ የፍትሕ መጓደል፣ በሽታ፣ እርጅናና ሞት አይኖሩም። (መዝ. 9:18፤ ማቴ. 12:20, 21፤ ራእይ 21:3, 4) እነዚህ በቅርቡ ፍጻሜያቸውን ከሚያገኙ ይሖዋ ከሰጠን ተስፋዎች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። ከተስፋዎቹ መካከል በተለይ የትኛው ሲፈጸም ለማየት ትጓጓለህ?
3 ምሥራቹን አውጁ:- የመንግሥቱን ተስፋ በተመለከተ ያገኘነውን እውቀት ለራሳችን ብቻ ይዘን ማስቀረት አንፈልግም። ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ‘ለድኾች ወንጌልን እንድንሰብክ፣ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንድናውጅ እንዲሁም የተጨቈኑትን ነጻ እንድናወጣ’ ይገፋፋናል። (ሉቃስ 4:18) ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን በገበያ ሥፍራ እንዲሁም ሰዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰብኳል። ራሱን በስብከቱ ሥራ አስጠምዶ ነበር። (ሥራ 18:5) በአገልግሎት በቅንዓት በመካፈል የጳውሎስን ምሳሌ መከተላችን ‘የዚህ ዓለም ውጣ ውረድና የሀብት አጓጊነት’ ክርስቲያናዊ ተስፋችንን እንዳያጨልሙብን ይረዳናል።—ማር. 4:19
4 በአገልግሎት ላይ ግዴለሽ የሆኑና ለመንግሥቱ መልእክት እምብዛም ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ወይም ተቃዋሚዎች ቢያጋጥሙንም የመንግሥቱ ተስፋችን አይደበዝዝም። ‘የተስፋችን ምስክርነት እንዳይነቃነቅ አጥብቀን እንይዛለን።’ (ዕብ. 10:23 የ1954 ትርጉም) ከዚህም በላይ ፈጽሞ ‘በወንጌል አናፍርም።’ (ሮሜ 1:16) በግልጽ የሚታየው ጠንካራ እምነታችንና ጽናታችን ውሎ አድሮ አንዳንዶች እንዲያዳምጡን ሊያነሳሳቸው ይችላል።
5 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ የሆኑና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ የመጡ አንዳንድ የዓለም ሁኔታዎችን ማንሳቱ ተገቢ ቢሆንም መዓት ይመጣል ብለን የምንሰብክ ሰዎች አይደለንም። ከዚህ ይልቅ አገልግሎታችን ያተኮረው በመንግሥቱ ተስፋ ይኸውም በአምላክ መንግሥት ምሥራች ላይ ነው። እንግዲያው “የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ” ይህን የምሥራች በጽኑ እምነትና በቅንዓት እንስበክ።—ዕብ. 6:11