ነቢያትን አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው—አሞጽ
1. የአሞጽ ምሳሌ ሊያበረታታን የሚችለው እንዴት ነው?
1 በአስተዳደግህ ወይም በትምህርት ደረጃህ ምክንያት ለመስበክ ብቃት እንደሌለህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ የአሞጽ ምሳሌ ሊያበረታታህ ይችላል። አሞጽ የበጎች እረኛና ወቅቶችን ጠብቆ በእርሻ ላይ የሚሠራ የጉልበት ሠራተኛ ነበር፤ ያም ሆኖ ይሖዋ አንድ አስፈላጊ መልእክት እንዲያውጅ ኃላፊነት ሰጠው። (አሞጽ 1:1፤ 7:14, 15) ይሖዋ ዛሬም ቢሆን ትሑት ሰዎችን ይጠቀማል። (1 ቆሮ. 1:27-29) ከነቢዩ አሞጽ ለአገልግሎታችን የሚጠቅሙን ምን ተጨማሪ ትምህርቶችን እናገኛለን?
2. በአገልግሎት ላይ ተቃውሞ ቢያጋጥመንም እንኳ በአቋማችን መጽናት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ተቃውሞ ሲያጋጥም በአቋም መጽናት፦ አሥሩን ነገዶች ባቀፈው ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ውስጥ የጥጃ አምልኮ ካህን የነበረው አሜስያስ አሞጽ ትንቢት ሲናገር በሰማ ጊዜ በቁጣ ተናግሮት ነበር፤ ‘ሂድ ወደ አገርህ! አትበጥብጠን! እኛ የራሳችን ሃይማኖት አለን’ ያለው ያህል ነበር። (አሞጽ 7:12, 13) አሜስያስ የአሞጽን ሥራ ለማስቆም ንጉሥ ኢዮርብዓም ፊት በቀረበበት ጊዜ የነቢዩን ቃላት ለማጣመም ሞክሯል። (አሞጽ 7:7-11) አሞጽ ግን በዚህ አልተደናገጠም። ዛሬም ቢሆን አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ስደት ለማድረስ የፖለቲካ መሪዎችን ድጋፍ ለማግኘት ይሞክራሉ። ያም ሆኖ በእኛ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ሁሉ እንደሚከሽፍ ይሖዋ ማረጋገጫ ሰጥቷል።—ኢሳ. 54:17
3. የምናውጀው መልእክት ምን ሁለት ገጽታ አለው?
3 የአምላክን ፍርድና ወደፊት ያዘጋጀውን በረከት ማወጅ፦ አሞጽ በአሥሩ የእስራኤል ነገዶች ላይ ስለሚመጣው ፍርድ ትንቢት የተናገረ ቢሆንም በስሙ የተጠራውን መጽሐፍ የደመደመው ይሖዋ ሕዝቡን መልሶ እንደሚያቋቁምና የተትረፈረፈ በረከት እንደሚሰጣቸው የገባውን ቃል በመግለጽ ነው። (አሞጽ 9:13-15) እኛም ብንሆን ስለ አምላክ “የፍርድ ቀን” እናውጃለን፤ ይህ ግን “የመንግሥቱ ምሥራች” ከሚያካትታቸው መልእክቶች አንዱ ብቻ ነው። (2 ጴጥ. 3:7፤ ማቴ. 24:14) ይሖዋ ክፉዎችን በአርማጌዶን ማጥፋቱ ምድርን ገነት ለማድረግ መንገድ ይጠርጋል።—መዝ. 37:34
4. የይሖዋን ፈቃድ መፈጸም እንችላለን ብለን እንድንተማመን የሚያደርገን ምንድን ነው?
4 በርካታ ተቃዋሚዎች ባሉበት ዓለም ውስጥ የመንግሥቱን መልእክት መስበክ ራሳችንን ስንወስን ለገባነው ቃል ያለንን ታማኝነት እንዲሁም የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ያለንን ቁርጠኝነት እንደሚፈትን ግልጽ ነው። (ዮሐ. 15:19) ያም ሆኖ ይሖዋ ለአሞጽ እንዳደረገው ሁሉ ፈቃዱን ለመፈጸም ብቁ እንደሚያደርገን እርግጠኞች ነን።—2 ቆሮ. 3:5