የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w20 መጋቢት ገጽ 18-23
  • ለመናገር ትክክለኛው ጊዜ መቼ ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለመናገር ትክክለኛው ጊዜ መቼ ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መናገር ያለብን መቼ ነው?
  • ዝም ማለት ያለብን መቼ ነው?
  • ይሖዋ ስለምንናገረው ነገር ምን ይሰማዋል?
  • አስተዋይነት የተንጸባረቀበት እርምጃ ወስዳለች
    በእምነታቸው ምሰሏቸው
  • አስተዋይነት የተንጸባረቀበት እርምጃ ወስዳለች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • አቢግያና ዳዊት
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
  • አንዲት ልባም ሴት ጥፋት እንዳይደርስ ተከላከለች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
w20 መጋቢት ገጽ 18-23

የጥናት ርዕስ 12

ለመናገር ትክክለኛው ጊዜ መቼ ነው?

“ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው።”—መክ. 3:7

መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን

ማስተዋወቂያa

1. መክብብ 3:7 ምን ያስተምረናል?

አንዳንዶቻችን ብዙ ማውራት እንወድ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ዝም ማለትን ይመርጣሉ። ይህ ርዕስ የተመሠረተበት ጥቅስ እንደሚያሳየው ለመናገርም ሆነ ዝም ለማለት ጊዜ አለው። (መክብብ 3:7⁠ን አንብብ።) አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ይበልጥ ቢያወሩ ደስ ይለን ይሆናል። ሌሎች ወንድሞቻችን ደግሞ ብዙ ባያወሩ እንመርጥ ይሆናል።

2. መቼና እንዴት መናገር እንዳለብን መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው ማን ነው?

2 የመናገር ችሎታ ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ነው። (ዘፀ. 4:10, 11፤ ራእይ 4:11) ይሖዋ ይህን ስጦታ በአግባቡ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ በቃሉ አማካኝነት ያስተምረናል። መቼ መናገር፣ መቼ ደግሞ ዝም ማለት እንዳለብን ለማወቅ የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም ስለምንናገረው ነገር ይሖዋ ምን እንደሚሰማው እናያለን። በመጀመሪያ ግን መናገር ያለብን መቼ እንደሆነ እንመልከት።

መናገር ያለብን መቼ ነው?

3. በሮም 10:14 መሠረት ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ መናገር ያለብን መቼ ነው?

3 ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ ለመናገር ምንጊዜም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። (ማቴ. 24:14፤ ሮም 10:14⁠ን አንብብ።) እንዲህ በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት አንዱ ምክንያት ስለ አባቱ የሚገልጸውን እውነት ለሰዎች ለማስተማር ነው። (ዮሐ. 18:37) ይሁንና የምንናገርበት መንገድም ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ማስታወስ አለብን። ስለ ይሖዋ የምንናገረው “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” ሊሆን ይገባል፤ እንዲሁም ለግለሰቡ ስሜትና እምነት አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 3:15) እንዲህ ካደረግን ንግግራችን ወሬ ከመሆን ባለፈ ለግለሰቡ ትምህርት የሚሰጥና ልቡን የሚነካ ይሆናል።

መናገር ያለብን መቼ ነው?

  • ለሰዎች ስለ ይሖዋ ስንናገር ‘የገርነት መንፈስ’ ማሳየትና እምነታቸውን ‘በጥልቅ ማክበር’ አለብን (አንቀጽ 3)

  • አንድ ሰው የተሳሳተ ጎዳና እየተከተለ እንደሆነ ስናይ

  • ሽማግሌዎች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በትዕግሥትና በጥበብ ምክር ይሰጣሉ

ሁለት እህቶች ልብስ መሸጫ ውስጥ። አንደኛዋ እህት የያዘችው አጭር ቀሚስ ተገቢ ልብስ እንዳልሆነ ሌላኛዋ እህት ስትነግራት።

(አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)b

አንድ ሽማግሌ መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ ለአንድ ወጣት ወንድም ስለ ንጽሕና ምክር ሲሰጠው። የወጣቱ ወንድም ቤት የተዝረከረከ ነው።

(አንቀጽ 4, 9⁠ን ተመልከት)c

4. በምሳሌ 9:9 መሠረት ንግግራችን ሌሎችን ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?

