ልጆቻችሁ ዝግጁ ናቸው?
1. ተማሪዎች ዝግጁ መሆናቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
1 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አዲስ የትምህርት ዓመት ይጀምራል። ልጆቻችሁ አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎችና ተጽዕኖዎች እንደሚያጋጥሟቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በሌላ በኩል ደግሞ ‘ስለ እውነት ለመመሥከር’ የሚያስችሉ ለየት ያሉ አጋጣሚዎች ይከፈቱላቸዋል። (ዮሐ. 18:37) ታዲያ ልጆቻችሁ ዝግጁ ናችው?
2. ልጆቻችሁ ዝግጁ እንዲሆኑ ማወቅ የሚያስፈልጋቸው ነገር ምንድን ነው?
2 ልጆቻችሁ፣ አንድ ሰው ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው እንዲሁም በሐሰት ሃይማኖት በዓላት ላይ ተካፍሏል የሚባለው ምን ቢያደርግ እንደሆነ ያውቃሉ? ደግሞስ በእነዚህ በዓላት ላይ መካፈል ስህተት የሆነው ለምን እንደሆነ ገብቷቸዋል? ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉ፣ የፍቅር ጓደኛ እንዲይዙና አልኮል እንዲጠጡ ወይም ዕፅ እንዲወስዱ የሚደርስባቸውን ግፊት ለመቋቋም ዝግጁ ናቸው? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ‘ሃይማኖቴ አይፈቅድልኝም’ በማለት ብቻ ያበቃሉ? ወይስ የሚያምኑበትን ነገር እንዴት ማስረዳት እንዳለባቸው ያውቃሉ?—1 ጴጥ. 3:15
3. ወላጆች በቤተሰብ አምልኮ ምሽት አማካኝነት ልጆቻቸውን ማዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው?
3 በቤተሰብ አምልኮ ምሽት ተጠቀሙ፦ በትምህርት ዓመቱ በሙሉ፣ ልጆቻችሁ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው በዚያ ዙሪያ እንደምትወያዩ የታወቀ ነው። ሆኖም ትምህርት ከመጀመሩ በፊት በትምህርት ቤት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጉዳዮችን አንስታችሁ ለመወያየት ተጨማሪ ጥረት ማድረጋችሁ ልጆቻችሁ በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። አንዳንድ ጊዜ፣ የቤተሰብ አምልኮ የምታደርጉበትን ምሽት ለምን ለዚህ ዓላማ አታውሉትም? ልጆቻችሁ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ሲያስቡ በጣም የሚያስጨንቃቸው ነገር ምን እንደሆነ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። በቀደሙት ዓመታት የተወያያችሁባቸውን ጉዳዮች ልጆቻችሁ አሁን በዕድሜም ሆነ በማስተዋል ከማደጋቸው አንጻር እንደገና አንስታችሁ መወያየት ትችላላችሁ። (መዝ. 119:95) እናንተ በትምህርት ቤት እንዳለ አስተማሪ ወይም አማካሪ አሊያም ተማሪ በመሆን ልምምድ የምታደርጉበት ፕሮግራም ማካተት ትችላላችሁ። ልጆቻችሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ መስጠት እንዲችሉ እንዲሁም እንደ ማመራመር እና የወጣቶች ጥያቄ በተባሉት መጻሕፍት እንዲጠቀሙ አስተምሯቸው። አንዲት ወላጅ ልምምድ የሚያደርጉበትን ወቅት ተጠቅማ አዲስ የትምህርት ዓመት ሲከፈት ልጆቿ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ለማሳወቅ እንዴት አስተማሪዎቻቸው ፊት ቀርበው መናገር እንደሚችሉ የማዘጋጀት ልማድ አላት።—ታኅሣሥ 15, 2010 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 3-5ን ተመልከት።
4. ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ምን ያደርጋሉ?
4 በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ክርስቲያን ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ‘ለመቋቋም የሚያስቸግሩ’ እየሆኑ መጥተዋል። (2 ጢሞ. 3:1) ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች እነዚህ ሁኔታዎች ከመከሰታቸው በፊት አሻግረው ለመመልከት ይጥራሉ። (ምሳሌ 22:3) አዲሱ የትምህርት ዓመት ከመጀመሩ በፊት ልጆቻችሁ ዝግጁ እንዲሆኑ ለመርዳት የቻላችሁትን ሁሉ አድርጉ።