የሕይወት ታሪክ
በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኩት አስደሳች ሕይወት
በካናዳ ቤቴል የነበረኝ የመጀመሪያ ሥራ የሕትመት ክፍሉን መጥረግ ነበር። ጊዜው 1958 ሲሆን እኔም 18 ዓመቴ ነበር። በሕይወቴ ደስተኛ ነበርኩ። ብዙም ሳይቆይ ደግሞ መጽሔቶች ታትመው ሲወጡ ዙሪያቸውን በሚከረክመው ማሽን ላይ መሥራት ጀመርኩ። ቤቴል ውስጥ በማገልገሌ በጣም ደስተኛ ነበርኩ!
በቀጣዩ ዓመት፣ በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ አዲስ ማተሚያ ማሽን ስለሚገጠም እዚያ ሄደው የሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ለቤቴል ቤተሰብ ማስታወቂያ ተነገረ። እኔም ተመዘገብኩ፤ ከዚያም መመረጤን ሳውቅ በጣም ደስ አለኝ። ካናዳዊ የሆኑ ሌሎች ሦስት ቤቴላውያንም ተመርጠው ነበር፤ እነሱም ቢል ማክሌላን፣ ኬን ኖርዲን እና ዴኒስ ሊች ነበሩ። በደቡብ አፍሪካ ለረጅም ጊዜ እንደምንቆይ ተነገረን።
እናቴ ጋ ደውዬ “እማዬ፣ ትልቅ ዜና አለኝ። ደቡብ አፍሪካ ልሄድ ነው!” አልኳት። እናቴ በባሕርይዋ ዝምተኛ ሰው ነች፤ ሆኖም ጠንካራ እምነት ያላት መንፈሳዊ ሴት ነበረች። ብዙ ነገር ባትለኝም ውሳኔዬን እንደደገፈችው እርግጠኛ ነበርኩ። እሷም ሆነች አባቴ ከእነሱ በጣም በመራቄ ቢያዝኑም በውሳኔዬ ቅሬታ አሰምተው አያውቁም።
ወደ ደቡብ አፍሪካ አቀናሁ!
በ1959 ከዴኒስ ሊች፣ ከኬን ኖርዲን እና ከቢል ማክሌላን ጋር ከኬፕ ታውን ወደ ጆሃንስበርግ በባቡር ስንጓዝ
አራታችን ከ60 ዓመት በኋላ በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ በ2019 በተገናኘንበት ወቅት
አራታችንም ከማተሚያ ማሽኖቹ ጋር በተያያዘ በብሩክሊን ቤቴል የሦስት ወር ሥልጠና ተሰጠን። ከዚያም ወደ ኬፕ ታውን፣ ደቡብ አፍሪካ በሚሄድ የዕቃ መጫኛ መርከብ ላይ ተሳፈርን። በወቅቱ 20 ዓመቴ ነበር። ኬፕ ታውን ከደረስን በኋላ ወደ ጆሃንስበርግ ለመሄድ ረጅሙን የባቡር ጉዞ ተያያዝነው። ባቡሩ የተነሳው ምሽት ላይ ነበር፤ ሊነጋጋ ሲል ከፊል በረሃማ በሆነ አካባቢ በምትገኝ ትንሽ ከተማ አቆምን። አየሩ በጭስና በአቧራ የተሞላ ከመሆኑም ሌላ በጣም ይሞቅ ነበር። አራታችንም በመስኮት ወደ ውጭ ስንመለከት “ምን ዓይነት አገር ነው? ምን ውስጥ ነው የገባነው?” ብለን አስበን ነበር። ከዓመታት በኋላ ተመልሰን ወደዚህ ቦታ ስንሄድ ግን እነዚህ ከተሞች ሰላማዊና ደስ የሚሉ እንደሆኑ አስተውለናል።
ለተወሰኑ ዓመታት ያህል ምድቤ ሊኖታይፕ በተባለው አስገራሚና የተወሳሰበ ማሽን ላይ መሥራት ነበር፤ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ለማተም የሚያስፈልጉትን ነገሮች አዘጋጅ ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮው መጽሔቶቹን በብዙ የአፍሪካ ቋንቋዎች ያትም ነበር፤ መጽሔቶችን የምናትመው ለደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገሮችም ጭምር ነበር። ዓለምን አቋርጠን እንድንመጣ ምክንያት የሆነው አዲሱ ማተሚያ በጥሩ ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋለ ነበር!
