ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ማርቆስ 9-10
እምነት የሚያጠናክር ራእይ
ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በተለወጠበት ወቅት በሰማይ ያለው አባቱ በእሱ ደስ እንደሚሰኝ ሲናገር መስማቱ እምነቱን በእጅጉ አጠናክሮለት እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ይህን መስማቱ ከፊቱ የሚጠብቀውን መከራ በድፍረት ለመጋፈጥ የሚያስችል ጥንካሬ እንደሰጠው ምንም ጥርጥር የለውም። ራእዩ በጴጥሮስ፣ በያዕቆብና በዮሐንስም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ኢየሱስ በእርግጥ መሲሕ እንደሆነና እሱን መስማታቸው ተገቢ እንደሆነ አረጋግጦላቸዋል። ጴጥሮስ ከ32 ዓመት በኋላ እንኳ በዚያ ወቅት የተከሰተውን ነገር እንዲሁም ይህ ሁኔታ ‘በትንቢታዊው ቃል’ ላይ ያለውን እምነት ምን ያህል እንዳጠናከረለት አስታውሶ ተናግሯል።—2ጴጥ 1:16-19
እኛ ይህን አስደናቂ ራእይ በገዛ ዓይናችን ባናይም እንኳ ፍጻሜውን ሲያገኝ እየተመለከትን ነው። ኢየሱስ ኃያል ንጉሥ ሆኖ እየገዛ ነው። በቅርቡ ደግሞ ‘ድሉን በማጠናቀቅ’ ጽድቅ ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም እንድንገባ ያደርገናል።—ራእይ 6:2
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ ማየትህ እምነትህን ያጠናከረልህ እንዴት ነው?