የአደባባይ ምሥክርነት የምንሰጥበት አዲስና አስደሳች ዘዴ
1. በክልላቸው ውስጥ እግረኛ የሚበዛባቸው ቦታዎች ያሏቸው ጉባኤዎች ምን እንዲያደርጉ ተበረታተዋል?
1 እግረኛ የሚበዛባቸው ቦታዎች ያሏቸው ጉባኤዎች ጠረጴዛዎችን ወይም ተንቀሳቃሽ የጽሑፍ መደርደሪያዎችን በመጠቀም የአደባባይ ምሥክርነት እንዲጀምሩ ተበረታትተው ነበር። ጉባኤው የሚጠቀመው በተንቀሳቃሽ የጽሑፍ መደርደሪያ ከሆነ ቢያንስ አንድ አስፋፊ ከመደርደሪያው አጠገብ መቆም ወይም መቀመጥ ይኖርበታል። ጽሑፎቹ የሚደረደሩት ጠረጴዛ ላይ ከሆነ ግን ከጠረጴዛው አጠገብ የግድ ሁለት አስፋፊዎች ሊኖሩ ይገባል። በጽሑፍ መደርደሪያው አጠገብ የሚገኙት አስፋፊዎች ፊታቸው ላይ ፈገግታ ሊታይና በቀላሉ የሚቀረቡ ሊሆኑ ይገባል፤ በአጠቃላይ ሰዎች ወደ እነሱ እንዲመጡ የሚጋብዝ ፊት ሊኖራቸው ይገባል። አንድ ሰው ወደ ጽሑፍ መደርደሪያው ሲመጣ ከአስፋፊዎቹ አንዱ ግለሰቡን ለማናገር ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፤ ምናልባትም “መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ማወቅ ይፈልጋሉ?” ብሎ በመጠየቅ ውይይት መጀመር ይችላል። የቀሩት ደግሞ (አንድ ወይም ሁለት ሊሆኑ ይችላሉ) ከጽሑፍ መደርደሪያው ብዙም ሳይርቁ በአካባቢው ካሉ ሰዎች ጋር መደበኛ ባልሆነ መንገድ ውይይት መጀመር ይችላሉ።
2. የጽሑፍ መደርደሪያዎችን ተጠቅሞ የአደባባይ ምሥክርነት መስጠት ያለውን ጥቅም የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
2 በዚህ ዘዴ አማካኝነት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማግኘት ተችሏል። አንዲት የኮሌጅ ተማሪ በይሖዋ ምሥክሮች ዙሪያ ጥናት በማካሄድ አንድ ጽሑፍ ማዘጋጀት ፈለገች፤ ይሁንና የመንግሥት አዳራሽ ማግኘት አልቻለችም። በቀጣዩ ሳምንት በምትማርበት ኮሌጅ ውስጥ ጽሑፎች የተደረደሩበት ጠረጴዛ አየች። ይህች ሴት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የተጠመቀች አስፋፊ ሆናለች፤ እንዲሁም እሷ ራሷ በዚህ የምሥክርነት ዘርፍ እየተካፈለች ነው።
3. አንዳንዶች ስለዚህ የአደባባይ ምሥክርነት ዘዴ ምን ይሰማቸዋል?
3 በዚህ የምሥክርነት ዘርፍ የምትካፈል አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንዶች ወደ ጽሑፍ መደርደሪያው የሚመጡት አዲስ የወጡ መጽሔቶችን ለመውሰድ ነው። ሌሎች ደግሞ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ፈጽሞ ሰምተው አያውቁም። ይህ የምሥክርነት ዘዴ እውነትን ለብዙዎች ለማዳረስ እንደሚያስችል ይሰማኛል።” ሌላ እህት ደግሞ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ይህ የምሥክርነት ዘዴ አዲስና አስደሳች ነው፤ ምክንያቱም ሰዎች ወደ እናንተ የሚመጡት በራሳቸው ፍላጎት ነው፤ ይህም ቢያንስ የተወሰነ ፍላጎት እንዳላቸው ይጠቁማል።”
4. የጽሑፍ መደርደሪያውን በተመሳሳይ ጊዜና በተመሳሳይ ቦታ ማስቀመጡ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
4 የጽሑፍ መደርደሪያውን በተመሳሳይ ቀናት፣ በተመሳሳይ ሰዓትና በተመሳሳይ ቦታ ማስቀመጡ ጥቅም አለው። በዚያ አካባቢ የሚተላለፉ ሰዎች የጽሑፍ መደርደሪያውን በተደጋጋሚ ስለሚያዩት ውሎ አድሮ አስፋፊዎቹን ቀርበው ለማነጋገር እና ጽሑፍ ለመውሰድ ሊደፋፈሩ ይችላሉ። የእናንተስ ጉባኤ በአደባባይ ምሥክርነት መካፈል ጀምሯል? ከሆነ ‘የአምላክን መንግሥት በየቦታው ለማወጅ’ በሚያስችለው በዚህ አስደሳችና ውጤታማ የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል ትችል ይሆናል።—ሉቃስ 9:60