ከጊዜ በኋላ በሕትመት ቢሮው ውስጥ መሥራት ጀመርኩ፤ ይህ ቢሮ የሕትመት፣ ጽሑፍ የመላክ እና የትርጉም ሥራውን ይከታተላል። ሕይወቴ በሥራ የተወጠረ፣ አርኪ እና ትርጉም ያለው ነበር።
ትዳር እና አዲስ ምድብ
በ1968 እኔ እና ሎራ በልዩ አቅኚነት ስናገለግል
በ1968 ሎራ ቦወን ከተባለች አቅኚ እህት ጋር ትዳር መሠረትኩ። ሎራ የምትኖረው በቤቴል አቅራቢያ ሲሆን ጽሑፎች በመተየብ የትርጉም ክፍሉን ታግዝ ነበር። በወቅቱ አዲስ ተጋቢዎች በቤቴል የሚያገለግሉበት ዝግጅት ስላልነበር ልዩ አቅኚ ሆነን ተመደብን። መጀመሪያ ላይ ሁኔታው ትንሽ አሳስቦኝ ነበር። ስለ ምግብና ስለ መጠለያ ፈጽሞ በማልጨነቅበት በቤቴል አሥር ዓመት ካገለገልኩ በኋላ በልዩ አቅኚ አበል እንዴት ልንኖር እንችላለን? ከሰዓት፣ ከተመላልሶ መጠየቅ እና ጽሑፍ ከማበርከት ጋር በተያያዘ የሚጠበቅብን ግብ ላይ ከደረስን እያንዳንዳችን በየወሩ 25 ራንድ (በወቅቱ በነበረው ተመን 35 የአሜሪካ ዶላር) ይሰጠን ነበር። ለቤት ኪራይ፣ ለምግብ፣ ለትራንስፖርት፣ ለሕክምና እንዲሁም ለሌሎች የግል ወጪዎች የምንጠቀመው ይህን ገንዘብ ነበር።
በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ባለችው ደርባን ከተማ ውስጥ በሚገኝ ትንሽ ቡድን ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያ ብዙ ሕንዶች ይኖሩ ነበር፤ አብዛኞቹ በ1800ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ በስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ወዛደሮች ዘሮች ናቸው። አሁን በሌሎች የሥራ መስኮች ተሰማርተዋል፤ ሆኖም ባሕላቸውንና ጣፋጭ ምግቦቻቸውን አልተዉም። እንግሊዝኛ ስለሚናገሩ ከእነሱ ጋር መግባባት ቀላል ነበር።
ልዩ አቅኚዎች በየወሩ 150 ሰዓት ማገልገል ይጠበቅባቸው ነበር፤ ስለዚህ እኔና ሎራ በመጀመሪያው ቀን ስድስት ሰዓት ለማገልገል ወሰንን። አየሩ ሞቃትና ወበቃማ ነበር። ተመላልሶ መጠየቅም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስላልነበረን ስድስት ሰዓት ሙሉ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ነበረብን። አገልግሎት ከጀመርን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰዓቴን ስመለከት ለካስ ያገለገልነው 40 ደቂቃ ብቻ ነው! “ታዲያ እንዴት ነው የምንዘልቀው?” ብዬ አሰብኩ።
ብዙም ሳይቆይ ግን ጥሩ ፕሮግራም አወጣን። በየቀኑ ሳንድዊች እናዘጋጃለን፤ እንዲሁም በፔርሙዝ ሾርባ ወይም ቡና እንይዛለን። ሲደክመን ትንሿን ቮልስዋገናችንን ዛፍ ሥር አቁመን አረፍ እንላለን፤ አንዳንድ ጊዜ የሚያማምሩ የሕንድ ልጆች በዙሪያችን ተሰብስበው ይመለከቱናል። ጥቂት ቀናት እንዳገለገልን ግን ሁለት ወይም ሦስት ሰዓት ከሰበክን በኋላ ጊዜው ቶሎ ይሄድልን ጀመር።
በዚያ ክልል ውስጥ ላሉ እንግዳ ተቀባይ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር በጣም ያስደስታል! ሕንዶቹ ሰው አክባሪ፣ ደግ እንዲሁም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ናቸው። በርካታ የሂንዱ እምነት ተከታዮች መልእክታችንን ይቀበሉ ነበር። ስለ ይሖዋ፣ ስለ ኢየሱስ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወደፊት ስለሚመጣው ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንዲሁም ሙታን ስላላቸው ተስፋ መማር ያስደስታቸው ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ የጥናቶቻችን ቁጥር 20 ደረሰ። በየቀኑ ከጥናቶቻችን ቤተሰቦች ጋር ወይ ምሳ ወይ ራት አብረን እንበላለን። በጣም ደስተኞች ነበርን።
