የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 7/12 ገጽ 4-7
  • መስበክ ከመጀመራችን በፊት ፍለጋ ማድረግ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መስበክ ከመጀመራችን በፊት ፍለጋ ማድረግ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2012
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ይሖዋ ፊቱን አብርቶላቸዋል’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • በአገልግሎት ክልላችሁ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በመፈለግ ረገድ ንቁ ሁኑ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
  • መስማት የተሳናቸውን ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ውድ እንደሆኑ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • አምላክ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ያስባል
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—2012
km 7/12 ገጽ 4-7

መስበክ ከመጀመራችን በፊት ፍለጋ ማድረግ

1. የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎች ቋንቋን መሠረት በማድረግ የአገልግሎት ክልል የሚመደብላቸው ለምንድን ነው?

1 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ፣ ርቀው ከሚገኙ የምድር ክፍሎች ለመጡ ሰዎች “በተለያዩ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።” (ሥራ 2:4) በዚህም ምክንያት 3,000 የሚያህሉ ሰዎች ተጠመቁ። የሚገርመው ነገር በዚያ ከተሰበሰቡት መካከል አብዛኛዎቹ በወቅቱ የነበሩትን የተለመዱ ቋንቋዎች ምናልባትም ዕብራይስጥ ወይም ግሪክኛ መናገር ይችሉ ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ የመንግሥቱን መልእክት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲሰሙ አደረገ። ይሖዋ እንዲህ ያደረገበት አንዱ ምክንያት ብዙውን ጊዜ ሰዎች፣ የመንግሥቱን ምሥራች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲሰሙ የተሻለ ምላሽ ስለሚሰጡ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎች የአገልግሎት ክልል የሚመደብላቸው ቋንቋን መሠረት በማድረግ ነው። (የተደራጀ ሕዝብ ገጽ 107 አን. 1-2) በውጭ አገር ቋንቋ የሚመሩ ቡድኖች የራሳቸው የሆነ የአገልግሎት ክልል አይሰጣቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ቡድኖቹ በታቀፉበት ጉባኤ እንዲሁም በአቅራቢያቸው ባሉ ሌሎች ጉባኤዎች ክልል ውስጥ ለሚገኙ የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች ይሰብካሉ።

2. (ሀ) የፍለጋ ሥራ የሚባለው ምንድን ነው? ይህን ሥራ ማከናወን አስፈላጊ የሚሆነው በምን ዓይነት አካባቢዎች ነው? (ለ) የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩበት አካባቢ ያሉ ጉባኤዎች መተጋገዝ የሚችሉት እንዴት ነው? (ሐ) ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ፍላጎት ያለው ሰው ብናገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

2 ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ቋንቋ በሚናገርበት አካባቢ የሚኖሩ አስፋፊዎች ሁሉንም ቤቶች በመደዳ ማንኳኳት ይችላሉ። የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩበት ከተማ ውስጥ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በተለያዩ ቋንቋዎች የሚመሩ ጉባኤዎች በተመሳሳይ አካባቢ ሊያገለግሉ ይችላሉ። ሌሎች ጉባኤዎች፣ እናንተ የምትሰብኩበትን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ሲያገኙ መረጃ ቢሰጧችሁም የራሳችሁን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ፈልጎ የማግኘት ዋነኛ ኃላፊነት ያለበት የእናንተ ጉባኤ ወይም ቡድን ነው። (“እርስ በርስ መተጋገዝ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በመሆኑም ጉባኤያችሁ የሚመራበትን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ለማግኘት የፍለጋ ሥራ ማካሄድ አለባችሁ። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

3. አንድ ጉባኤ ወይም ቡድን የፍለጋ ሥራውን የሚያከናውንበትን ቦታ እና በዚህ ሥራ ምን ያህል ጊዜ እንደሚያሳልፍ የሚወስነው ምንድን ነው?

