የጥያቄ ሣጥን
◼ አንዲት አስፋፊ በር ላይ እንደቆመች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመራበት ጊዜ አንድ ወንድም አብሯት ከተገኘ ራሷን መሸፈን ይኖርባታል?
አንዲት አስፋፊ በቋሚነት የሚደረግ መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመራበት ጊዜ አንድ ወንድም አብሯት ከተገኘ ራሷን መሸፈን ይኖርባታል። (1 ቆሮ. 11:3-10) የሐምሌ 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ በገጽ 27 ላይ ሁኔታውን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ በአስጠኚው የሚመራ ቀደም ሲል ፕሮግራም የተያዘለት የትምህርት ክፍለ ጊዜ ነው። በዚህ መሠረት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጉባኤ ስብሰባ ክፍል እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። አንድ የተጠመቀ ምሥክር ባለበት አንዲት እህት እንዲህ ያለ ጥናት የምትመራ ከሆነ ራስዋን መሸፈኗ ተገቢ ነው።” ይኸው መመሪያ ካልተጠመቀ ወንድ አስፋፊ ጋር በምታስጠናበት ጊዜም ይሠራል። ጥናቱ የሚደረገው ቤት ውስጥም ይሁን በር ላይ አሊያም በሌላ ቦታ እህት ራሷን መሸፈኗ አስፈላጊ ነው።
በሌላ በኩል ግን በር ላይ የሚደረገው ውይይት ወደ ጥናት ደረጃ ካልተሸጋገረ፣ አስፋፊዋ ከአንድ ወንድም ጋር ብትሆንም እንኳ ራሷን መሸፈን አያስፈልጋትም፤ ይህች እህት ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርገው ጥናቱ እንዴት እንደሚከናወን ለማሳየት አሊያም በማስጠኛ ጽሑፎቻችን ላይ ተመሥርታ ለመወያየት ቢሆንም እንኳ ራሷን መሸፈን አይጠበቅባትም። በር ላይ እንደቆምን የምናወያየውን ሰው ወደ ጥናት የምናሸጋግረው ቀስ በቀስ ማለትም ተደጋጋሚ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ስለሆነ አንዲት እህት ራሷን መሸፈን የሚያስፈልጋት መቼ እንደሆነ በምንወስንበት ጊዜ ሁኔታዎቹን ግምት ውስጥ ማስገባትና ምክንያታዊ መሆን ያስፈልገናል።