በአገልግሎት የምታሳልፉትን ጊዜ በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት
የይሖዋ ምሥክሮች በ2014 የአገልግሎት ዓመት 1,945,487,604 ሰዓት በአገልግሎት አሳልፈዋል፤ ይህ ደግሞ በይሖዋ አገልግሎት ለመጠመድ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው። (መዝ. 110:3፤ 1 ቆሮ. 15:58) “የቀረው ጊዜ አጭር” ከመሆኑ አንጻር በአገልግሎት የምናሳልፈውን ውድ ጊዜ የበለጠ ብዙ ሰዎችን ለማነጋገር ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?—1 ቆሮ. 7:29
በአገልግሎት የምናሳልፈውን ጊዜ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ከፈለግን እንደ ሁኔታው ለውጥ ማድረግ ይኖርብናል። ለምሳሌ አገልግሎት ወጥተን ምንም ሰው ሳናነጋግር አንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ጊዜ ያልፍብናል? ከሆነ ሰዎችን አግኝተን ለማነጋገር ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብን ይሆን? እርግጥ ነው ሁኔታዎች ከቦታ ቦታ ሊለያዩ ይችላሉ። ያም ቢሆን ቀጥሎ የቀረቡት ሐሳቦች ‘አየር ከመምታት’ ይልቅ ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት ይረዱናል።—1 ቆሮ. 9:26
ከቤት ወደ ቤት ማገልገል፦ ለብዙ አሥርተ ዓመታት አስፋፊዎች የዕለቱን አገልግሎታቸውን ከቤት ወደ ቤት በመስበክ የመጀመር ልማድ አዳብረዋል። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ቀን ቀን ሥራ ስለሚውሉ ከቤት ወደ ቤት የምናደርገውን አገልግሎት ከሥራ መልስ ባለው ጊዜ ወይም አመሻሹ ላይ ማድረግ እንችል ይሆን? ምክንያቱም ይህ ጊዜ ሰዎች ቤታቸው የሚገኙበትና ዘና የሚሉበት ወቅት ነው። የቀኑን ክፍለ ጊዜ በመንገድ ላይ ወይም በንግድ አካባቢዎች ለመመሥከር ብንጠቀምበት የተሻለ ውጤት ልናገኝ እንችላለን።
የአደባባይ ምሥክርነት፦ በጠረጴዛዎችና በተንቀሳቃሽ የጽሑፍ መደርደሪያዎች አማካኝነት የሚሰጠው ምሥክርነት መካሄድ ያለበት በጉባኤው ክልል ውስጥ በሚገኙ እግረኛ በሚበዛባቸው ቦታዎች ነው። (የሐምሌ 2013 የመንግሥት አገልግሎታችንን ገጽ 5 ተመልከት።) ለአደባባይ ምሥክርነት በተመረጠው ቦታ የሚተላለፉ ሰዎች ቁጥር ከቀነሰ የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ የጽሑፍ መደርደሪያው ወይም ጠረጴዛው ከፍተኛ የእግረኛ ፍሰት ባለበት ሌላ ቦታ እንዲቀመጥ ሊወስን ይችላል።
ተመላልሶ መጠየቅና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች፦ ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግበትንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምንመራበትን ሰዓት፣ በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ለመካፈል እምብዛም አመቺ ባልሆነበት ሰዓት ላይ ማድረግ እንችል ይሆን? ለምሳሌ ከቤት ወደ ቤት ለማገልገል አመቺ የሆነው ቅዳሜ ጠዋት ከሆነ ጥናታችንን ከሰዓት በኋላ ወይም አመሻሹ ላይ ማድረግ እንችላለን። ተመላልሶ መጠየቅ በምናደርግበት ጊዜ ደግሞ በአንድ መኪና ብዙ ሆኖ ከመሄድ ይልቅ ብዙ ሰዎችን ማነጋገር እንዲቻል አስፋፊዎች በትናንሽ ቡድኖች ተከፋፍለው መሄድ ይችሉ ይሆን?
በአገልግሎት ላይ እስከሆንን ድረስ ያሳለፍነውን ሰዓት በሙሉ ሪፖርት ማድረግ የምንችል ቢሆንም ይበልጥ ደስተኛ የምንሆነው በአገልግሎታችን ውጤታማ ስንሆን ነው። በመሆኑም በአንድ ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል የመረጣችሁት ሰዓት ያን ያህል ውጤታማ ካልሆነ በሌላ የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ሞክሩ። እንዲሁም በአገልግሎት የምታሳልፉትን ጊዜ በተሻለ መንገድ በመጠቀም ረገድ “የመከሩ ሥራ ኃላፊ” የሆነው ይሖዋ እንዲመራችሁ ጸልዩ!—ማቴ. 9:38