ብዙም ሳይቆይ አዲስ የአገልግሎት ምድብ ተሰጠን፤ ውብ በሆነው የሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ባሉት አካባቢዎች በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተመደብን። በየሳምንቱ በተለያዩ ወንድሞች ቤት በእንግድነት እናርፍ የነበረ ሲሆን በጉባኤ ውስጥ ያሉትን አስፋፊዎች በመጠየቅና አብረናቸው በማገልገል እናበረታታቸው ነበር። ወንድሞች የቤተሰባቸው አባል እንደሆንን እንዲሰማን አድርገዋል፤ እኛም ከልጆቻቸውና ከቤት እንስሶቻቸው ጋር መጫወት ያስደስተን ነበር። በዚህ መንገድ ሁለት አስደሳች ዓመታት አለፉ። ከዚያም ከቅርንጫፍ ቢሮው ያልጠበቅነው ስልክ ተደወለልን። “ቤቴል እንድትመጡ እንፈልጋለን” አሉን። እኔም “ይሄኛውን ምድብ እኮ በጣም ወደነው ነበር” አልኳቸው። ያም ቢሆን በተመደብንበት ቦታ ሁሉ ለማገልገል ፈቃደኞች ነበርን።
ቤቴል ተመለስን
ቤቴል ውስጥ የተመደብኩት በአገልግሎት ዘርፍ ነበር፤ በዚያም ተሞክሮ ካላቸው በሳል የሆኑ በርካታ ወንድሞች ጋር የመሥራት መብት አግኝቼ ነበር። በዚያ ዘመን የወረዳ የበላይ ተመልካቹ አንድን ጉባኤ ጎብኝቶ ሪፖርት ከላከ በኋላ ጉባኤው ከቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ይደርሰው ነበር። የደብዳቤው ዓላማ ወንድሞችን ማበረታታትና አስፈላጊ ከሆነ መመሪያ መስጠት ነበር። በመሆኑም ጸሐፊዎቻችን ከቆሳ፣ ከዙሉ እንዲሁም ከሌሎች ቋንቋዎች ወደ እንግሊዝኛ፣ ከእንግሊዝኛ ደግሞ ወደነዚህ የአፍሪካ ቋንቋዎች ደብዳቤዎችን ይተረጉሙ ነበር፤ ይህ ቀላል ሥራ አልነበረም። እነዚህን ታታሪ ተርጓሚዎች በጣም አደንቃቸዋለሁ፤ እነዚህ ወንድሞች፣ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ስለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች እንዳውቅም ረድተውኛል።
በወቅቱ ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ሥርዓት ሥር ነበረች። እያንዳንዱ ዘር የተመደበለት መኖሪያ አካባቢ ነበረው፤ በመሆኑም የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች አይቀላቀሉም። ጥቁር ወንድሞቻችን የራሳቸውን ቋንቋ ይጠቀሙ ነበር፤ በራሳቸው ቋንቋ ይሰብኩ ነበር፤ እንዲሁም በራሳቸው ቋንቋ የጉባኤ ስብሰባ ያደርጉ ነበር።
የተመደብኩባቸው ጉባኤዎች በሙሉ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ስለነበሩ ከጥቁሮቹ ወንድሞቻችን ጋር ለመተዋወቅ ብዙ አጋጣሚ አልነበረኝም። አሁን ግን ስለ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን፣ ስለ ባሕላቸውና ስለ ልማዳቸው የማወቅ አጋጣሚ አገኘሁ። ከአካባቢው ልማዶችና ሃይማኖታዊ እምነቶች ጋር በተያያዘ ወንድሞቻችን እያጋጠሟቸው ስላሉት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አወቅኩ። ወንድሞቻችን ከቤተሰቦቻቸውና ከመንደራቸው ነዋሪዎች ከባድ ተቃውሞ ቢደርስባቸውም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶችንና መናፍስታዊ ድርጊቶችን አይከተሉም ነበር። በእርግጥም በጣም ደፋሮች ነበሩ! በገጠራማ አካባቢዎች ድህነት ተንሰራፍቶ ነበር። ብዙዎች በቀለም ትምህርት ባይገፉም ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ነበራቸው።
