የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w21 ሚያዝያ ገጽ 20-25
  • ይሖዋ ውድ አድርጎ ይመለከትሃል!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ውድ አድርጎ ይመለከትሃል!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ የሚወደን መሆኑን መጠራጠር አደገኛ ነው
  • ከጳውሎስ ምሳሌ የምናገኘው ትምህርት
  • መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ ጸሎት እና ታማኝ ወዳጆች የሚረዱን እንዴት ነው?
  • በይሖዋ ፍቅር ኑሩ
  • ይሖዋ እንደሚወድህ አምነህ ተቀበል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ፍቅርህ እያደገ ይሂድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • ፍቅራችሁ እንዳይቀዘቅዝ ተጠንቀቁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • ከአምላክ ፍቅር ማን ይለየናል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
w21 ሚያዝያ ገጽ 20-25

የጥናት ርዕስ 17

ይሖዋ ውድ አድርጎ ይመለከትሃል!

“ይሖዋ በሕዝቡ ደስ ይሰኛል።”—መዝ. 149:4

መዝሙር 108 የአምላክ ታማኝ ፍቅር

ማስተዋወቂያa

የተለያየ ባሕል ያላቸው ሰዎች በእርካታ ስሜት ፈገግ ብለው።

የሰማዩ አባታችን በእያንዳንዳችን “ደስ ይሰኛል” (አንቀጽ 1⁠ን ተመልከት)

1. ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር በተያያዘ ምን ያስተውላል?

ይሖዋ አምላክ “በሕዝቡ ደስ ይሰኛል።” (መዝ. 149:4) ይህ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ይሖዋ ያሉንን መልካም ባሕርያት ያስተውላል፤ ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንደምንችል ያውቃል፤ እንዲሁም ወደ ራሱ ይስበናል። ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ ከሆንን ለዘላለም ወዳጃችን ይሆናል!—ዮሐ. 6:44

2. አንዳንዶች ይሖዋ እንደሚወዳቸው ማመን የሚከብዳቸው ለምንድን ነው?

2 አንዳንዶች ‘ይሖዋ ሕዝቡን በቡድን ደረጃ እንደሚወድ አውቃለሁ፤ ሆኖም እኔን በግለሰብ ደረጃ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተኝ እንዴት እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?’ ብለው ያስቡ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች እንዲህ እንዲሰማቸው የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? በልጅነቷ ብዙ መከራ ያሳለፈችው ኦክሳናb እንዲህ ብላለች፦ “በተጠመቅኩበትና አቅኚነት በጀመርኩበት ወቅት ደስተኛ ነበርኩ። ከ15 ዓመት በኋላ ግን በልጅነቴ ያጋጠመኝ መጥፎ ነገር ወደ አእምሮዬ እየመጣ ያሠቃየኝ ጀመር። በመሆኑም የይሖዋን ሞገስ እንዳጣሁና እሱ ሊወደኝ እንደማይችል ተሰማኝ።” ዩዋ የተባለችው አቅኚም በልጅነቷ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋታል፤ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን ማስደሰት ስለፈለግኩ ሕይወቴን ለእሱ ወሰንኩ። ይሁንና ይሖዋ መቼም ቢሆን ሊወደኝ እንደማይችል ይሰማኝ ነበር።”

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ቀደም ሲል እንደተጠቀሱት ታማኝ ክርስቲያኖች ሁሉ አንተም ይሖዋን ከልብህ ብትወደውም እሱ የሚወድህ መሆኑን ትጠራጠር ይሆናል። ይሁንና ይሖዋ ከልቡ እንደሚያስብልህ እርግጠኛ መሆን ያለብህ ለምንድን ነው? እንዲሁም ‘ይሖዋ አይወደኝም’ የሚል ስሜት ሲሰማህ ምን ሊረዳህ ይችላል? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ የሚወደን መሆኑን መጠራጠር አደገኛ ነው

