ሌሎች ሰዎች ይሖዋን እንዲወዱ አስተምሯቸው
1. አንዳንድ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲሳቡ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
1 ስለ ይሖዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማህበትን ወቅት ታስታውሳለህ? ወደ እሱ እንድትሳብ ያደረገህ ምን ነበር? ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች ወደር ስለሌላቸው የይሖዋ ባሕርያት በተለይም ስለ ርኅራኄውና ስለ ፍቅሩ እውቀት ማግኘታቸው ወደ ፈጣሪያችን እንዲሳቡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።—1 ዮሐ. 4:8
2, 3. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንዲያድግ ለመርዳት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
2 “አምላካችን ይህ ነው”፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ስለ ይሖዋ ፍቅርና ከእሱ ጋር ዝምድና መመሥረት አስፈላጊ ስለመሆኑ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ሌሎች ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እንዲያድግ ለመርዳት በዚህ መጽሐፍ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? በአንድ አዲስ ነጥብ ላይ ስንወያይ “ይህ እውነት ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?” ወይም “ይህ ነጥብ ይሖዋ ወደር የማይገኝለት አባት ለመሆኑ ማስረጃ የሚሆነው እንዴት ነው?” እንደሚሉት ያሉ አመራማሪ ጥያቄዎችን ማንሳት እንችላለን። በዚህ መንገድ ማስተማራችን ተማሪው ከይሖዋ ጋር ዘላቂ ዝምድና እንዲመሠርት ሊረዳው ይችላል።
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ሕያው ስለሆነው ብቸኛው እውነተኛ አምላክ እውቀት መቅሰማቸው ልዩ መብት መሆኑን እንዲገነዘቡ ስንረዳቸው “አምላካችን ይህ ነው” የሚሉት የኢሳይያስ ቃላት እውነት መሆናቸውን ይረዳሉ። (ኢሳ. 25:9) ለሰዎች የአምላክን ቃል በምናስረዳበት ወቅት፣ ይሖዋ በክርስቶስ ኢየሱስ በሚመራው ንጉሣዊ አገዛዝ አማካኝነት ዓላማውን ከፍጻሜው ሲያደርስ የሰው ልጆች በእጅጉ እንደሚባረኩ ጎላ አድርገን መግለጽ ይኖርብናል።—ኢሳ. 9:6, 7
4, 5. ይሖዋን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?
4 ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልበት መንገድ፦ ይሖዋን በፍጹም ልብ፣ ነፍስና ሐሳብ መውደድ ሲባል እንወደዋለን ብለን የመናገር ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የእሱን አስተሳሰብ መኮረጅና በዚያ መሠረት ሕይወታችንን መምራት ይኖርብናል። (መዝ. 97:10) ለአምላክ ያለን ፍቅር የሚገለጸው ትእዛዛቱን ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም መከራም ሆነ ተቃውሞ በሚያጋጥመን ጊዜም እንኳ ‘ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደርን መሆናችንን በሚያሳዩ ተግባሮች’ መካፈላችንን በመቀጠል ነው።—2 ጴጥ. 3:11 NW፤ 2 ዮሐ. 6
5 ከፍቅር ተነሳስተን የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችን ደስታ ያስገኝልናል። (መዝ. 40:8) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አምላክ ትእዛዛቱን ለአገልጋዮቹ የሰጠው ለእነሱ ዘላቂ ጥቅም ሲል መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል። (ዘዳ. 10:12, 13) አንድ ሰው ከይሖዋ መመሪያዎች ጋር ተስማምቶ በመኖር አምላክ ላከናወናቸው ድንቅ ሥራዎች አድናቆት እንዳለው ያሳያል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ፣ በይሖዋ የጽድቅ መንገድ መጓዝ ከብዙ መከራና ሥቃይ የሚያድን መሆኑን እንዲገነዘብ እርዳው።
6. አንድ ሰው ይሖዋን በመውደዱ ምን በረከት ሊያገኝ ይችላል?
6 አምላክን የሚወዱ ሰዎች የሚያገኙት በረከት፦ ይሖዋ እሱን ለሚወዱት ትሑት ሰዎች በጥልቅ የሚያስብላቸው ከመሆኑም በላይ ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ ይገልጽላቸዋል። (1 ቆሮ. 2:9, 10) እነዚህ ሰዎች የይሖዋን ዓላማ ስለሚያውቁ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩሕ አመለካከትና እርግጠኛ ተስፋ አላቸው። (ኤር. 29:11) ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ወደር የማይገኝለት ደግነቱን ይቀምሳሉ። (ዘፀ. 20:6) አምላክ ለእነዚህ ሰዎች ከፍተኛ ፍቅር ስላለው ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጥቷቸው።—ዮሐ. 3:16
7. ሌሎች ይሖዋን እንዲወዱ ስለማስተማር ምን ይሰማሃል?
7 በሰማይ ስለሚኖረው አባታችን ባወቅን መጠን ለሌሎች ሰዎች ስለ እሱ ይበልጥ እንናገራለን። (ማቴ. 13:52) ሌሎች ሰዎች በተለይ ደግሞ ልጆቻችን ይሖዋን እንዲወዱት ማስተማራችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! (ዘዳ. 6:5-7) እኛም ሆንን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ‘የይሖዋን በጎነት’ በቀመስን መጠን እሱን ዘወትር ማወደሳችንን እንቀጥል።—መዝ. 145:7