መንግሥቱን በማስታወቅ ያሳለፍነው የመቶ ዓመት ታሪክ
1. ከመቶ ዓመት ገደማ በፊት የይሖዋ ሕዝቦች ምን እንዲያደርጉ ተበረታተው ነበር?
1 “እነሆ ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው! እናንተ ደግሞ የእሱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ።” ወንድም ራዘርፎርድ ከመቶ ዓመት ገደማ በፊት ያቀረበው ይህ ስሜት ቀስቃሽ ንግግር የይሖዋ ሕዝቦች የመንግሥቱን መልእክት በስፋት እንዲያውጁ አበረታቷቸዋል። ደግሞም ይህን ማበረታቻ ተግባራዊ አድርገናል! እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም የመንግሥቱን ምሥራች ‘ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ’ ሰብከናል። (ቆላ. 1:23) ያለፈው መቶ ዓመት ታሪካችንን እስቲ መለስ ብለን እንቃኝ፤ የአምላክን መንግሥት በማስታወቅ ረገድ ምን አከናውነናል? መንግሥቱ የተወለደበት 100ኛ ዓመት በተቃረበበት በዚህ ወቅት መንግሥቱን ማስታወቃችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
2. ጽሑፎቻችን የአምላክን መንግሥት የሚያስታውቁት እንዴት ነው?
2 ታሪካችንን መቃኘት፦ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ጽሑፎቻችን የአምላክን መንግሥት ሲያስታውቁ ቆይተዋል። በዋነኝነት የምንጠቀምበት መጽሔት ከ1939 ጀምሮ የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል። ይህ መጽሔት በአብዛኛው የሚናገረው ስለ መንግሥቱና ይህ መንግሥት ወደፊት ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ነው። ንቁ! መጽሔትም ለሰው ዘር ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ሁለት መጽሔቶች፣ በሚተረጎሙባቸው ቋንቋዎች ብዛትም ሆነ በስርጭታቸው በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌላቸው መሆኑ በእርግጥም የተገባ ነው።—ራእይ 14:6
3. መንግሥቱን ለማስታወቅ ከተጠቀምንባቸው መንገዶች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
3 የይሖዋ ሕዝቦች መንግሥቱን ለማስታወቅ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት የድምፅ ማጉያ መሣሪያ የተገጠመላቸው መኪኖችን፣ የሬዲዮ ማሰራጫዎችን እና ተንቀሳቃሽ የሸክላ ማጫወቻዎችን እንጠቀም ነበር። በአንጻራዊ ሁኔታ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር አነስተኛ በነበረበት በዚያ ወቅት እነዚህ ዘዴዎች ምሥራቹን በአንድ ጊዜ ለብዙ ሰዎች ለማድረስ አስችለውናል። (መዝ. 19:4) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በjw.org ላይ ልዩ ልዩ መረጃዎችን ማውጣት ጀምረናል፤ ይህም ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ለሚኖሩት ጨምሮ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ስለ መንግሥቱ ለማወጅ ረድቶናል።
4. በየትኞቹ ልዩ የስብከት ዘዴዎች ተጠቅመናል?
4 በተጨማሪም የይሖዋ ሕዝቦች የመንግሥቱን መልእክት ለማድረስ ልዩ የስብከት ዘዴዎችን ተጠቅመዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ከቤት ወደ ቤት ከምናከናውነው አገልግሎት በተጨማሪ በመናፈሻዎች፣ በመኪና ማቆሚያዎችና በንግድ ቦታዎች ለመስበክ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል። በቅርቡ ደግሞ በዓለም ዙሪያ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ልዩ የአደባባይ ምሥክርነት መስጠት ጀምረናል። በተጨማሪም ብዙ ጉባኤዎች በክልላቸው ውስጥ ብዙ ሰው በሚተላለፍባቸው አካባቢዎች የጽሑፍ ጋሪዎችንና ጠረጴዛዎችን በመጠቀም የአደባባይ ምሥክርነት እየሰጡ ነው። እርግጥ ነው፣ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል የመንግሥቱን ምሥራች የምንሰብክበት ዋነኛ ዘዴ እንደሆነ ይቀጥላል።—ሥራ 20:20
5. በአዲሱ የአገልግሎት ዓመት ብዙዎቻችን ምን አጋጣሚዎች አሉን?
5 የወደፊቱን ጊዜ መጠባበቅ፦ አዲሱን የአገልግሎት ዓመት በምንጀምርበት በመስከረም ወር ላይ ብዙዎች የዘወትር አቅኚዎች ሆነው ማገልገል ይጀምራሉ። አንተስ በዚህ አገልግሎት መስክ መካፈል ትችል ይሆን? ይህን ማድረግ የማትችል ከሆነ ደግሞ አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትችላለህ? በአቅኚነት አገልግሎት መካፈል ባትችል እንኳ መንግሥቱን በማስታወቁ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ስትል የምትከፍለውን ማንኛውንም መሥዋዕትነት ይሖዋ እንደሚባርክልህ እርግጠኛ ሁን።—ሚል. 3:10
6. ጥቅምት ልዩ ወር የሆነው ለምንድን ነው?
6 ጥቅምት 2014 የአምላክ መንግሥት ከተወለደ 100 ዓመት ይሞላዋል። በዚያ ወር ለሕዝብ የሚሰራጨው የመጠበቂያ ግንብ እትም በአምላክ መንግሥት ላይ ያተኮረ ይሆናል፤ ይህ ምንኛ የተገባ ነው! ታዲያ ይህን እትም ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ የተቻለህን ሁሉ ጥረት ማድረግ አይገባህም? የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት ስንጠባበቅ ሁላችንም ሰሚ ጆሮ ላላቸው ሁሉ ‘የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጃችንን’ እንቀጥል።—ሥራ 8:12