4. ይሖዋ የሚወደን መሆኑን መጠራጠር አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

4 ፍቅር ለሥራ የማነሳሳት ከፍተኛ ኃይል አለው። ይሖዋ እንደሚወደንና እንደሚደግፈን እርግጠኞች ከሆንን በሕይወታችን ውስጥ ችግሮች ቢያጋጥሙንም እንኳ እሱን በሙሉ ልባችን ለማገልገል እንገፋፋለን። በሌላ በኩል ግን፣ አምላክ የሚያስብልን መሆኑን ከተጠራጠርን ‘ጉልበታችን እጅግ ይዳከማል።’ (ምሳሌ 24:10) ከዚህም ሌላ ተስፋ ከቆረጥንና ይሖዋ እንደማይወደን ከተሰማን ለሰይጣን ጥቃቶች ተጋላጭ እንሆናለን።—ኤፌ. 6:16

5. አንዳንዶች ይሖዋ የሚወዳቸው መሆኑን በመጠራጠራቸው ምን ደርሶባቸዋል?

5 በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ታማኝ ክርስቲያኖች ይሖዋ የሚወዳቸው መሆኑን በመጠራጠራቸው ምክንያት በመንፈሳዊ ተዳክመዋል። ጄምስ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በቤቴል እንዲሁም በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ አገለግላለሁ፤ ያም ቢሆን ይሖዋ የማቀርበውን መሥዋዕት የሚቀበል መሆኑን እጠራጠር ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ይሖዋ ጸሎቴን የሚሰማ መሆኑን እንኳ እስከ መጠራጠር ደርሼ ነበር።” የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነችው ኤቫም እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እንደሚወደን መጠራጠር በጣም አደገኛ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፤ ምክንያቱም ይህ ስሜት ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ሁሉን ነገር ይነካብናል። ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለንን ፍላጎትና ይሖዋን በማገልገል የምናገኘውን ደስታ ይቀንሰዋል።” የዘወትር አቅኚና የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ማይክል ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እንደሚያስብላችሁ ካላመናችሁ ቀስ በቀስ ከእሱ እየራቃችሁ ትሄዳላችሁ።”

6. አምላክ የሚወደን መሆኑን መጠራጠር ብንጀምር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

6 እነዚህ ተሞክሮዎች ይሖዋ የሚወደን መሆኑን መጠራጠር መንፈሳዊነታችንን ምን ያህል ሊጎዳው እንደሚችል ያሳያሉ። ይሁንና አምላክ የሚወደን መሆኑን መጠራጠር ብንጀምር ምን ማድረግ ይኖርብናል? እንዲህ ያለውን ሐሳብ ወዲያውኑ ከአእምሯችን ልናወጣው ይገባል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ‘እረፍት የሚነሳ ሐሳብ’ እንዲያስወግድልህ እንዲሁም ‘ልብህንና አእምሮህን የሚጠብቅልህን የአምላክ ሰላም’ እንዲሰጥህ ልትጠይቀው ትችላለህ። (መዝ. 139:23 ግርጌ፤ ፊልጵ. 4:6, 7) በተጨማሪም እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ እንዳልሆንክ አስታውስ። ሌሎች ታማኝ ወንድሞችና እህቶችም ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር ይታገላሉ። በጥንት ዘመን የኖሩ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ እንዲህ ካሉ ስሜቶች ጋር መታገል አስፈልጓቸው ነበር። ከሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።

ከጳውሎስ ምሳሌ የምናገኘው ትምህርት

7. ጳውሎስ የትኞቹ ችግሮች አጋጥመውታል?

7 ብዙ ኃላፊነቶች እንደተደራረቡብህና ሁሉንም በተገቢው መልኩ ማከናወን እንደተሳነህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ የጳውሎስ ስሜት ይገባሃል። ጳውሎስን ያስጨንቀው የነበረው የአንድ ጉባኤ ብቻ ሳይሆን “የጉባኤዎች ሁሉ ሐሳብ” ነበር። (2 ቆሮ. 11:23-28) ያጋጠመህ ከባድ የጤና እክል ደስታህን አሳጥቶሃል? ጳውሎስ ‘ሥጋውን የሚወጋ እሾህ’ ለረጅም ጊዜ አሠቃይቶት ነበር፤ ጳውሎስ ‘እሾህ’ ያለው ያጋጠመውን የጤና እክል ሊሆን ይችላል፤ ከዚህ መከራ ለመገላገል ይጓጓ ነበር። (2 ቆሮ. 12:7-10) ከአለፍጽምናህ ጋር የምታደርገው ትግል ተስፋ አስቆርጦሃል? ጳውሎስም እንዲህ የተሰማው ጊዜ ነበር። ከአለፍጽምናው ጋር በሚያደርገው የማያባራ ትግል የተነሳ “ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ” ብሏል።—ሮም 7:21-24

8. ጳውሎስ ያጋጠሙትን ችግሮች እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው?