ከአምልኮ ነፃነት ወይም ከገለልተኝነት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወንድሞች ፍርድ ቤት መቅረብ ሲያስፈልጋቸው በሕግ ሂደቱ ውስጥ ለእነሱ ድጋፍ የመስጠት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ትናንሽ ልጆች በጸሎት ወይም በሃይማኖታዊ መዝሙር ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ከትምህርት ቤት ሲባረሩ ያሳዩትን ታማኝነትና ድፍረት መመልከት በእጅጉ እምነት የሚያጠናክር ነበር።
ወንድሞቻችን በወቅቱ ስዋዚላንድ ተብላ በምትጠራው ትንሿ የአፍሪካ አገር ውስጥ ሌላም ፈተና አጋጥሟቸዋል። ዳግማዊ ንጉሥ ሶቡዛ ሲሞቱ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በሐዘን መግለጫ ልማዶች እንዲካፈሉ ታዘው ነበር። ወንዶች ፀጉራቸውን መላጨት፣ ሴቶች ደግሞ ፀጉራቸውን በአጭሩ መቆረጥ ነበረባቸው። ብዙ ወንድሞችና እህቶች የሞቱ ዘመዶችን ከማምለክ ጋር ግንኙነት ባላቸው በእነዚህ ልማዶች ለመካፈል ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ስደት ደርሶባቸዋል። ለይሖዋ ባሳዩት ታማኝነት ኮርተናል! ከአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ስለ ታማኝነትና ትዕግሥት ብዙ ተምረናል፤ ይህ ደግሞ እምነታችንን አጎልብቶልናል።
ወደ ሕትመት ሥራ ተመለስኩ
በ1981 በኮምፒውተር በሚታገዝ የሕትመት ሥራ ላይ እንድሳተፍ ተመደብኩ። ስለዚህ እንደገና በሕትመት ክፍሉ ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። የሕትመት ዘዴዎች በጣም እየተለወጡ ነበር፤ በዚህ ሥራ ለመካፈል ጓጉቼ ነበር! አንድ ድርጅት ቅርንጫፍ ቢሯችን እንዲሞክረው አንድ ማሽን በነፃ ሰጠን። በመሆኑም እንጠቀምባቸው የነበሩትን ዘጠኝ ሊኖታይፕ ማሽኖች በአምስት አዲስ ማሽኖች ቀየርናቸው። በተጨማሪም አዲስ ማተሚያ ማሽን ገጠምን። ሥራው እየተቀላጠፈ ነበር!
በኮምፒውተር የታገዘው አሠራር፣ ሜፕስን (መልቲላንጉዌጅ ኤሌክትሮኒክ ፐብሊሺንግ ሲስተም) ተጠቅመን ጽሑፉን በገጹ ላይ የምናስቀምጥበትን አዲስ መንገድ እንድንፈጥር አስችሎናል። አራት ቤቴላውያን ከካናዳ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲመጡ ምክንያት ከሆኑት ግዙፍና ቀርፋፋ ማሽኖች ተነስተን የደረስንበት ደረጃ በጣም አስደናቂ ነው! (ኢሳ. 60:17) በዚህ ወቅት አራታችንም መንፈሳዊ አመለካከት ካላቸው ግሩም አቅኚ እህቶች ጋር ትዳር መሥርተን ነበር። እኔና ቢል በቤቴል ማገልገላችንን ቀጥለን ነበር። ኬንና ዴኒስ ደግሞ ቤተሰብ መሥርተው ነበር።
ቅርንጫፍ ቢሯችን የሚያከናውናቸው ሥራዎች እየሰፉ ሄዱ። በቅርንጫፍ ቢሯችን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የሚተረጎሙባቸውና የሚታተሙባቸው ቋንቋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡ ሲሆን ጽሑፎችን ወደ ሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎችም እንልክ ነበር። በዚህም የተነሳ አዲስ የቤቴል ሕንፃ አስፈለገን። ወንድሞች ከጆሃንስበርግ በስተ ምዕራብ በሚገኝ ውብ አካባቢ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ የገነቡ ሲሆን በ1987 ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰነ። እየሰፋ በሚሄደው ሥራ ውስጥ የበኩሌን አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።
ሌላ ምድብ ተሰጠን!
