ክርስቲያናዊ ሕይወት
የሐሰት ወሬ እንዳታሰራጩ ተጠንቀቁ
በዛሬው ጊዜ በጽሑፎች፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት መረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሊሰራጭ ይችላል። “የእውነት አምላክ” የሆነውን ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ሳያውቁትም ቢሆን የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት አይፈልጉም። (መዝ 31:5፤ ዘፀ 23:1) የሐሰት ወሬ ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። አንድ መረጃ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ፦
‘ምንጩ አስተማማኝ ነው?’ ወሬውን የነገረህ ሰው የተሟላ መረጃ ላይኖረው ይችላል። መረጃ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ሲተላለፍ መቀየሩ አይቀርም፤ በመሆኑም የመረጃውን ምንጭ በትክክል ካላወቅክ ጥንቃቄ አድርግ። በተለይ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች እንደ ተአማኒ የመረጃ ምንጭ ተደርገው ስለሚታዩ ያልተጣራ መረጃ እንዳያስተላልፉ ይበልጥ መጠንቀቅ አለባቸው
‘መረጃው የሌሎችን ስም የሚያጠፋ ነው?’ ወሬው የአንድን ሰው ወይም ቡድን መልካም ስም የሚያጎድፍ ከሆነ ወሬውን ማስተላለፍ አይኖርብንም።—ምሳሌ 18:8፤ ፊልጵ 4:8
‘ወሬው ለማመን የሚከብድ ነው?’ የሚያስደምሙ ታሪኮችን ወይም ተሞክሮዎችን ስትሰማ ጥንቃቄ አድርግ
ሐሜትን ማስወገድ የምችለው እንዴት ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
በምሳሌ 12:18 መሠረት ቃላት ምን ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ?
ፊልጵስዩስ 2:4 ስለ ሌሎች ሰዎች ማውራትን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንድንይዝ የሚረዳን እንዴት ነው?
ስለ አንድ ሰው አሽሙር ወይም ወደ መጥፎ ነገር ማውራት ከተጀመረ ምን ማድረግ አለብን?
ስለ ሌሎች ማውራት ከመጀመራችን በፊት ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል?