እውነተኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
1 ውሸት “1. ሆን ተብሎ ለማጭበርበር የታቀደ አነጋገር ወይም ድርጊት . . . 2. የውሸት ግምት ለማሳደር የታቀደ ማንኛውም ነገር” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ዓላማውም የሚዋሸው ሰው የሚናገረው ነገር እውነት እንዳልሆነ እያወቀ ሌሎች ሰዎች ሐሰት የሆነውን ነገር እንዲያምኑት ማድረግ ነው። ሐሰት ወይም ግማሽ እውነት ብቻ በመናገር እውነቱን ማወቅ የሚገባቸውን ሰዎች ለማታለል ጥረት ያደርጋል።
2 ሰዎች የሚዋሹባቸው ምክንያቶች፦ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ይዋሻሉ። አንዳንዶች በዚህ በውድድር በተሞላ ዓለም ውስጥ ዕድገት ለማግኘት ስለ ችሎታዎቻቸው ለመዋሸት እንደሚገደዱ ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ ስህተታቸውን ወይም ጥፋታቸውን በውሸት ለመሸፈን ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ ሰዎችን ለማስደነቅ ሲሉ ያልሠሩትን ‘ሠርተናል’ ብለው በውሸት ያወራሉ። የሌሎች ሰዎችን ጥሩ ስም ለማጉደፍ፣ ከውርደት ለመዳን፣ አስቀድመው የተናገሩት ውሸት እውነት እንደሆነ ለማስመሰል ወይም አጭበርብረው የሰዎችን ገንዘብ ለመውሰድ ሲሉ የሚዋሹም አሉ።
3 ሆኖም ልማደኛ ውሸታም ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎችም በሌሎች ፊት ከመጋለጥ፣ ከቅጣትና ከመሳሰሉት ለመዳን ሲሉ ያለምንም ማመንታት ይዋሹ ይሆናል። ይህ ፍጽምና የጎደለው ሥጋችን ካሉት ድክመቶች አንዱ ነው። ይህን ዝንባሌ አስወግደን እውነትን ለመናገር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
4 እውነተኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው? እውነት፣ ታላቁ ፈጣሪያችን ለሁላችንም ያስቀመጠው የአቋም ደረጃ ነው። በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራውያን 6:18 ላይ ‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም’ ይላል። እሱን በመወከል በምድር ላይ ያገለገለው ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስም ተመሳሳይ የአቋም ደረጃ ነበረው። ኢየሱስ፣ ሊገድሉት ያስቡ ለነበሩት አይሁዳውያን መሪዎች እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ግን ከአምላክ የሰማሁትን እውነት የነገርኳችሁን እኔን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። . . . አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ውሸታም መሆኔ ነው።” (ዮሐ. 8:40, 55) ኢየሱስ “ምንም ኃጢአት አልሠራም፤ ከአንደበቱም የማታለያ ቃል አልወጣም፤” በዚህ መንገድ ለእኛ ምሳሌ ትቶልናል።—1 ጴጥ. 2:21, 22
5 ምሳሌ 6:16-19 ስሙ ይሖዋ የሆነው ፈጣሪያችን ሐሰትን እንደሚጠላ በግልጽ ይናገራል። እውነተኛ የሆነው ይህ አምላክ፣ በእሱ ፊት ተቀባይነት እንድናገኝ ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች እንድናከብር ይጠብቅብናል። በእሱ መንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃሉም “አንዳችሁ ሌላውን አትዋሹ። አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ” በማለት ያዝዘናል። (ቆላ. 3:9) የመዋሸት ልምዳቸውን ለማቆም ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች በእሱ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም፤ እሱ የሚሰጠውን የሕይወት ስጦታ አያገኙም። እንዲያውም መዝሙር 5:6 በግልጽ እንደሚናገረው አምላክ ‘ሐሰት የሚናገሩትን ያጠፋቸዋል።’ በተጨማሪም ራእይ 21:8 “የውሸታሞች ሁሉ” ዕጣ ፈንታ “ሁለተኛው ሞት” ማለትም የዘላለም ጥፋት እንደሆነ ይናገራል። ስለዚህ አምላክ ስለ ውሸት ያለውን አመለካከት መቀበላችን እውነትን እንድንናገር ጠንካራ ምክንያት ይሆነናል።
(ከታኅሣሥ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 22 እና 23 የተወሰደ)