8 ጳውሎስ የተለያዩ ፈተናዎችና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም ይሖዋን ማገልገሉን ቀጥሏል። ይህን ለማድረግ የሚያስችል ብርታት ያገኘው እንዴት ነው? ከአለፍጽምናው ጋር መታገል ቢኖርበትም በቤዛው ላይ የማይናወጥ እምነት ነበረው። በተጨማሪም ኢየሱስ ‘በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንደሚኖረው’ የገባውን ቃል ያውቅ ነበር። (ዮሐ. 3:16፤ ሮም 6:23) በቤዛው “የሚያምን ሁሉ” ከተባሉት መካከል ጳውሎስም እንደሚገኝበት ምንም ጥያቄ የለውም። ይሖዋ፣ ንስሐ እስከገቡ ድረስ ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችንም ጭምር ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ ጳውሎስ እርግጠኛ ነበር።—መዝ. 86:5

9. ጳውሎስ በገላትያ 2:20 ላይ ከተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?

9 ጳውሎስ፣ አምላክ ክርስቶስን ቤዛ አድርጎ መስጠቱ ለእሱ ታላቅ ፍቅር ያለው መሆኑን እንደሚያሳይ ያምን ነበር። (ገላትያ 2:20⁠ን አንብብ።) በገላትያ 2:20 መጨረሻ ላይ የሚገኘውን የሚያጽናና ሐሳብ ልብ በል። ጳውሎስ “በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው በአምላክ ልጅ ላይ እምነት አለኝ” ብሏል። ጳውሎስ፣ አምላክ ሊወደው እንደማይችል አልተሰማውም። ‘አምላክ ወንድሞቼን ሊወዳቸው እንደሚችል ይገባኛል፤ እኔን ግን ጨርሶ ሊወደኝ አይችልም’ የሚል አመለካከት አልነበረውም። ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል” ብሏቸዋል። (ሮም 5:8) በእርግጥም የአምላክን ፍቅር ሊገድበው የሚችል ምንም ነገር የለም!

10. ከሮም 8:38, 39 ምን እንማራለን?

10 ሮም 8:38, 39⁠ን አንብብ። ጳውሎስ፣ አምላክ ለእሱ ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። ‘ምንም ነገር ከአምላክ ፍቅር ሊለየን አይችልም’ በማለት ጽፏል። ጳውሎስ፣ ይሖዋ እስራኤላውያንን ምን ያህል በትዕግሥት እንደያዛቸው ያውቅ ነበር። ይሖዋ ለእሱ ምሕረት ያሳየው እንዴት እንደሆነም ያውቃል። ጳውሎስ እንዲህ ብሎ የተናገረ ያህል ነው፦ ‘ይሖዋ የገዛ ልጁ እንኳ ለእኔ ሲል እንዲሞት ካደረገ እንደሚወደኝ የምጠራጠርበት ምን ምክንያት ይኖራል?’—ሮም 8:32

ምስሎች፦ 1. ጳውሎስ ፈሪሳዊ በነበረበት ወቅት አንድን ክርስቲያን እስር ቤት ሲያስገባ። 2. ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ አንድን ወጣት ወንድም ሲያበረታታ።

አምላክ ትኩረት የሚያደርገው አሁን እና ወደፊት በምናከናውናቸው ነገሮች ላይ እንጂ ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች ላይ አይደለም (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)c

11. ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 1:12-15 ላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ኃጢአቶችን ፈጽሞ የነበረ ቢሆንም አምላክ እንደሚወደው እርግጠኛ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

11 አንደኛ ጢሞቴዎስ 1:12-15⁠ን አንብብ። ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ባደረጋቸው ነገሮች የተነሳ አንዳንድ ጊዜ በጥፋተኝነት ስሜት ተውጦ መሆን አለበት። “ከኃጢአተኞች . . . ዋነኛ ነኝ” በማለት ተናግሯል፤ ደግሞም እንዲህ የተሰማው መሆኑ አያስገርምም። ጳውሎስ እውነትን ከማወቁ በፊት ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ እየሄደ ክርስቲያኖችን ያሳድድ ነበር። ብዙዎችን ወህኒ ቤት አስገብቷል፤ አንዳንዶች ደግሞ እንዲገደሉ የድጋፍ ድምፅ ሰጥቷል። (ሥራ 26:10, 11) ጳውሎስ፣ በእሱ ምክንያት ወላጆቹ ከተገደሉበት አንድ ወጣት ክርስቲያን ጋር ቢገናኝ ምን ሊሰማው እንደሚችል እስቲ አስበው። ጳውሎስ በሠራቸው ስህተቶች ተጸጽቷል፤ ሆኖም ያለፈውን ነገር መቀየር እንደማይችል ያውቅ ነበር። ክርስቶስ ለእሱ ሲል እንደሞተ የተቀበለ ሲሆን “አሁን የሆንኩትን ለመሆን የበቃሁት በአምላክ ጸጋ ነው” በማለት በልበ ሙሉነት ጽፏል። (1 ቆሮ. 15:3, 10) እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ክርስቶስ ለአንተ ሲል እንደሞተና ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና የመመሥረት አጋጣሚ እንደከፈተልህ አምነህ ተቀበል። (ሥራ 3:19) የይሖዋ ምሥክሮች ከመሆናችን በፊትም ሆነ በኋላ አንዳንድ ስህተቶችን እንደሠራን የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን አምላክ ትኩረት የሚያደርገው አሁን እና ወደፊት በምናከናውናቸው ነገሮች ላይ እንጂ ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች ላይ አይደለም።—ኢሳ. 1:18

12. እንደማንረባ ወይም ማንም ሊወደን እንደማይችል ሲሰማን በ1 ዮሐንስ 3:19, 20 ላይ ያለው ሐሳብ የሚረዳን እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ ኃጢአትህን ለማስተሰረይ ሲል እንደሞተ ስታስብ ‘እኔ እንዲህ ያለ ክብር የሚገባኝ ሰው አይደለሁም’ የሚል ስሜት ይፈጠርብህ ይሆናል። እንዲህ የሚሰማህ ለምን ሊሆን ይችላል? ፍጹም ያልሆነው ልባችን እንደማንረባና ማንም ሊወደን እንደማይችል እንድናስብ በማድረግ ሊያታልለን ይችላል። (1 ዮሐንስ 3:19, 20⁠ን አንብብ።) እንዲህ ያለ ስሜት ሲፈጠርብን “አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ” እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። የሰማዩ አባታችን ፍቅርና ምሕረት፣ በልባችን ውስጥ ሊያድር ከሚችለው ከየትኛውም አሉታዊ ስሜት የበለጠ ኃይል አለው። ይሖዋ ለእኛ ያለውን አመለካከት ለመቀበል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለዚህ እንዲረዳን አዘውትረን ቃሉን ማንበብ፣ ወደ እሱ መጸለይ እንዲሁም ከታማኝ ሕዝቦቹ ጋር መቀራረብ ያስፈልገናል። እነዚህን ነገሮች ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ ጸሎት እና ታማኝ ወዳጆች የሚረዱን እንዴት ነው?

13. የአምላክን ቃል ማጥናታችን የሚረዳን እንዴት ነው? (“የአምላክ ቃል የረዳቸው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

13 የአምላክን ቃል በየዕለቱ አጥና፤ እንዲህ ማድረግህ የይሖዋ ግሩም ባሕርያት ይበልጥ ግልጽ ሆነው እንዲታዩህ ያደርጋል። እሱ ምን ያህል እንደሚወድህ ትገነዘባለህ። በየቀኑ በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰልህ አስተሳሰብህንና ምኞቶችህን “ለማቅናት” ስለሚረዳህ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖርህ ያደርጋል። (2 ጢሞ. 3:16) ‘አልረባም’ ከሚል ስሜት ጋር የሚታገል ኬቨን የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “መዝሙር 103⁠ን ማንበቤና ማሰላሰሌ አመለካከቴን ለማስተካከልና ይሖዋ ለእኔ ያለውን እውነተኛ ስሜት ለመረዳት አስችሎኛል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤቫም እንዲህ ብላለች፦ “ሁልጊዜ ምሽት ላይ ጸጥ ያለ ቦታ ላይ ሆኜ ይሖዋ ከፍ አድርጎ ስለሚመለከታቸው ነገሮች አሰላስላለሁ። እንዲህ ማድረጌ ውስጣዊ ሰላም እንዳገኝና እምነቴ እንዲጠናከር ይረዳኛል።”

የአምላክ ቃል የረዳቸው እንዴት ነው?

