በአምላክ አገዛዝ ሥር ሁሉም ፍጥረታት በሰላምና በአንድነት ይኖሩ ነበር
የአምላክ መንግሥት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ፣ ከፈጣሪያችን ከይሖዋ በቀር ሌላ ማንም ገዢ አልነበረም። የይሖዋ አገዛዝ ፍቅር የሚንጸባረቅበት ነበር። ይሖዋ ለሰዎች ውብ የሆነ መኖሪያ ማለትም የኤደንን የአትክልት ስፍራ የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ የተትረፈረፈ ምግብ አቅርቦላቸው ነበር። አርኪ የሆነ ሥራም ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28, 29፤ 2:8, 15) የሰው ልጆች ከአምላክ ፍቅራዊ አገዛዝ ባይወጡ ኖሮ በሰላም መኖር ይችሉ ነበር።
የመጀመሪያዎቹ ሰዎች፣ አምላክን ገዢያቸው አድርገው ለመቀበል አሻፈረኝ ብለዋል
መጽሐፍ ቅዱስ ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የተጠራ አንድ ዓመፀኛ መልአክ የአምላክን የመግዛት መብት እንደተገዳደረ ይገልጻል። ሰይጣን፣ ሰዎች ከአምላክ አገዛዝና አመራር ነፃ ቢሆኑ የተሻለ ሕይወት መምራት እንደሚችሉ የሚጠቁም ሐሳብ ተናገረ። የሚያሳዝነው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋንም ከእሱ ጋር በመተባበር በአምላክ ላይ ዓመፁ።—ዘፍጥረት 3:1-6፤ ራእይ 12:9
አዳምና ሔዋን የአምላክን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው ገነት የሆነችውን መኖሪያቸውን እንዲሁም ፍጹም ጤነኛ ሆነው ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን አጡ። (ዘፍጥረት 3:17-19) የእነሱ ውሳኔ፣ ከጊዜ በኋላ በወለዷቸው ልጆች ላይ ጭምር አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። መጽሐፍ ቅዱስ አዳም ኃጢአት ስለሠራ ‘ኃጢአት ወደ ዓለም እንደገባ፣ በኃጢአትም ምክንያት ሞት እንደመጣ’ ይናገራል። (ሮም 5:12) ኃጢአት ሌላም አስከፊ መዘዝ አስከትሏል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሲናገር “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” ይላል። (መክብብ 8:9) በሌላ አባባል፣ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ከሆነ ችግሮች መከሰታቸው አይቀርም ማለት ነው።
የሰው አገዛዝ ጀመረ
ናምሩድ በይሖዋ ላይ ዓምጿል
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ገዢ እንደሆነ የተገለጸው የመጀመሪያው ሰው ናምሩድ ነው። ናምሩድ በይሖዋ አገዛዝ ላይ ዓምፆ ነበር። ከናምሩድ ዘመን አንስቶ ኃያላን ሰዎች ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ግፍ ፈጽመዋል። ከ3,000 ዓመታት ገደማ በፊት ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ግፍ የተፈጸመባቸውን ሰዎች እንባ ተመለከትኩ፤ የሚያጽናናቸውም ሰው አልነበረም። ግፍ የሚፈጽሙባቸውም ሰዎች ኃይል ነበራቸው።”—መክብብ 4:1
በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2009 ያወጣው ጽሑፍ “በዓለማችን ላይ ያሉት አብዛኞቹ ችግሮች መንስኤ የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑ ከምንጊዜውም ይበልጥ በግልጽ እየታየ ነው” ብሏል።
አምላክ እርምጃ ይወስዳል!
ዓለም የተሻለ ገዢና የተሻለ የአገዛዝ ሥርዓት ያስፈልገዋል። ደግሞም ፈጣሪያችን እንዲህ ያለ ለውጥ እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል!
ጥሩ የሚባሉት ሰብዓዊ መንግሥታት እንኳ የሰው ልጆችን መሠረታዊ ችግሮች መፍታት አልቻሉም
አምላክ ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት የሚተካ መንግሥት ወይም አገዛዝ ያቋቋመ ሲሆን ይህ መንግሥት “ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።” (ዳንኤል 2:44) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲጸልዩ የኖሩት ስለዚህ መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) ሆኖም የዚህ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ የሚገዛው አምላክ ራሱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአንድ ወቅት በምድር ላይ ሰው ሆኖ ይኖር የነበረ አንድ ገዢ ሾሟል። ለመሆኑ አምላክ የመረጠው ይህ ገዢ ማን ነው?