3 የፍለጋ ሥራውን ማደራጀት፦ የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩባቸው አካባቢዎች የፍለጋ ሥራውን በማካሄድ የምናሳልፈውን ጊዜ የሚወስነው በአካባቢው ያለው ሁኔታ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በዚያ አካባቢ ቋንቋውን የሚናገሩ ምን ያህል ሰዎች አሉ? በአካባቢው ምን ያህል አስፋፊዎች አሉ? ጉባኤው ወይም ቡድኑ የምን ያህል ሰዎች አድራሻ በእጁ አሉት? ጉባኤው በክልሉ ውስጥ ባሉ ሰፈሮች ውስጥ በሙሉ በእኩል መጠን ፍለጋ ማካሄድ አይጠበቅበትም፤ ከዚህ ይልቅ በክልሉ ውስጥ የቋንቋው ተናጋሪዎች በብዛት በሚገኙባቸው እንዲሁም በጣም ሩቅ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ ሊወስን ይችላል። ይሁንና በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች የይሖዋን ስም የመጥራት አጋጣሚ እንዲያገኙ የፍለጋ ሥራውን በደንብ በተደራጀ መልኩ ማካሄዱ አስፈላጊ ነው።​—ሮም 10:13, 14

4. (ሀ) የፍለጋው ሥራ መደራጀት ያለበት እንዴት ነው? (ለ) ጉባኤያችሁ የሚመራበትን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ለማግኘት በየትኞቹ መንገዶች መጠቀም ይቻላል?

4 የፍለጋ ሥራ ማካሄድ አስፈላጊ በሆነባቸው አካባቢዎች፣ የተለያዩ አስፋፊዎች ተመሳሳይ ወደሆነ ቦታ በመሄድ መደራረብ እንዳይፈጥሩ ለማድረግ የሽማግሌዎች አካል በተለይም ደግሞ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ የፍለጋ ሥራውን ማደራጀትና በበላይነት መከታተል ይኖርበታል። (1 ቆሮ. 9:26) በውጭ አገር ቋንቋ በሚመሩ ቡድኖች ውስጥ የሚካሄደውን የፍለጋ ሥራ ለማስተባበር ቡድኑ በታቀፈበት ጉባኤ ውስጥ ያለው የሽማግሌዎች አካል ብቃት ያለው አንድ ወንድም (የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ቢሆን ይመረጣል) ሊመርጥ ይችላል። ብዙ ጉባኤዎችና ቡድኖች በደንብ የተደራጀ አሠራር በመጠቀም ቅድመ ጥናት ያካሂዳሉ፤ በዚህ ወቅት የስልክ ማውጫ ወይም ኢንተርኔት በመመልከት የቋንቋው ተናጋሪዎች የሚጠቀሙባቸውን የተለመዱ ስሞች ማግኘት ይቻላል። ከዚያም ስልክ በመደወል ወይም በአካል በመሄድ የፍለጋ ሥራው ይከናወናል፤ ይህም በክልሉ ካርታ ላይ ምልክት ሊደረግባቸው የሚገቡት የትኞቹ ቤቶች እንደሆኑ ለመወሰን ይረዳል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ ቡድኑ የታቀፈበት ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል፣ መላው ጉባኤ አልፎ አልፎ በፍለጋው ሥራ እንዲካፈል ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል።​—“የእናንተን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ማግኘት የምትችሉባቸው መንገዶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

5. (ሀ) የፍለጋ ሥራውን የሚያከናውኑ አስፋፊዎች ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ምን ሐሳቦች ቀርበዋል? (ለ) የፍለጋ ሥራውን በምናከናውንበት ወቅት ምን ዓይነት አቀራረብ መጠቀም እንችላለን?

