ከስብከቱ ሥራችን የምናርፍበት ጊዜ የለም!
1. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ወንጌላውያን ከስብከቱ ሥራ የሚያርፉበት ጊዜ እንዳለ ተሰምቷቸው አያውቅም እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?
1 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ቀናተኛ ወንጌላውያን ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ምሥራቹን “ያለማሰለስ” ይሰብኩ ነበር። (ሥራ 5:42) በመሆኑም ከቤት ወደ ቤት በሚያገለግሉበት ወቅት በመንገድ ላይ ለሚያገኟቸው ሰዎችም ይሰብኩ እንደነበር እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲሁም አገልግሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ገበያ በሚሄዱበት ጊዜ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይሉ ግልጽ ነው። እንደ ኢየሱስ ሁሉ እነሱም ከስብከቱ ሥራ የሚያርፉበት ጊዜ እንዳለ ተሰምቷቸው አያውቅም።—ማር. 6:31-34
2. ከምንጠራበት ስም ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ምን ማድረግን ይጠይቃል?
2 ዘወትር ዝግጁ መሆን፦ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው መጠሪያችን የምንሠራውን ሥራ ብቻ ሳይሆን ማንነታችንንም ጭምር የሚገልጽ ነው። (ኢሳ. 43:10-12) ስለሆነም ከቤት ወደ ቤት ስንመሠክር ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጊዜያትም ስለ ተስፋችን መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁዎች መሆን አለብን። (1 ጴጥ. 3:15) መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ስለሚያስችሉህ ሁኔታዎች አስቀድመህ በማሰብ ምን ብለህ እንደምትናገር ትዘጋጃለህ? ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች መስጠት እንድትችል ምንጊዜም ጽሑፎች ትይዛለህ? (ምሳሌ 21:5) የምታገለግለው ከቤት ወደ ቤት ብቻ ነው? ወይስ ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ በሌሎች አጋጣሚዎችም ምሥራቹን ለሰዎች ትሰብካለህ?
3. “አማራጭ” ምሥክርነት የሚለው ስያሜ በመንገድ ላይ፣ በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች፣ በመናፈሻዎች፣ በንግድ ቦታዎችና በሌሎች አካባቢዎች የሚደረገውን የስብከት ሥራ ጥሩ አድርጎ አይገልጽም የምንለው ለምንድን ነው?
3 “አማራጭ” መንገድ አይደለም፦ በመንገድ ላይ፣ በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች፣ በመናፈሻዎች፣ በንግድ ቦታዎች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የሚደረገውን የስብከት ሥራ ለማመልከት “አማራጭ” የሚለውን ቃል የተጠቀምንባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሁንና “አማራጭ” የሚለው ቃል በእነዚህ ቦታዎች መስበክ ከተለመደው ውጪ እንደሆነ ወይም ለምርጫ እንደተተወ ሊያመለክት ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በአደባባይ” እና ከቤት ወደ ቤት እንደሰበከ ተናግሯል። (ሥራ 20:20) ስለዚህ ‘የአደባባይ’ ምሥክርነት የሚለው መጠሪያ “አማራጭ” ምሥክርነት ከሚለው የተሻለ ነው። ከቤት ወደ ቤት የምናደርገው አገልግሎት ዋነኛውና ውጤታማው መንገድ በመሆኑ የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች ለማዳረስ ወደፊትም በዚህ መንገድ መጠቀማችንን እንቀጥላለን። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ወንጌላውያን ትኩረት ያደረጉት በቤቶች ላይ ሳይሆን በሰዎች ላይ ነበር። እውነትን ለሰዎች ለመስበክ እያንዳንዱን አጋጣሚ ተጠቅመዋል፤ በሌላ አባባል በአደባባይ፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ እና ከቤት ወደ ቤት አገልግለዋል። እኛም አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም ተመሳሳይ አመለካከት ለመያዝ እንጣር።—2 ጢሞ. 4:5