የግልና የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በጣም አስፈላጊ ናቸው!
1. በዛሬው ጊዜ የበላይ አካሉ ስለ እኛ የሚያሳስበው ነገር ምንድን ነው? ለምንስ?
1 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜም የበላይ አካሉ የይሖዋ ሕዝቦች ደኅንነት በጣም ያሳስበዋል። (ሥራ 15:6, 28) አስፈሪ የሆነው ታላቅ መከራ እየቀረበ በመጣ መጠን እያንዳንዱ የመንግሥቱ አስፋፊ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ማጠናከሩ በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህ ቀደም ለጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ተመድቦ የነበረውን ጊዜ እንዴት ልትጠቀሙበት አስባችኋል? ሁላችንም ይህን ጊዜ በቤተሰብ ሆነን ለይሖዋ አምልኮ እንድናቀርብበት ማበረታቻ ተሰጥቶናል። ይህን ጊዜ በጥበብ መጠቀማችን በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል በጥልቀት በመቆፈር በውስጡ የሚገኘውን ሕይወት ሰጪ ውኃ ለመቅዳት ያስችለናል።—መዝ. 1:1-3፤ ሮሜ 11:33, 34
2. ማታ የምናደርገውን የአምልኮ ፕሮግራም እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?
2 ማታ የሚደረግ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም፦ የቤተሰብ ራሶች ቋሚና የታሰበበት የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም እንዲኖራቸው በማድረግ ይሖዋ የጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይገባቸዋል። (ዘዳ. 6:6, 7) የቤተሰብ ኃላፊነት የሌለባቸው ያላገቡ ወንድሞችና እህቶች ይህን ጊዜ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ሁላችንም እነዚህን ‘ክፉ ቀናት’ ለመጋፈጥ የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ጥንካሬ ማግኘት እንድንችል ጥናት ለማድረግና ለማሰላሰል ‘ዘመኑን በሚገባ መዋጀት’ ይኖርብናል።—ኤፌ. 5:15, 16
3, 4. በጥናታችን ወቅት የምንጠቀምባቸውን ጽሑፎች በተመለከተ ምን ሐሳብ ተሰጥቷል? ዓላማችንስ ምን መሆን ይኖርበታል?
3 ምን ማጥናት ይቻላል? የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ ወይም በሲዲ የተዘጋጀው ዎችታወር ላይብረሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ በጣም አስደሳች እንዲሆን የሚያስችሏችሁን ርዕሶች እንድታገኙ ይረዳችኋል። ቤተሰቦች “ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?” “ልጆቻችሁን አስተምሩ” እና “ለወጣት አንባቢያን” እንደሚሉት ባሉ የመጠበቂያ ግንብ ዓምዶች ላይ መወያየት ይችላሉ። ንቁ! መጽሔትም “የወጣቶች ጥያቄ” የሚለውን ዓምድ ጨምሮ አስደናቂ ስለሆኑት የፍጥረት ሥራዎች የሚናገሩ ልብ የሚማርኩ ርዕሶችን ይዞ ይወጣል።
4 ረጋ ባለ መንፈስ የሚካሄድ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የአምላክን መመሪያዎችና ትምህርቶች በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ልብና አእምሮ ላይ ለመቅረጽ ያስችላል። (ዕብ. 4:12) በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ድርጅቱ ካዘጋጃቸው ቪዲዮዎች መካከል አንዱን በመመልከት ውይይት ልታደርጉበት ትችላላችሁ። ይህ አጋጣሚ፣ የሚጠናውን ርዕሰ ጉዳይ በመምረጥም ሆነ ጥናቱን በሚገባ በመምራት ረገድ ያላችሁን የፈጠራ ችሎታ ያዳብርላችኋል። የቤተሰባችሁ አባላት ምን ቢያጠኑ ደስ እንደሚላቸው ለምን አትጠይቋቸውም?
5. የግልና የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መንፈሳዊነታችንን ማጠናከራችን ‘ጸንተን በመቆም ይሖዋ የሚያደርግልንን ማዳን እንድናይ’ የሚያስፈልገንን ዝግጅት እንድናደርግ ይረዳናል። (ዘፀ. 14:13 NW) ወላጆች በዚህ ‘ጠማማና ክፉ በሆነው ትውልድ መካከል’ ልጆቻቸውን ለማሳደግ መለኮታዊ መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። (ፊልጵ. 2:15) ልጆች ደግሞ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚታየውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዘቀጠ የመጣውን ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ ለማሸነፍ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 22:3, 6) ባልና ሚስቶች ይሖዋ ያለበትን “በሦስት የተገመደ” ትዳራቸውን ለማጥበቅ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (መክ. 4:12) እንግዲያው የቀረውን ጊዜ ‘እጅግ ቅዱስ የሆነውን እምነታችንን’ ለመገንባት በጥበብ እንጠቀምበት!—ይሁዳ 20