5 በፍለጋ ሥራው ላይ በምንሰማራበት ወቅት ሁሉ ዓላማችንን መዘንጋት አይኖርብንም። ይህ ሥራ የአገልግሎታችን ክፍል በመሆኑ መደበኛ አገልግሎት ስናከናውን የምናደርገው ዓይነት አለባበስ ሊኖረን ይገባል። ብዙዎች በፍለጋው ሥራ ላይ በሚሰማሩበት ወቅት የመግቢያ ሐሳቦችን መለማመዳቸውና በሚሰብኩበት ቋንቋ መነጋገራቸው ለሥራው ያላቸው ቅንዓት እንዳይቀንስ እንዲሁም የቋንቋ ችሎታቸው እንዲሻሻል ረድቷቸዋል። ቋንቋውን የሚናገሩ ሰዎችን በመፈለጉ ሥራ ያሳለፍነውን ሰዓት በአገልግሎት ሪፖርታችን ላይ ማካተት እንችላለን፤ የክልል ካርታና የሰዎችን አድራሻ የያዘ ዝርዝር በማዘጋጀት ያሳለፍነውን ጊዜ ግን በሪፖርታችን ላይ መመዝገብ አይኖርብንም። ቋንቋውን የሚናገር ሰው በምናገኝበት ጊዜ ምሥራቹን ለመመሥከር ጥረት ማድረግ አለብን፤ ከዚያም በክልል ካርዱ ላይ ምልክት ማድረግ እንዲቻል ለአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ወይም እሱ ለወከለው ወንድም ስለ ግለሰቡ ወዲያውኑ ማሳወቅ ይኖርብናል። ግለሰቡ ፍላጎት ቢኖረውም ባይኖረውም እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። የፍለጋ ሥራው አስፈላጊ ቢሆንም ሚዛናዊ መሆንና በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች መካፈል ይኖርብናል።​—“በፍለጋ ሥራው ላይ የሚኖረን አቀራረብ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

6. መስማት የተሳናቸው ሰዎችን በምንፈልግበት ወቅት የሚያጋጥሙን ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

6 መስማት የተሳናቸው ሰዎችን መፈለግ፦ መስማት የተሳናቸው ሰዎችን መፈለግ ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያሉት ሥራ ሲሆን ጽናትና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። መስማት የተሳነውን ሰው በስሙ፣ በአካላዊ ሁኔታው ወይም በአለባበሱ ለይቶ ማወቅ አይቻልም። ከዚህም በተጨማሪ የዚህ ግለሰብ ቤተሰቦች ወይም ጓደኞች ለእሱ ደኅንነት ሲሉ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ። መስማት የተሳናቸው ሰዎችን ለማግኘት የሚረዱትን ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችንም ለማግኘት ልንጠቀምባቸው እንችላለን።

7. (ሀ) በመኖሪያ አካባቢዎች መስማት የተሳናቸው ሰዎችን ለማግኘት ፍለጋ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የቤቱን ባለቤት ጥርጣሬ ለማስወገድ ምን ማድረግ እንችላለን?

7 በምልክት ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችና ቡድኖች፣ በመኖሪያ አካባቢዎች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስማት የተሳናቸው ሰዎችን ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ ተሳክቶላቸዋል። የቤቱ ባለቤት፣ ከጎረቤቶቹ አሊያም አብረውት ከሚሠሩ ወይም ከሚማሩ መካከል መስማት የተሳነው ሰው ያውቅ ይሆናል። በአንዳንድ አገሮች መስማት የተሳናቸው ልጆች ባሉባቸው ሰፈሮች ይህን የሚጠቁም የትራፊክ ምልክት እንዲኖር ይደረጋል፤ ምናልባት ያነጋገራችሁት ሰው እንዲህ ዓይነት ምልክት ያየበትን ቦታ ይጠቁማችሁ ይሆናል። አሊያም ደግሞ መስማት የተሳነው ዘመድ ይኖረው ይሆናል። የፍለጋ ሥራችሁን የምታከናውኑበትን ዓላማ አንዳንዶች በጥርጣሬ ሊያዩት እንደሚችሉ አስታውሱ። ይሁንና ከልብ የመነጨ ወዳጃዊ ስሜት ማሳየት እንዲሁም አጠር ያለና ትክክለኛ ማብራሪያ በአክብሮት መስጠት የቤቱን ባለቤት ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። አንዳንዶች መስማት የተሳነው ሰው ያውቅ እንደሆነ የቤቱን ባለቤት በሚጠይቁበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ወይም በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ዲቪዲዎችን ማሳየታቸው ጥሩ ውጤት አስገኝቶላቸዋል። ይህን ካደረጉ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ተስፋ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ማካፈል እንደሚፈልጉ ለቤቱ ባለቤት ይነግሩታል። የቤቱ ባለቤት መረጃ ለመስጠት ቢያቅማማም እንኳ አድራሻችሁን ወይም የጉባኤ ስብሰባ መጋበዣ ወረቀት ከእናንተ ተቀብሎ መስማት ለተሳነው ዘመዱ ወይም ጓደኛው ለመስጠት ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል።

8. አንድ ጉባኤ በምልክት ቋንቋ የሚመራ ጉባኤን ለማገዝ ምን ማድረግ ይችላል?