በ2001 አዲስ በተቋቋመው የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ እንዳገለግል ስጋበዝ በጣም ተገረምኩ። በደቡብ አፍሪካ ያለውን ሥራችንን እና ወዳጆቻችንን ትተን መሄዳችን ቢያሳዝነንም በዩናይትድ ስቴትስ የቤቴል ቤተሰብ ውስጥ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ጓጉተን ነበር።
ሆኖም በዕድሜ የገፉትን የሎራን እናት ትተን መሄዳችን አሳስቦን ነበር። ከኒው ዮርክ ሆነን ብዙም ልንረዳቸው እንደማንችል የታወቀ ነው፤ የሎራ ሦስት እህቶች ግን ለእሳቸው አካላዊ፣ ስሜታዊና ቁሳዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው አረጋገጡልን። እንዲህ አሉን፦ “እኛ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት አንችልም፤ ሆኖም እማዬን ከተንከባከብናት እናንተ በአገልግሎት ምድባችሁ መቀጠል እንድትችሉ እናግዛችኋለን።” የሎራን እህቶች ከልብ እናመሰግናቸዋለን።
በቶሮንቶ፣ ካናዳ የሚኖረው ወንድሜና ባለቤቱም መበለት የሆነችውን እናቴን ይንከባከቧት ነበር። በወቅቱ እናቴ ከወንድሜ ቤተሰብ ጋር ከ20 ዓመት በላይ ኖራለች። ኒው ዮርክ ከሄድን ብዙም ሳይቆይ እናቴ አረፈች፤ ወንድሜና ባለቤቱ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ በፍቅር ያደረጉላትን እንክብካቤ በጣም እናደንቃለን። በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችንን ለመንከባከብ ሲሉ በሕይወታቸው ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ የቤተሰብ አባሎች ስላሉን በጣም አመስጋኞች ነን፤ ይህ ኃላፊነት አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሊሆን ይችላል።
ለተወሰኑ ዓመታት ያህል በዩናይትድ ስቴትስ የነበረኝ የሥራ ኃላፊነት ከጽሑፍ ሕትመት ጋር የተያያዘ ነበር፤ ሥራው ይበልጥ ዘመናዊና ቀላል ሆኖ ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ በዕቃ ግዢ ክፍል አገልግያለሁ። ላለፉት 20 ዓመታት በዚህ ትልቅ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በማገልገላችን በጣም ደስተኞች ነን። በአሁኑ ጊዜ የቤቴል ቤተሰባችን አባላት 5,000 የተመላላሾች ቁጥር ደግሞ 2,000 ደርሷል!
የዛሬ 60 ዓመት፣ የሕይወቴ አቅጣጫ ይህን ሊመስል ይችላል ብዬ ጨርሶ ላስብ አልችልም ነበር። በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ሎራ በሙሉ ልቧ ደግፋኛለች። በእርግጥም ሕይወታችን አርኪ ነበር! በነበሩን የተለያዩ የሥራ ምድቦች በጣም ደስተኛ ነን፤ እንዲሁም በተለያየ የዓለም ክፍል የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ስንጎበኝ የተዋወቅናቸውን ወንድሞች ጨምሮ አብረናቸው የሠራናቸውን ወንድሞችና እህቶች ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። አሁን 80 ዓመት ስላለፈኝ የሥራ ጫናዬ ቀንሶልኛል፤ ደግሞም ሥራውን ማከናወን የሚችሉ ከእኔ በዕድሜ የሚያንሱ ብቃት ያላቸው ብዙ ወንድሞች አሉ።
መዝሙራዊው “ይሖዋ አምላኩ የሆነ ብሔር . . . ደስተኛ ነው” በማለት ጽፏል። (መዝ. 33:12) ይህ ምንኛ እውነት ነው! ከዚህ ደስተኛ ሕዝብ ጋር ይሖዋን ማገልገል በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ።