የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት በተግባር የተደገፈ እምነት፣ ክፍል 1፦ ከጨለማ መውጣት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብርሃን ከእውነት ጋር፣ ጨለማ ደግሞ ከውሸት ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል። (መዝ. 43:3፤ ኢሳ. 5:20) ሰይጣን ሔዋንን በማታለል ድቅድቅ ጨለማ ወደ ዓለም እንዲገባና ከጊዜ በኋላ የሰውን ዘር በሙሉ እንዲውጥ አደርጓል። (ራእይ 12:9) የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት በተግባር የተደገፈ እምነት፣ ክፍል 1፦ ከጨለማ መውጣት የተባለው ቪዲዮ መንፈሳዊ ብርሃን በጨለማው ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጎላ እያለ መታየት የጀመረው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። (ኢሳ. 60:1, 2) ይህንን ቪዲዮ ከተመለከትክ በኋላ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ትችላለህ?
(1) ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ የሰው ዘር በድቅድቅ ጨለማ የተዋጠው እንዴት ነው? (2) ከ1100ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ፣ ሰዎች ቤተ ክርስትያኗ የምትሄድበት ጎዳና የተሳሳተ እንደሆነ እንዲያስተውሉ የረዳቸው ምንድን ነው? (3) ሄንሪ ግሩ እና ጆርጅ ስቶርዝ እነማን ነበሩ? (4) በቻርልስ ቴዝ ራስል ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጡት በሕይወቱ የተመለከታቸው የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው? (5) ወንድም ራስል ከአባቱና ሌሎች ከሚያውቃቸው ሰዎች ጋር ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረው እንዴት ነው? በጥናታቸውስ ምን መደምደሚያዎች ላይ ደርሰዋል? (6) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ከኔልሰን ባርበር ቡድን ጋር ኅብረት የፈጠረው ለምንድን ነው? ከጊዜ በኋላ ወንድም ራስል ከዚህ ቡድን ጋር ግንኙነቱን እንዲያቋርጥ ያደረገው ምንድን ነው? (7) በሐምሌ 1879 መንፈሳዊ ብርሃን የሚፈነጥቅበት አዲስ ዘመን እንዲጀምር ምክንያት የሆነው ክንውን ምንድን ነው? (8) ከዚህ ክንውን በኋላ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምሥራቹን ያስፋፉት እንዴት ነው? (9) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከብዙ ዓመታት አስቀድሞ በ1914 ምን እንደሚፈጸም ይጠባበቁ ነበር? (10) ወንድም ራስል ከሞተ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ገጠሟቸው? (11) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ወንድም ራዘርፎርድና ሌሎች ከእሱ ጋር ታስረው የነበሩ ወንድሞች ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ምን አደረጉ? (12) ይህ ቪዲዮ ለይሖዋ ድርጅት ያለህ አድናቆት እንዲጨምር ያደረገው እንዴት ነው? (13) ይህ ቪዲዮ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙም በቅንዓት መስበክህን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እንድታደርግ የረዳህ እንዴት ነው? (14) ይህንን ቪዲዮ በመጠቀም ዘመዶቻችንን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
የቀድሞዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የተዉልን መንፈሳዊ ውርሻ እንዴት ውድ ነው! እነዚህ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ጨለማ በሆነ ዓለም ውስጥ ደፋርና ቀናተኛ ብርሃን አብሪዎች ነበሩ። እኛም የእነሱን ምሳሌ በመከተል ‘የብርሃን ልጆች ሆነን መመላለሳችንን መቀጠል’ አለብን።—ኤፌ. 5:8