ለጥናቶቻችሁ ‘ነፍሳችሁን አካፍሉ’
1. አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመርዳት ምን ይጠይቃል?
1 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ራሱን መወሰን የሚችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ለመርዳት በቋሚነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመምራት ያለፈ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከሚያስተምራቸው ሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ሲገልጽ ራሱን ልጆቿን ከምትንከባከብ የምታጠባ እናት ጋር አመሳስሏል። እኛም በተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ለመርዳት “የገዛ ነፍሳችንን” ለማካፈል ዝግጁዎች ነን።—1 ተሰ. 2:7-9
2. ከልብ የመነጨ አሳቢነት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? አሳቢነት ማሳየት የምንችልባቸው ምን ምን መንገዶች አሉ?
2 ልባዊ አሳቢነት አሳዩ፦ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የተማረውን በተግባር ማዋል ሲጀምር ሕሊናው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከማያከብሩ ሰዎች ጋር የነበረውን ወዳጅነት እንዲያቆም ይገፋፋዋል። (1 ጴጥ. 4:4) ቤተሰቦቹም ሊጠሉት ይችላሉ። (ማቴ. 10:34-36) በዚህ ጊዜ ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን ከልብ የመነጨ አሳቢነት በማሳየት የተፈጠረውን ክፍተት መድፈን እንችላለን። አንድ ተሞክሮ ያካበተ ሚስዮናዊ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥቷል፦ “ጥናቱ እንዳበቃ ለመሄድ አትቸኩሉ። ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነ ከእሱ ጋር ቆይታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ተጫወቱ።” ለተማሪያችሁ የሚያስፈልገውን እርዳታ ለማበርከት ንቁዎች ሁኑ። ለምሳሌ ያህል፣ ጥናታችሁ ሲታመም ስልክ ልትደውሉለት ወይም ሄዳችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ? በስብሰባ ላይ አብራችሁት ልትቀመጡና ካስፈለገም ልጆቹን በመያዝ ልታግዙት ትችላላችሁ?
3. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከጉባኤው ማበረታቻ እንዲያገኝ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
3 ከጉባኤው የሚገኝ እርዳታ፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ በሚኖርበት አካባቢ እያገለገልክ ከሆነ የአገልግሎት ጓደኛህን ለማስተዋወቅ ወደ ጥናትህ ቤት ለምን ጎራ አትልም? የሚቻል ከሆነ በጥናቱ ላይ እንዲገኙ ሽማግሌዎችን ጨምሮ የተለያዩ አስፋፊዎችን አልፎ አልፎ መጋበዝ ትችላለህ። በተጨማሪም ማስጠናት እንደጀመርክ ብዙም ሳትቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ አበረታታው። እንዲህ ማድረጉ ወደፊት መንፈሳዊ ቤተሰቦቹ ከሚሆኑት የጉባኤው አባላት ጋር የሚያንጽ ወዳጅነት እንዲመሠርት አጋጣሚ ይከፍትለታል።—ማር. 10:29, 30፤ ዕብ. 10:24, 25
4. ትጋታችን የሚክሰን እንዴት ነው?
4 ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ልጆቹን በመንፈሳዊ የሚረዳ አንድ ወላጅ ልጆቹ ከይሖዋ ጎን ሲቆሙና በእውነት ጎዳና ሲመላለሱ ሲመለከት በጣም ይደሰታል። (3 ዮሐ. 4) እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ለመርዳት ነፍሳችንን ስናካፍል ተመሳሳይ ደስታ እናገኛለን።