አንዲት እህት አውቶቡስ ውስጥ ሆና መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ።
  • “መጽሐፍ ቅዱስን በተመስጦ ሳጠና በራሴ ላይ ሳይሆን በይሖዋና በሌሎች ሰዎች ላይ ማተኮር እችላለሁ።”—ማይክል

  • “ቋሚ መንፈሳዊ ፕሮግራም ለማዳበር ጥረት ማድረጌ በአሉታዊ ስሜት እንዳልዋጥ ረድቶኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወይም ለማንበብ የማልነሳሳበት ጊዜ እንዳለ አልክድም፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ይሖዋ እንደሚወደኝ እንዲነግረኝ አጋጣሚ እየሰጠሁት ነው።”—ኬቨን

  • “የመዝሙር መጽሐፍን ማንበብ ያስደስተኛል። በተለይ መዝሙር 27⁠ን በጣም እወደዋለሁ። ከቁጥር 1 እስከ 6⁠ን፣ ቁጥር 10⁠ን እንዲሁም ከቁጥር 12 እስከ 14⁠ን በተደጋጋሚ እያነበብኩ አሰላስላለሁ።”—ኦክሳና

  • “በየቀኑ የአምላክን ቃል በማንበብ እና ረጅም ጸሎት በማቅረብ ዕለቱን ለመጀመር ጥረት አደርጋለሁ። የሚያስፈልገኝን እርዳታ የሚሰጠኝ ሐሳብ ምንጊዜም በቃሉ ውስጥ አገኛለሁ።”—ጄምስ

  • “የአምላክን ቃል ሳጠና ወደ ይሖዋ በጣም እንደቀረብኩ ይሰማኛል። ይሖዋ ብርታትና ሰላም ስለሚሰጠኝ ካጠናሁ በኋላ ልቤ በእጅጉ ይረጋጋል። የአምላክን ቃል ማጥናቴ ይሖዋ ችላ እንደማይለኝ እንድተማመን ረድቶኛል።”—ሴጂ

14. ጸሎት የሚረዳን እንዴት ነው?

14 አዘውትረህ ጸልይ። (1 ተሰ. 5:17) ከአንድ ሰው ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንዲኖረን ከፈለግን አዘውትረን ልባዊ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ይኖርብናል። ከይሖዋ ጋር ካለን ወዳጅነት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለይሖዋ ስሜታችንን፣ ሐሳባችንንና ጭንቀታችንን አውጥተን በጸሎት ስንነግረው በእሱ እንደምንተማመን እንዲሁም እንደሚወደን እርግጠኞች እንደሆንን እናሳያለን። (መዝ. 94:17-19፤ 1 ዮሐ. 5:14, 15) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዩዋ እንዲህ ብላለች፦ “ወደ ይሖዋ ስጸልይ በቀኑ ውስጥ ያጋጠሙኝን ነገሮች በመጥቀስ ብቻ ላለመወሰን ጥረት አደርጋለሁ። ለይሖዋ የልቤን አውጥቼ በማፍሰስ እውነተኛ ስሜቴን እነግረዋለሁ። ይሖዋን እንደ አንድ መሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ ሳይሆን ልጆቹን ከልቡ እንደሚወድ አባት መመልከት ጀምሬያለሁ።”—“አንብባችሁታል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

አንብባችሁታል?

ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ አንብባችሁታል? እስካሁን ካላነበባችሁት ለምን በግል ጥናታችሁ ውስጥ አታካትቱትም? በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ይህን መጽሐፍ ማንበቤና ባነበብኩት ነገር ላይ ማሰላሰሌ ሕይወቴን በእጅጉ እንዳሻሻለልኝና ወደ ሰማዩ አባቴ ይበልጥ እንድቀርብ እንደረዳኝ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ። አሁን ይሖዋ ወዳጄ እንደሆነ ይሰማኛል። . . . በቃላት መግለጽ ከምችለው በላይ ይሖዋን እወደዋለሁ፤ እንዲህ ያለ ስሜት ለማዳበር የረዳኝ አንዱ ነገር ይህን መጽሐፍ ማንበቤ ነው።”

15. ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት የሚያሳየን እንዴት ነው?