8 በምልክት ቋንቋ የሚመራ አንድ ጉባኤ ሰፊ የሆነ ክልል ካለው በከተማው ካሉት ሰፈሮች ውስጥ በአንዱ የሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎችን በመፈለጉ ሥራ እንዲያግዘው በአቅራቢያው ያለን ሌላ ጉባኤ በዓመት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ሊጋብዝ ይችላል። በምልክት ቋንቋ የሚመራው ጉባኤ በሚያካሂደው የአገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ ለዚህ ሥራ የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን መስጠትና ሠርቶ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። በቡድን በቡድን ሆነው እንዲያገለግሉ በሚመደቡበት ጊዜ በእያንዳንዱ ቡድን ውስጥ በምልክት ቋንቋ ከሚመራው ጉባኤ ቢያንስ አንድ አስፋፊ መካተት አለበት፤ እንዲሁም እያንዳንዱ ቡድን፣ ፍለጋ የሚካሄድበትን አካባቢ በትክክል የሚያሳይ ካርታ ሊኖረው ይገባል።

9. መስማት የተሳናቸው ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው፣ በሚዝናኑባቸው ወይም ማኅበራዊ አገልግሎት በሚያገኙባቸው ቦታዎች የፍለጋ ሥራውን ማከናወን የሚቻለው እንዴት ነው?

9 መስማት የተሳናቸው ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው፣ በሚዝናኑባቸው ወይም ማኅበራዊ አገልግሎት በሚያገኙባቸው ቦታዎችም የፍለጋ ሥራውን ማከናወን ይቻላል። አስፋፊዎች ለሁኔታው የሚስማማ ልብስ መልበስ ይኖርባቸዋል። ብዙ ሰዎችን አንድ ላይ ሰብስቦ ከማነጋገር ይልቅ አንድ ወይም ሁለት ሰዎችን ትኩረት በማይስብ መንገድ ቀርቦ ማነጋገሩ የተሻለ ነው። ጥሩ ውይይት ማድረግ ከተቻለ ደግሞ አድራሻ መለዋወጥ ይቻል ይሆናል።

10. አስፋፊዎች በንግድ ቦታዎች የፍለጋ ሥራውን ማከናወን የሚችሉት እንዴት ነው?

10 የፍለጋ ሥራውን ለማከናወን የሚረዳው ሌላ ዘዴ ደግሞ በአካባቢው ያሉ የንግድ ቦታዎችን የሚያሳይ ካርታ ማዘጋጀትና አመቺ በሆነ ወቅት ወደ እነዚህ ቦታዎች መሄድ ነው። በአንድ ካርታ ላይ የነዳጅ ማደያዎችን የሚያሳዩ ምልክቶችን ማስፈር ይቻላል። በሌሎች ካርታዎች ላይ ደግሞ የልብስ ንጽሕና መስጫ ሱቆችን፣ ምግብ ቤቶችን፣ ሆቴሎችን ወይም ሌሎች የንግድ ቦታዎችን ማካተት ይቻላል። በእያንዳንዱ ካርታ ላይ የሚታየው የንግድ ድርጅት አንድ ዓይነት ከሆነ አስፋፊዎቹ ተመሳሳይ የሆነ አቀራረብ በመጠቀም ልምድና ችሎታ ማዳበር ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሆቴሎች መስማት የተሳናቸው ደንበኞች ስለሚኖሯቸው በእንግዳ መቀበያ ላይ ለሚሠራው ሰው ስለ ሥራችን በአጭሩ ልንገልጽለት እንችላለን፤ ከዚያም አስቀድመን በፖስታ ውስጥ የከተትነውን ዲቪዲና የጉባኤ ስብሰባ መጋበዣ ወረቀት መስማት ለማይችሉ የሆቴሉ ደንበኞች እንዲሰጥልን ልንጠይቀው እንችላለን። በአንዳንድ የንግድ ቦታዎች ደግሞ ከሠራተኞች ወይም ከደንበኞች መካከል መስማት የተሳነው ሰው እንዳለ በቀጥታ መጠየቅ እንችል ይሆናል። በክልሉ ውስጥ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ትምህርት ቤት ካለ አንዳንድ ዲቪዲዎቻችን በቤተ መጻሕፍት ውስጥ እንዲቀመጡ ልንጠይቅ እንችላለን።

11. የፍለጋ ሥራ ማካሄድ የአገልግሎታችን ወሳኝ ክፍል የሆነው ለምንድን ነው?

11 አስፈላጊ የሆነ ሥራ፦ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን የመፈለጉ ሥራ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። በተጨማሪም የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች መኖሪያቸውን ቶሎ ቶሎ ሊቀያይሩ ይችላሉ፤ ይህም የአገልግሎት ክልል መዝገቡ ወቅታዊ መረጃ የያዘ እንዲሆን ማድረግ ፈታኝ እንዲሆን ያደርጋል። ያም ቢሆን ቁጥራቸው እየጨመረ በመጣ አካባቢዎች የፍለጋ ሥራው ለአገልግሎታችን አስፈላጊ ሆኗል። የመስበክ ተልእኮ የሰጠን ይሖዋ የማያዳላ አምላክ ነው። (ሥራ 10:34) “የእሱ ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞ. 2:3, 4) እንግዲያው ማንኛውንም ቋንቋ የሚናገሩ ‘መልካምና ጥሩ ልብ’ ያላቸው ሰዎችን ለማግኘት ከይሖዋ እንዲሁም ከወንድሞቻችን ጋር ተባብረን እንሥራ።​—ሉቃስ 8:15

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እርስ በርስ መተጋገዝ

በሌላ ቋንቋ የሚመራ አንድ ጉባኤ ወይም ቡድን የፍለጋ ሥራውን ለማከናወን እገዛ የሚያስፈልገው ከሆነ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በአቅራቢያው ያሉ የሌሎች ጉባኤዎች ሽማግሌዎችን ሊያነጋግር ይችላል። በዚህ ወቅት ከጉባኤው ብዙም የማይርቁ ወይም በክልላቸው ውስጥ የዚያ ቋንቋ ተናጋሪዎች በብዛት ያሏቸውን ጉባኤዎች ብቻ መጠየቁ የተሻለ ነው። እገዛ እንዲያደርጉ የተጠየቁት ጉባኤዎች በእነሱ ሥር ለሚገኙ አስፋፊዎች፣ ይህን ቋንቋ የሚናገር ሰው ካገኙ አድራሻውን ጽፈው ለጉባኤያቸው የአገልግሎት የበላይ ተመልካች እንዲሰጡ ሊነግሯቸው ይችላሉ፤ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹም አድራሻዎቹን እርዳታ ለጠየቀው ጉባኤ ወይም ቡድን ይሰጣል። በፍለጋው ሥራ በሚካፈሉ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቾች፣ ሁሉንም በሚጠቅም መንገድ ክልሉን ለመሸፈን እንዲሁም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ቋንቋቸው ወደሚነገርበት ጉባኤ ወይም ቡድን ለመምራት የሚያስችል ዘዴ ሊቀይሱ ይገባል።

አስፋፊዎች ሌላ ቋንቋ የሚናገር ሰው አግኝተው ፍላጎት እንዳለው ከተሰማቸው (ወይም መስማት የተሳነው ሰው ካገኙ) እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የተባለውን ቅጽ በአፋጣኝ ሞልተው ለጉባኤያቸው ጸሐፊ መስጠት ይኖርባቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ግለሰቡ ወዲያውኑ መንፈሳዊ እርዳታ እንዲያገኝ ያስችለዋል።​—km 5/11 ገጽ 3⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የእናንተን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ማግኘት የምትችሉባቸው መንገዶች

• የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁን፣ የቤተሰባቸውን አባላት፣ የሥራ ባልደረቦቻችሁንና ሌሎችን ጠይቁ።

• የስልክ ማውጫዎች በመመልከት የቋንቋው ተናጋሪዎች የሚጠቀሙባቸውን የተለመዱ ስሞች ማግኘት ይቻላል። የሰዎችን አድራሻ ዝርዝር የያዘና በዚህ መሠረት ስማቸውን ለማግኘት የሚረዳ ማውጫም ኢንተርኔት ላይ ወይም የስልክ ማውጫ ከሚያዘጋጅ ድርጅት ማግኘት ይቻል ይሆናል።

• እንደ ቤተ መጻሕፍት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ኮሌጆች ወዳሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመሄድ መረጃ እንዲሰጧችሁ በጥበብ ጠይቁ።

• የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች ያዘጋጇቸውን ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ፕሮግራሞች የሚመለከት መረጃ ለማግኘት ጋዜጣዎች ላይ የሚወጡ ማስታወቂያዎችን ተመልከቱ።

• ለውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች አገልግሎት ለመስጠት ወደተከፈቱ ሱቆችና ሌሎች የንግድ ቦታዎች ሂዱ።

• የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች በሚያዘወትሯቸው የንግድ ቦታዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ወይም ትራንስፖርት የሚያዝባቸው ቦታዎች ላይ ፈቃድ ጠይቃችሁ ጽሑፎችን መደርደር ይቻላል።

• የአገራችሁ ሕግ የሚፈቅድ ከሆነ የንግድ ድርጅቶች የሚያዘጋጁትን የአድራሻ ማውጫ ወይም በኢንተርኔት ላይ ሰዎችን ለመፈለግ የሚያገለግሉ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን መግዛት ትችላላችሁ።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በፍለጋ ሥራው ላይ የሚኖረን አቀራረብ

ከልብ የመነጨ ወዳጃዊ ስሜት ማሳየት እንዲሁም ጉዳዩን በቀጥታ መናገር የሰዎችን ጥርጣሬ ለማስወገድ ይረዳል። በውይይታችን መጀመሪያ ላይ በቋንቋው የተዘጋጁ ጽሑፎችን ማሳየት አብዛኛውን ጊዜ ጠቃሚ ነው።

ሰላምታ ከተለዋወጣችሁ በኋላ እንዲህ ማለት ትችላላችሁ፦ “መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ተስፋ ለማካፈል የ․․․․․ ቋንቋ ተናጋሪዎችን እየፈለግሁ ነበር። ይህን ቋንቋ የሚናገር ሰው ያውቃሉ?”

መስማት የተሳናቸው ሰዎችን በመፈለጉ ሥራ ላይ ስትሰማሩ እንዲህ ማለት ትችላላችሁ፦ “ጤና ይስጥልኝ። [በአካባቢያችሁ የተለመደ ከሆነ በእጅ ሊያዝ የሚችል የቪዲዮ ማጫወቻ በመጠቀም በዲቪዲ ከተዘጋጀው የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቂት ቁጥሮች ሲነበቡ ማሳየት ትችላላችሁ። ከዚያም ጥቅሱ በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ ከተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰደ እንደሆነ መግለጽ ትችላላችሁ።] መስማት የተሳናቸው ሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማርካት ሲባል መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ በርካታ ቪዲዮዎች ይገኛሉ፤ ፍላጎት ያለው ሰው እነዚህን ቪዲዮዎች በነፃ ማግኘት ይችላል። እርስዎ የመስማት ችግር ያለበት በምልክት ቋንቋ የሚጠቀም ሰው ያውቃሉ?” የቤቱ ባለቤት ሰው ሊጠቁማችሁ ካልቻለ በሥራ ቦታው፣ በትምህርት ቤቱ ወይም በሚኖርበት አካባቢ አሊያም በሌሎች ቦታዎች መስማት የተሳናቸው ሰዎችን አግኝቶ ያውቅ እንደሆነ ጠይቁት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