አገልግሎታችን ለአምላክ ያለን ፍቅር ነጸብራቅ ነው
1. ኢየሱስ ለአምላክ ያለው ፍቅር ምን እንዲያደርግ ገፋፍቶታል?
1 ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናወነው በፍቅር ተገፋፍቶ ነው። ኢየሱስ የተካፈለበት እያንዳንዱ የአገልግሎት ዘርፍ ለይሖዋ ፍቅር እንዳለው በግልጽ የሚያሳይ ነበር። “እኔ አብን እንደምወድ ዓለም እንዲያውቅ አብ የሰጠኝን ትእዛዝ እየፈጸምኩ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 14:31) እኛም የኢየሱስን ፈለግ የምንከተል እንደመሆናችን መጠን ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር እንዳለን በአገልግሎታችን የማሳየት መብት አግኝተናል።—ማቴ. 22:37፤ ኤፌ. 5:1, 2
2. ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?
2 “ስምህ ይቀደስ”፦ ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ ለሰዎች ለመናገር የሚያስችለንን እያንዳንዱን አጋጣሚ ጥሩ አድርገን በመጠቀም ለአምላክ ፍቅር እንዳለን ማሳየት እንችላለን፤ በተጨማሪም ስለ ይሖዋ መናገራችን ለስሙ መቀደስ አስተዋጽኦ ያበረክታል። (መዝ. 83:18 NW፤ ሕዝ. 36:23፤ ማቴ. 6:9) እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ይሖዋን በማገልገል ስሙ ሲቀደስና ፈቃዱ ሲፈጸም ማየት የዘወትር ፍላጎታችን እንደሆነ ማሳየት እንችላለን።—ማቴ. 26:39
3. ለይሖዋ ያለን ፍቅር መሰናክሎችን እንድንወጣ የሚረዳን በምን መንገድ ነው?
3 ፍቅር መሰናክሎችን እንድንወጣ ይረዳናል፦ ለይሖዋ ፍቅር ካለን የማንወጣው መሰናክል አይኖርም። (1 ቆሮ. 13:4, 7) ኢየሱስ አገልግሎቱን ከማከናወን ወደኋላ እንዲል የሚያደርጉ በርካታ መሰናክሎች አጋጥመውት ነበር። ይሁን እንጂ ለይሖዋ ያለው ጥልቅ ፍቅርና ፈቃዱን ለመፈጸም ያለው ከፍተኛ ፍላጎት ያጋጠመውን ማንኛውንም መሰናክል እንዲወጣ አስችሎታል። (ማር. 3:21፤ 1 ጴጥ. 2:18-23) እኛም በርካታ ተፈታታኝ ችግሮች ያጋጥሙናል፤ ይሁንና ለአምላክ ያለን ፍቅር እነዚህን ችግሮች እንድንወጣ ሊረዳን ይችላል። ኢየሱስ የተወልንን ምሳሌ በጥብቅ መከተላችን አገልግሎታችንን ለመፈጸም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንድናደርግ ይገፋፋናል። የቤተሰብ ተቃውሞ፣ ጤና ማጣት፣ የዕድሜ መግፋት ወይም የሰዎች ግዴለሽነት ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮች ቢሆኑም አገልግሎታችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ በማከናወን ለይሖዋ ያለንን ፍቅር በተግባር ከማሳየት ሊያግዱን አይችሉም።
4. ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምን መብት አስገኝቶልናል?
4 ፍቅር ከፍተኛ ኃይል አለው፤ አምላክን በሙሉ ነፍሳችን እንደምንወደው በአገልግሎታችን ማሳየት መቻላችን በእርግጥም ትልቅ መብት ነው። (1 ቆሮ. 13:13) የይሖዋ ስም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚቀደስበት ቀን በፍጥነት እየቀረበ በመጣ መጠን ‘ፍቅራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛ እንዲሄድ’ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።—ፊልጵ. 1:9፤ ማቴ. 22:36-38