በአገልግሎታችን ትዕግሥተኛ መሆን ይገባናል
1. ይሖዋ ለሰው ልጆች ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው?
1 አምላክ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ለሰው ልጆች ከፍተኛ ትዕግሥት አሳይቷል። (ዘፀ. 34:6፤ መዝ. 106:41-45፤ 2 ጴጥ. 3:9) ትዕግሥቱን በዋነኝነት ካሳየባቸው መንገዶች አንዱ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲካሄድ ማድረጉ ነው። ይሖዋ የሰው ልጆችን ለ2,000 ዓመታት የታገሠ ሲሆን አሁንም ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ራሱ መሳቡን አላቆመም። (ዮሐ. 6:44) እኛስ በአገልግሎታችን የይሖዋን ትዕግሥት ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?
2. በክልላችን ውስጥ ስንሠራ ትዕግሥት ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
2 ከቤት ወደ ቤት ማገልገል፦ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት ክልል ውስጥ “ያለማሰለስ” በመስበክ የይሖዋን ትዕግሥት ማንጸባረቅ እንችላለን። (ሥራ 5:42) በአገልግሎት ላይ ግድ የለሽ፣ ፌዘኛና ተቃዋሚ የሆኑ ሰዎች ቢያጋጥሙንም በትዕግሥት እንጸናለን። (ማር. 13:12, 13) በተጨማሪም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል፤ ሆኖም የዘራነውን የእውነት ዘር ውኃ ለማጠጣት የምናደርገውን ጥረት ባለማቋረጥ ትዕግሥት እናሳያለን።
3. ተመላልሶ መጠየቅ በምናደርግበትም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በምንመራበት ወቅት ትዕግሥት ማሳየት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች፦ አንድን ተክል ማሳደግ ትዕግሥት ይጠይቃል። ተክሉን መንከባከብ እንችል ይሆናል፤ እድገቱን ማፋጠን ግን አንችልም። (ያዕ. 5:7) በተመሳሳይም አንድ ሰው መንፈሳዊ እድገት የሚያደርገው ቀስ በቀስ እንዲሁም ደረጃ በደረጃ ነው። (ማር. 4:28) የምናስጠናቸው ሰዎች ቀደም ሲል የሚያምኑባቸውን የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶች መተው ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ጥናቶቻችን ለውጥ እንዲያደርጉ በመጫን እድገታቸውን ለማፋጠን መሞከር የለብንም። የአምላክ መንፈስ በተማሪው ልብ ውስጥ ገብቶ ሥራውን ለመሥራት የሚያስችል በቂ ጊዜ እንዲያገኝ ትዕግሥት ያስፈልጋል።—1 ቆሮ. 3:6, 7
4. ትዕግሥተኛ መሆን ለማያምኑ ዘመዶቻችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመመሥከር ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
4 የማያምኑ ዘመዶች፦ የማያምኑ ዘመዶቻችን እውነትን እንዲያውቁ ከልብ የምንመኝ ቢሆንም ስለ እምነታችን ለመንገር ተስማሚ የሆነ ጊዜ በመጠበቅ እንዲሁም በአንድ ጊዜ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ላለማካፈል በመጠንቀቅ ትዕግሥት እናሳያለን። (መክ. 3:1, 7) እስከዚያው ድረስ ግን እነዚህ ሰዎች አኗኗራችንን በማየት እውነት ምን ያህል እንደለወጠን እንዲገነዘቡ ማድረግ እንችላለን፤ እንዲሁም ስለ እምነታችን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ለማስረዳት ምንጊዜም ዝግጁዎች ሆነን እንጠብቃለን። (1 ጴጥ. 3:1, 15) በእርግጥም በአገልግሎታችን ትዕግሥተኛ መሆናችን ጥሩ ውጤት የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ የሰማዩ አባታችንን ያስደስተዋል።