ለመስበክ ብቁ ነኝ?
1. ለመስበክ ብቃት የለኝም የሚል ስሜት ሊሰማን የማይገባው ለምንድን ነው?
1 እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ በአእምሯችሁ የሚመላለስ ከሆነ አይዟችሁ! የአምላክ አገልጋዮች ለመሆን ብቁ የሚያደርገን መደበኛ ትምህርት መከታተላችን ወይም በተፈጥሯችን ልዩ ተሰጥኦ ያለን መሆናችን አይደለም። በጥንት ጊዜ የኖሩ አንዳንድ ደቀ መዛሙርት “ያልተማሩ” እንደነበሩ ተገልጿል። ያም ሆኖ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ለመከተል ቆርጠው ስለነበር ምሥራቹን በመስበክ የተዋጣላቸው ነበሩ።—ሥራ 4:13፤ 1 ጴጥ. 2:21
2. የኢየሱስን ትምህርቶች የተለዩ ያደረጓቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
2 ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ፦ ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ያልተወሳሰበ፣ ተግባራዊ ሊሆን የሚችልና በቀላሉ የሚገባ ነበር። የሚያነሳቸው ጥያቄዎች፣ ምሳሌዎቹና ያልተወሳሰቡት መግቢያዎቹ የአድማጮቹን ትኩረት የሚስቡ ነበር። (ማቴ. 6:26) በተጨማሪም ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት ያሳይ ነበር። (ማቴ. 14:14) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ይሖዋ እንደላከውና ተልዕኮውን ለመፈጸም ኃይል እንደሰጠው ስለሚያውቅ በልበ ሙሉነትና በሥልጣን ይናገር ነበር።—ሉቃስ 4:18
3. ይሖዋ አገልግሎታችንን እንድንፈጽም የሚረዳን እንዴት ነው?
3 ይሖዋ ይረዳናል፦ ታላቁ አስተማሪያችን በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ምሥራቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመስበክ የሚያስፈልገንን ሥልጠና ይሰጠናል። (ኢሳ. 54:13) ይሖዋ፣ ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ በጽሑፍ እንዲሰፍርና እስከ ዘመናችን እንዲቆይ ስላደረገ የኢየሱስን የማስተማር ዘዴ መመርመርና መከተል እንችላለን። ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጠን ከመሆኑም ሌላ በጉባኤ ስብሰባዎች አማካኝነት ያሠለጥነናል። (ዮሐ. 14:26) በተጨማሪም ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ሊረዱን የሚችሉ ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎች ይሰጠናል።
4. ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች ለመንገር ብቁ እንደሆንን ሊሰማን ይገባል የምንለው ለምንድን ነው?
4 “ብቃታችንን ያገኘነው ከአምላክ” እንደመሆኑ መጠን ለመስበክ ብቁ እንደሆንን እንዲሰማን የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለን። (2 ቆሮ. 3:5) በይሖዋ ከታመንን እንዲሁም ፍቅራዊ ዝግጅቶቹን በሚገባ ከተጠቀምንባቸው “ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ” ሆነን እንገኛለን።—2 ጢሞ. 3:17