በድምፅ የተቀረጹ ጽሑፎችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
1. በጽሑፍ ከሚዘጋጁት ነገሮች በተጨማሪ በየትኛው ዝግጅት መጠቀም እንችላለን?
1 ብዙ ሰዎች jw.org በተባለው ድረ ገጽ ላይ የሚወጣውን ደስ የሚያሰኝና ትክክል የሆነውን የእውነት ቃል ማንበብ ያስደስታቸዋል። (መክ. 12:10) ይሁንና በድምፅ የተቀረጹ ጽሑፎችንስ አዳምጣችሁ ታውቃላችሁ? እንዲህ በማድረግ በድረ ገጻችን ላይ የሚገኙትን የተለያዩ መረጃዎች መስማት ትችላላችሁ። በድምፅ የተቀረጹ ጽሑፎች ሊጠቅሙን የሚችሉት እንዴት ነው?
2. የግል ወይም የቤተሰብ ጥናት ስናደርግ በድምፅ የተቀረጹ ነገሮችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
2 የግል ወይም የቤተሰብ ጥናት ስናደርግ፦ ስንጓዝ ወይም ደግሞ የዕለት ተዕለት ተግባራችንን ስናከናውን በድምፅ የተቀረጹ የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የመጽሔቶች ወይም የሌሎች ጽሑፎች ቅጂዎችን ማዳመጣችን ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት ያስችለናል። (ኤፌ. 5:15, 16) የቤተሰብ አምልኮ በምናደርግበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ ጽሑፋችንን ይዘን በመከታተል በድምፅ የተቀረጸውን ንባብ ማዳመጥ እንችላለን። በግል ጥናታችን ወቅት በድምፅ የተቀረጹ ጽሑፎችን ተጠቅመን የንባብ ችሎታችንን ማሻሻል ወይም አዲስ ቋንቋ መማር እንችላለን።
3. በድምፅ የተቀረጹ ጽሑፎች በክልላችን ውስጥ የሚገኙ የትኞቹን ሰዎች ሊጠቅሙ ይችላሉ?
3 በአገልግሎት ላይ ስንሆን፦ ጽሑፎቻችንን ለማንበብ ጊዜ እንደሌላቸው የሚሰማቸው በክልላችን ውስጥ የምናገኛቸው ሰዎች በድምፅ የተቀረጹ ጽሑፎችን ለመስማት ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም ደግሞ በአገልግሎት ያገኘናቸው ሰዎች ከእኛ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ ሊሆኑና የመንግሥቱን መልእክት ‘በአገራቸው ቋንቋ’ ቢሰሙ ጥሩ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። (ሥራ 2:6-8) በአንዳንድ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ማዳመጥ ባሕላቸው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሞብ በሚባለው ባሕል ሰዎች ታሪክን ለወጣቱ ትውልድ የሚያስተላልፉት በቃል ሲሆን ሕዝቡ በጆሮው የሰማውን መረጃ የማስታወስ ችሎታ አለው። በብዙ የአፍሪካ ባሕሎች ሰዎች ትምህርት የሚቀስሙት ተረት በመስማት ነው።
4. በክልላችን ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች ልንጠይቅ ይገባል?
4 በክልላችሁ ውስጥ በድምፅ ከተቀረጹት ነገሮች አንዱን ለምታነጋግሩት ሰው ማሰማታችሁ ሊጠቅመው ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ? ለአንድ ሰው በድምፅ የተቀረጸ ጽሑፍ በኢሜይል ብንልክለት ይጠቀም ይሆን? ፍላጎት ላሳየ አንድ ሰው በድምፅ የተቀረጸ አንድ ጽሑፍ በሲዲ ላይ አውርደን ምናልባትም ከታተመው የጽሑፍ ቅጂ ጋር ልንሰጠው እንችላለን? በአገልግሎት ላይ በዚህ መንገድ አንድን ሙሉ መጽሐፍ፣ ብሮሹር፣ መጽሔት ወይም ትራክት ለአንድ ሰው ከሰጠን እንደተበረከተ ጽሑፍ መመዝገብ እንችላለን። በድምፅ የተቀረጹ ጽሑፎችን የግል ጥናት ስናደርግም ሆነ የመንግሥቱን እውነት ስንዘራ ልንጠቀምባቸው እንችላለን።—1 ቆሮ. 3:6