ሕሊናህን ጠብቅ
1. በ2013 የአገልግሎት ዓመት የሚካሄደው የልዩ ስብሰባ ቀን ጭብጥ ምንድን ነው? ይህ ስብሰባ የተዘጋጀበት ዓላማስ ምንድን ነው?
1 ከሕሊናችን ጋር የሚጋጩ ነገሮችን እንድናደርግ የሚገፋፉ ሁኔታዎች በየዕለቱ ያጋጥሙናል። በመሆኑም በ2013 የአገልግሎት ዓመት የሚካሄደው የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም “ሕሊናህን ጠብቅ” የሚል ጭብጥ ያለው መሆኑ የተገባ ነው። (1 ጢሞ. 1:19) ይህ ስብሰባ የተዘጋጀው ሁላችንም ፈጣሪያችን የሰጠንን ውድ ስጦታ ማለትም ሕሊናችንን ስለምንጠቀምበት መንገድ ትኩረት ሰጥተን እንድናስብ ለመርዳት ነው።
2. በስብሰባው ላይ ለየትኞቹ አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?
2 በስብሰባው ላይ የሚብራሩት ነጥቦች፦ የልዩ ስብሰባው ሕሊናን በተመለከተ ለሚነሱ ለሚከተሉት ሰባት ዋና ዋና ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፦
• ለሕሊና አደገኛ የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?
• ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?
• ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?
• አስተሳሰባችንም ሆነ ድርጊታችን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ መሆኑ ስለ እኛ ምን ያሳያል?
• ለሕሊና በተተዉ ጉዳዮች ረገድ የሌሎችን ሕሊና ከማቁሰል መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?
• ወጣቶች፣ አቋማችሁን እንድታላሉ የሚደረግባችሁን ጫና ችላችሁ ማሳለፍ የምትችሉት እንዴት ነው?
• በመንፈስ የሚመራ ሕሊናቸውን የሚከተሉ ሰዎች ምን በረከቶች ያገኛሉ?
3. ከስብሰባው ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
3 በይሖዋ እርዳታ ሰይጣን ሕሊናችንን ለማቆሸሽ የሚያደርጋቸውን ጥረቶች መቋቋም እንችላለን። አፍቃሪው የሰማዩ አባታችን፣ በቃሉና በድርጅቱ በኩል “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” በማለት እየመራን ነው። (ኢሳ. 30:21) ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን አመራር ከሚሰጥባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ይህ ስብሰባ ነው። በመሆኑም ከፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንድትሆኑ ከወዲሁ ዝግጅት አድርጉ። ስብሰባው ሲካሄድ በትኩረት አዳምጡ፤ እንዲሁም ከስብሰባው ያገኛችሁትን ትምህርት በግለሰብ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ስለምትችሉበት መንገድ አስቡ። በቤተሰብ አንድ ላይ ሆናችሁ ስለ ስብሰባው ተወያዩ። ከስብሰባው የምናገኘውን ትምህርት ተግባራዊ ማድረጋችን “ጥሩ ሕሊና” ይዘን ለመቀጠል የሚያስችል ጥንካሬ እንድናገኝና የሰይጣን ዓለም በሚያቀርባቸው ጊዜያዊ ደስታ በሚያስገኙ ነገሮች ተታልለን ከመንገድ ስተን እንዳንወጣ ይረዳናል።—1 ጴጥ. 3:16