4 ሽማግሌዎች አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ምክር እንደሚያስፈልጋቸው ካስተዋሉ ከመናገር ወደኋላ ሊሉ አይገባም። እርግጥ ነው ግለሰቡ እንዳይሸማቀቅ የሚናገሩበትን ጊዜ በጥበብ መምረጥ ይኖርባቸዋል። ምናልባት ሌሎች ሰዎች በሌሉበት ቢናገሩ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ሽማግሌዎች በሚናገሩበት ጊዜ የሚመክሩትን ሰው ክብር ለመጠበቅ ምንጊዜም ጥረት ያደርጋሉ። ያም ቢሆን ወንድሞች ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ እንዲወስዱ ለመርዳት ሲሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከማካፈል ወደኋላ አይሉም። (ምሳሌ 9:9⁠ን አንብብ።) ታዲያ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በድፍረት መናገራችን ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው? ሁለት ተቃራኒ ምሳሌዎችን እንመልከት፤ ልጆቹን ማረም የነበረበትን አንድ ሰውና ንጉሥ ለመሆን የተቀባን ሰው ፊት ለፊት ማነጋገር የነበረባትን አንዲት ሴት ታሪክ እንመለከታለን።

5. ሊቀ ካህናቱ ኤሊ መናገር ቢኖርበትም ሳይናገር የቀረው መቼ ነው?

5 ሊቀ ካህናቱ ኤሊ በጣም የሚወዳቸው ሁለት ልጆች ነበሩት። ሆኖም ልጆቹ ለይሖዋ ምንም አክብሮት አልነበራቸውም። የኤሊ ልጆች በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ካህን ሆነው የማገልገል ትልቅ ኃላፊነት ነበራቸው። ሆኖም ሥልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመውበታል፤ ለይሖዋ ለሚቀርበው መሥዋዕት ከፍተኛ ንቀት ነበራቸው፤ አልፎ ተርፎም የፆታ ብልግና ይፈጽሙ ነበር። (1 ሳሙ. 2:12-17, 22) በሙሴ ሕግ መሠረት የኤሊ ልጆች ሞት ይገባቸው ነበር፤ ሆኖም ኤሊ መጠነኛ ተግሣጽ ብቻ በመስጠት በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ፈቀደላቸው። (ዘዳ. 21:18-21) ታዲያ ይሖዋ ኤሊ ስላደረገው ነገር ምን ተሰማው? ኤሊን “ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ያከበርከው ለምንድን ነው?” ብሎታል። ይሖዋ እነዚያ ክፉ ልጆች እንዲገደሉ ወሰነ።—1 ሳሙ. 2:29, 34

6. ከኤሊ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 ከኤሊ ታሪክ አስፈላጊ ትምህርት እናገኛለን። አንድ ጓደኛችን ወይም ዘመዳችን የአምላክን ሕግ እንደጣሰ ካወቅን ይህን አስመልክቶ ልናነጋግረው ይገባል። ከዚያም የሚያስፈልገውን እርዳታ ይሖዋ ከሾማቸው ሰዎች እንዲያገኝ ማድረግ አለብን። (ያዕ. 5:14) ከይሖዋ ይልቅ ጓደኞቻችንን ወይም ዘመዶቻችንን በማክበር እንደ ኤሊ መሆን አንፈልግም። እርግጥ እርማት የሚያስፈልገውን ሰው ማነጋገር ድፍረት ይጠይቃል፤ ሆኖም እንዲህ ማድረጉ አያስቆጭም። እስቲ ኤሊ ባደረገው ነገርና አቢጋኤል የተባለች አንዲት እስራኤላዊት ባደረገችው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተዋል ሞክሩ።

አቢጋኤል ተንበርክካ ዳዊትን ስታነጋግረው።

አቢጋኤል ለመናገር ትክክለኛውን ጊዜ በመምረጥ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትታለች (ከአንቀጽ 7-8⁠ን ተመልከት)d

7. አቢጋኤል ዳዊትን ያነጋገረችው ለምንድን ነው?

7 አቢጋኤል ናባል የተባለ ሀብታም ሰው ሚስት ነበረች። ዳዊትና ሰዎቹ ከንጉሥ ሳኦል እየሸሹ በነበረበት ወቅት ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከናባል እረኞች ጋር ቆይተው ነበር፤ በዚያ ወቅት የናባልን በጎች ከዘራፊዎች ይጠብቁለት ነበር። ታዲያ ናባል ለተደረገለት ነገር አመስጋኝ ነበር? በፍጹም። ዳዊት ለእሱና ለሰዎቹ ጥቂት ምግብና ውኃ እንዲሰጣቸው ናባልን በጠየቀው ጊዜ ናባል ተቆጥቶ የስድብ ናዳ አወረደባቸው። (1 ሳሙ. 25:5-8, 10-12, 14) በዚህም ምክንያት ዳዊት በናባል ቤት ያሉትን ወንዶች በሙሉ ለመግደል ተነሳ። (1 ሳሙ. 25:13, 22) እንዲህ ያለውን አስከፊ ሁኔታ ማስቆም የሚቻለው እንዴት ነው? አቢጋኤል መናገር እንዳለባት ስለተገነዘበች ወደ 400ዎቹ የተራቡ፣ የተቆጡና የታጠቁ ሰዎች ሄዳ ዳዊትን አነጋገረችው።

8. ከአቢጋኤል ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

8 አቢጋኤል ዳዊትን ስታገኘው በድፍረት፣ በአክብሮትና አሳማኝ በሆነ መንገድ አነጋገረችው። ችግሩ የተፈጠረው በእሷ ጥፋት ባይሆንም ዳዊትን ይቅርታ ጠየቀችው። የዳዊትን መልካም ባሕርያት በመግለጽ ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርግ ያበረታታችው ሲሆን ይሖዋ እንደሚረዳት ተማምና ነበር። (1 ሳሙ. 25:24, 26, 28, 33, 34) እኛም አንድ ሰው በአደገኛ ጎዳና ላይ እየተጓዘ እንደሆነ ብናይ እንደ አቢጋኤል በድፍረት መናገር አለብን። (መዝ. 141:5) በአክብሮት መናገር ቢኖርብንም ምክሩን አለዝበን አናቀርብም። በፍቅር ተነሳስተን አስፈላጊውን ምክር ስንሰጥ እውነተኛ ጓደኛ መሆናችንን እናሳያለን።—ምሳሌ 27:17

9-10. ሽማግሌዎች ሌሎችን በሚመክሩበት ጊዜ ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል?

9 በተለይ ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ያሉ የተሳሳተ ጎዳና የሚከተሉ አስፋፊዎችን ለማነጋገር ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል። (ገላ. 6:1) ሽማግሌዎች እነሱም ፍጹማን እንዳልሆኑና ምክር የሚያስፈልጋቸው ጊዜ እንደሚኖር በትሕትና ይቀበላሉ። ሆኖም ይህ እውነታ ተግሣጽ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ከመውቀስ ወደኋላ እንዲሉ ሊያደርጋቸው አይገባም። (2 ጢሞ. 4:2፤ ቲቶ 1:9) አንድን ሰው ሲመክሩ ከይሖዋ ያገኙትን የመናገር ችሎታ በመጠቀም ግለሰቡን በጥበብና በትዕግሥት ለማስተማር ጥረት ያደርጋሉ። ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅር አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት ያነሳሳቸዋል። (ምሳሌ 13:24) ሆኖም በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ነገር የይሖዋን መሥፈርቶች በመደገፍ እሱን ማክበራቸውና ጉባኤውን ከጉዳት መጠበቃቸው ነው።—ሥራ 20:28

10 እስካሁን ድረስ መቼ መናገር እንዳለብን ተመልክተናል። ይሁንና ምንም ነገር አለመናገራችን የተሻለ የሚሆንበት ጊዜ አለ። በመሆኑም ዝም ማለት ያለብን መቼ እንደሆነ በሚቀጥሉት አንቀጾች ላይ እንመለከታለን።

ዝም ማለት ያለብን መቼ ነው?

11. ያዕቆብ የትኛውን ምሳሌ ተጠቅሟል? ምሳሌው ተስማሚ ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

11 ንግግራችንን መቆጣጠር ከባድ ሊሆንብን ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመግለጽ ተስማሚ ምሳሌ ተጠቅሟል። እንዲህ ብሏል፦ “በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው ለመላ ሰውነቱ ልጓም ማስገባት የሚችል ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕ. 3:2, 3 ግርጌ) ልጓም በፈረስ አፍና ጭንቅላት ላይ የሚጠለቅ መቆጣጠሪያ ነው። ጋላቢው ልጓሙን በመጎተት ፈረሱን አቅጣጫ ማስቀየር ወይም ማስቆም ይችላል። ጋላቢው ልጓሙን መቆጣጠር ካቃተው ግን ፈረሱ ከቁጥጥር ውጭ በመሆን በራሱም ሆነ በጋላቢው ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። እኛም በተመሳሳይ ንግግራችንን ካልተቆጣጠርን ብዙ ጉዳት ልናደርስ እንችላለን። ልጓማችንን በመጎተት ከመናገር መታቀብ የሚኖርብን በየትኞቹ ጊዜያት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

መናገር የሌለብን መቼ ነው?

  • ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ሥራው እንዴት እንደሚከናወን ለመናገር ስንፈተን

  • በሚስጥር መያዝ ያለባቸውን የጉባኤ ጉዳዮች ስናውቅ

በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አስፋፊዎች ከሌላ ቦታ የመጡን አንድ ባልና ሚስት ከበው ጥያቄ ሲጠይቋቸው።

(አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)e

አንድ ሽማግሌ ስልክ ለማነጋገር ባለቤቱ ካለችበት ክፍል ወጥቶ በሩን ሲዘጋው።

(ከአንቀጽ 13-14⁠ን ተመልከት)f

12. ልጓማችንን በመጎተት ከመናገር መታቀብ የሚኖርብን መቼ ነው?

12 አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት በሚስጥር መያዝ ያለበት መረጃ እንዳላቸው ብናውቅ ምን እናደርጋለን? ለምሳሌ ሥራችን በታገደበት አገር ከሚኖር ወንድም ጋር ብንገናኝ በዚያ አገር ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ በተመለከተ ዝርዝር ነገሮችን እንዲነግረን ለመጠየቅ እንፈተን ይሆን? እንዲህ የምናደርገው በቅን ልቦና ተነሳስተን እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ወንድሞቻችንን እንወዳቸዋለን እንዲሁም ያሉበት ሁኔታ ያሳስበናል። በተጨማሪም ስለ እነሱ ስንጸልይ አንዳንድ ነገሮችን ለይተን መጥቀስ እንፈልግ ይሆናል። ይሁንና በዚህ ወቅት ልጓማችንን በመጎተት ከመናገር መታቀብ ይኖርብናል። ሚስጥራዊ መረጃ ያለው ወንድማችን መረጃውን እንዲነግረን ብንጎተጉተው ለእሱም ሆነ ሚስጥራቸውን እንደሚጠብቅላቸው ለሚተማመኑበት ወንድሞችና እህቶች ፍቅር እንደጎደለን የሚያሳይ ይሆናል። ማናችንም ብንሆን ሥራችን በታገደባቸው አገሮች የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ችግራቸው እንዲባባስ የሚያደርግ ነገር ማድረግ አንፈልግም። በተመሳሳይም እንዲህ ባለው አገር ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች በዚያ አገር የሚከናወነውን አገልግሎትና ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ አስመልክቶ መናገራቸው ተገቢ አይሆንም።

13. በምሳሌ 11:13 መሠረት ሽማግሌዎች ምን ማድረግ አለባቸው? ለምንስ?