15 ከታማኝ ወዳጆችህ ጋር ተቀራረብ፤ እነሱ ከይሖዋ ያገኘሃቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው። (ያዕ. 1:17) የሰማዩ አባታችን “ምንጊዜም አፍቃሪ” የሆኑ ወንድሞችና እህቶች በመስጠት በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ያሳየናል። (ምሳሌ 17:17) ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ድጋፍ ስላደረጉለት ክርስቲያኖች ሲናገር “በእጅጉ አጽናንተውኛል” ብሏል። (ቆላ. 4:10, 11 ግርጌ) ክርስቶስ ኢየሱስም እንኳ የወዳጆቹ እርዳታ አስፈልጎታል፤ በመሆኑም መላእክትና ሰዎች ላደረጉለት እርዳታ አመስጋኝ ነበር።—ሉቃስ 22:28, 43

16. ታማኝ ወዳጆች ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የሚረዱን እንዴት ነው?

16 ከይሖዋ ያገኘሃቸው ታማኝ ወዳጆች ከሚሰጡህ እርዳታ የተሟላ ጥቅም እያገኘህ ነው? ለአንድ የጎለመሰ ወዳጃችን ጭንቀታችንን አውጥተን ማካፈላችን የድክመት ምልክት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ጥበቃ ይሆንልናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጄምስ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “በመንፈሳዊ ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረቴ በጣም ጠቅሞኛል። በአሉታዊ ስሜቶች ስዋጥ እነዚህ ውድ ወዳጆቼ በትዕግሥት ያዳምጡኛል፤ እንዲሁም እንደሚወዱኝ ይገልጹልኛል። ከእነሱ ያገኘሁት እርዳታ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወደኝና እንደሚያስብልኝ አስገንዝቦኛል።” ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረታችንና ወዳጅነታችንን ይዘን መቀጠላችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

በይሖዋ ፍቅር ኑሩ

17-18. መስማት ያለብን ማንን ነው? ለምንስ?

17 ሰይጣን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ መታገላችንን እንድናቆም ይፈልጋል። ሰይጣን ይሖዋ እንደማይወደንና መዳን እንደማይገባን እንዲሰማን ይፈልጋል። ሆኖም እስካሁን እንደተመለከትነው ይህ ጨርሶ ከእውነታው የራቀ ሐሳብ ነው።

18 ይሖዋ ይወድሃል። በእሱ ፊት ትልቅ ዋጋ አለህ። እሱን ከታዘዝከው፣ ልክ እንደ ኢየሱስ ለዘላለም ‘በፍቅሩ መኖር’ ትችላለህ። (ዮሐ. 15:10) እንግዲያው ሰይጣንንም ሆነ የሚኮንንህን ልብህን አትስማ። ከዚህ ይልቅ፣ በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለውን መልካም ነገር የሚያየው ይሖዋ የሚልህን ስማ። ይሖዋ አንተን ጨምሮ ‘በሕዝቡ ደስ እንደሚሰኝ’ እርግጠኛ ሁን!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ይሖዋ እንደሚወደን ጥርጣሬ ቢያድርብን ይህን ስሜት ልናሸንፈው የሚገባው ለምንድን ነው?

  • ሐዋርያው ጳውሎስና በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

  • መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ ጸሎትና ታማኝ ወዳጆች የሚረዱን እንዴት ነው?

መዝሙር 141 ሕይወት ተአምር ነው

a አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይሖዋ እንደሚወዳቸው ማመን ይከብዳቸዋል። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወደን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም ይሖዋ እንደሚወደን ጥርጣሬ ሲያድርብን ምን ማድረግ እንደምንችል እንመለከታለን።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በርካታ ክርስቲያኖችን ወህኒ ቤት አስገብቷል። ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር አምኖ ከተቀበለ በኋላ ግን ለውጥ አድርጎ ክርስቲያን ወንድሞቹን ማበረታታት ጀመረ፤ ከእነዚህ ወንድሞች መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎች ዘመዶች ሊሆኑ ይችላሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