13 በተለይ ሽማግሌዎች ሚስጥር ጠባቂ በመሆን በምሳሌ 11:13 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋል አለባቸው። (ጥቅሱን አንብብ።) ይሁንና አንድ ሽማግሌ ያገባ ከሆነ እንዲህ ማድረግ ከባድ ሊሆንበት ይችላል። ባለትዳሮች ወዳጅነታቸውን የሚያጠናክሩት አዘውትረው በመጨዋወት እንዲሁም ውስጣዊ ስሜታቸውን፣ ሐሳባቸውንና ስጋታቸውን በመነጋገር ነው። ሆኖም ሽማግሌዎች የወንድሞቻቸውንና የእህቶቻቸውን ሚስጥር ማውጣት እንደሌለባቸው ያውቃሉ። ሽማግሌዎች ሚስጥር ካባከኑ የወንድሞችን እምነት ያጣሉ፤ እንዲሁም መልካም ስማቸው ይጎድፋል። በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንድሞች “በሁለት ምላስ የማይናገሩ” ወይም በአንደበታቸው የማያታልሉ ሊሆኑ ይገባል። (1 ጢሞ. 3:8 ግርጌ) ይህም ሲባል መሠሪ ወይም ሐሜተኛ ሊሆኑ አይገባም ማለት ነው። አንድ ሽማግሌ ሚስቱን የሚወድ ከሆነ የማያስፈልጋትን መረጃ በመስጠት ሸክም አይጨምርባትም።

14. የአንድ ሽማግሌ ሚስት ባለቤቷ መልካም ስሙን ይዞ እንዲቀጥል ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው?

14 የአንድ ሽማግሌ ሚስት ባለቤቷ በሚስጥር መያዝ ያለባቸውን ነገሮች እንዲነግራት ባለመገፋፋት ባለቤቷ መልካም ስሙን ይዞ እንዲቀጥል ልትረዳው ትችላለች። አንዲት ሚስት ይህን ምክር ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ባለቤቷን እንደምትደግፍ ብሎም ሚስጥራቸውን ለነገሩት ወንድሞች አክብሮት እንዳላት ታሳያለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ የጉባኤው ሰላምና አንድነት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ በማድረጓ ይሖዋን ታስደስታለች።—ሮም 14:19

ይሖዋ ስለምንናገረው ነገር ምን ይሰማዋል?

15. ይሖዋ የኢዮብን ሦስት ጓደኞች በተመለከተ ምን ተሰማው? ለምንስ?

15 መቼና እንዴት መናገር እንዳለብን ከኢዮብ መጽሐፍ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። ኢዮብ በተከታታይ ከባድ ችግሮች ከደረሱበት በኋላ አራት ሰዎች ሊያጽናኑትና ሊመክሩት መጡ። እነዚህ ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ ዝም ብለው ቆይተዋል። ሆኖም ሦስቱ ሰዎች ማለትም ኤሊፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር በኋላ ላይ ከተናገሩት ነገር መረዳት እንደሚቻለው ዝም ብለው የቆዩት ኢዮብን እንዴት እንደሚረዱት ለማሰብ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ኢዮብ ኃጢአት እንደሠራ እንዴት እንደሚያሳምኑት እያሰቡ ነበር። እርግጥ ነው የተናገሯቸው አንዳንዶቹ ሐሳቦች ትክክል ነበሩ፤ ሆኖም ስለ ኢዮብም ሆነ ስለ ይሖዋ የተናገሩት አብዛኛው ነገር ደግነት የጎደለው ወይም ከእውነታው የራቀ ነበር። ኢዮብን ያለርኅራኄ ፈርደውበታል። (ኢዮብ 32:1-3) ታዲያ ይሖዋ ምን ተሰማው? በሦስቱ ሰዎች ላይ ቁጣው ነደደ። ሰዎቹ ሞኞች እንደሆኑ የተናገረ ከመሆኑም ሌላ ኢዮብ እንዲጸልይላቸው እንዲጠይቁት አድርጓል።—ኢዮብ 42:7-9

16. ከኤሊፋዝ፣ ከበልዳዶስና ከሶፋር መጥፎ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

16 ከኤሊፋዝ፣ ከበልዳዶስና ከሶፋር መጥፎ ምሳሌ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በወንድሞቻችን ላይ መፍረድ የለብንም። (ማቴ. 7:1-5) ከዚህ ይልቅ ከመናገራችን በፊት በጥሞና ልናዳምጣቸው ይገባል። ሁኔታቸውን መረዳት የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። (1 ጴጥ. 3:8) በሁለተኛ ደረጃ፣ በምንናገርበት ጊዜ ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል ደግነት የሚንጸባረቅበትና እውነተኛ መሆን ይኖርበታል። (ኤፌ. 4:25) በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ እርስ በርስ የምንነጋገረው ነገር እንደሚያሳስበው እንማራለን።

17. ከኤሊሁ ምሳሌ ምን እንማራለን?

17 ኢዮብን ሊጠይቅ የመጣው አራተኛው ሰው የአብርሃም ዘመድ የሆነው ኤሊሁ ነው። ኤሊሁ ኢዮብና ሦስቱ ሰዎች ሲነጋገሩ ያዳምጥ ነበር። ኤሊሁ ኢዮብ አመለካከቱን እንዲያስተካክል የሚረዳ ቀጥተኛ ምክር ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ መስጠት መቻሉ የተነጋገሩትን ነገር በጥሞና እንዳዳመጠ ያሳያል። (ኢዮብ 33:1, 6, 17) የኤሊሁ ዋነኛ ዓላማ ራሱን ወይም ሌሎች ሰዎችን ሳይሆን ይሖዋን ከፍ ከፍ ማድረግ ነበር። (ኢዮብ 32:21, 22፤ 37:23, 24) የኤሊሁ ምሳሌ ዝም ብለን ማዳመጥ የሚያስፈልገን ጊዜ እንዳለ ያሳያል። (ያዕ. 1:19) በተጨማሪም ምክር በምንሰጥበት ጊዜ ዋናው ዓላማችን ወደ ራሳችን ትኩረት መሳብ ሳይሆን ይሖዋን ከፍ ከፍ ማድረግ መሆን እንዳለበት እንማራለን።

18. አምላክ ለሰጠን የመናገር ችሎታ አድናቆታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 መጽሐፍ ቅዱስ መቼና እንዴት መናገር እንዳለብን የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ አምላክ ለሰጠን የመናገር ችሎታ አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም ነው።” (ምሳሌ 25:11) ሌሎች ሲናገሩ በጥሞና የምናዳምጥ እንዲሁም ከመናገራችን በፊት የምናስብ ከሆነ ንግግራችን እንደ ወርቅ ፖም ውድና ማራኪ ይሆናል። የምንናገረው ብዙም ይሁን ጥቂት ንግግራችን ሌሎችን የሚያንጽ ይሆናል፤ ይሖዋም ይደሰትብናል። (ምሳሌ 23:15፤ ኤፌ. 4:29) አምላክ ለሰጠን ለዚህ ስጦታ አድናቆታችንን ማሳየት የምንችልበት ከዚህ የተሻለ ምን መንገድ አለ!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • መናገር ያለብን መቼ ነው?

  • ዝም ማለት ያለብን መቼ ነው?

  • በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ምን ትምህርት አግኝተሃል?

መዝሙር 82 “ብርሃናችሁ ይብራ”

a መቼ መናገር፣ መቼ ደግሞ ዝም ማለት እንዳለብን ለማወቅ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶች በአምላክ ቃል ውስጥ ይገኛሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ስናስተውልና በሥራ ላይ ስናውል ንግግራችን ይሖዋን የሚያስደስት ይሆናል።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት ለሌላ እህት ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር ስትሰጥ።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ንጽሕናን አስመልክቶ ምክር ሲሰጥ።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ አቢጋኤል በተገቢው ጊዜ ዳዊትን በማነጋገሯ ጥሩ ውጤት አግኝታለች።

e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ባልና ሚስት ሥራችን በታገደበት አካባቢ ሥራው እንዴት እንደሚካሄድ ከመናገር ሲቆጠቡ።

f የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ሽማግሌ ሚስጥራዊ ስለሆነ የጉባኤ ጉዳይ ሰው እንዳይሰማው ተጠንቅቆ ሲነጋገር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