የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w22 ጥር ገጽ 20-25
  • በመታሰቢያው በዓል ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በመታሰቢያው በዓል ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዓሉ ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው?
  • ሌሎች በጎች በዓሉ ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው?
  • ሁላችንም በበዓሉ ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?
  • ሁላችንም በዓሉ ላይ መገኘታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
  • የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ አምላክንና ክርስቶስን ያወድሳሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • ይሖዋ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር የምናደርገውን ጥረት ይባርካል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • የመታሰቢያው በዓል ለአንድነታችን አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • የጌታ ራትን የምናከብረው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
w22 ጥር ገጽ 20-25

የጥናት ርዕስ 4

በመታሰቢያው በዓል ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?

“ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።”—ሉቃስ 22:19

መዝሙር 20 ውድ ልጅህን ሰጠኸን

ማስተዋወቂያa

1-2. (ሀ) በሞት ያጣነውን የምንወደውን ሰው በተለይ የምናስታውሰው መቼ ነው? (ለ) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ምን አድርጓል?

ምንም ያህል ጊዜው ቢረዝም፣ በሞት ያጣናቸውን የምንወዳቸውን ሰዎች ምንጊዜም እናስታውሳቸዋለን። ከዓመት ዓመት፣ የሞቱበት ዕለት ሲደርስ ትዝታቸው እንደ አዲስ ድቅን ይልብናል።

2 በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር አብረን ሆነን፣ በጣም የምንወደው ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተበትን ዕለት መታሰቢያ እናከብራለን። (1 ጴጥ. 1:8) በዚህ ዕለት አብረን የምንሰበሰበው እኛን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ የሰጠንን ክርስቶስን ለማሰብ ነው። (ማቴ. 20:28) ኢየሱስም ቢሆን ተከታዮቹ ሞቱን እንዲያስቡ ይፈልጋል። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት አንድ ልዩ በዓል ካቋቋመ በኋላ “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል።—ሉቃስ 22:19

3. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

3 በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ከሚገኙት መካከል ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ሆኖም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም በዚህ በዓል ላይ ይገኛሉ። በዚህ ርዕስ ላይ፣ ሁለቱም ቡድኖች በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት የሚፈልጉባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን። በዓሉ ላይ መገኘታችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልንም እናያለን። እስቲ በመጀመሪያ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በበዓሉ ላይ የሚገኙባቸውን አንዳንድ ምክንያቶች እንመልከት።

ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዓሉ ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው?

4. ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ለምንድን ነው?

4 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙት የበዓሉ ተካፋዮች ሆነው ነው። ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ለምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ምን እንደተከናወነ እንመልከት። ፋሲካ ከተከበረ በኋላ ኢየሱስ አንድ በዓል አቋቋመ፤ ይህ በዓል በኋላ ላይ የጌታ ራት ተብሏል። ኢየሱስ ቂጣውና የወይን ጠጁ በ11ዱ ታማኝ ሐዋርያቱ ፊት እንዲያልፍ ካደረገ በኋላ ከዚያ ላይ እንዲበሉና እንዲጠጡ ነገራቸው። ከዚያም ስለ ሁለት ቃል ኪዳኖች ማለትም ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን እና ስለ መንግሥት ቃል ኪዳን ገለጸላቸው።b (ሉቃስ 22:19, 20, 28-30) እነዚህ ቃል ኪዳኖች ሐዋርያቱና የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሌሎች ሰዎች በሰማይ ነገሥታትና ካህናት እንዲሆኑ መንገድ ከፍተዋል። (ራእይ 5:10፤ 14:1) በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል የሚችሉት በእነዚህ ሁለት ቃል ኪዳኖች የታቀፉት ቅቡዓን ቀሪዎችc ብቻ ናቸው።

5. ቅቡዓኑ የተሰጣቸው ተስፋ ምን እንደሚያስገኝላቸው ያውቃሉ?

5 ቅቡዓኑ በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት የሚፈልጉበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ይህ ነው፦ በዓሉ ላይ መገኘታቸው በተስፋቸው ላይ ለማሰላሰል አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ይሖዋ አስደናቂ ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ በሰማይ የማይሞትና የማይበሰብስ ሕይወት ያገኛሉ። እንዲሁም ክብር ከተጎናጸፈው ከኢየሱስ ክርስቶስና ከሌሎቹ 144,000ዎች ጋር ከሁሉ በላይ ደግሞ ራሱ ይሖዋ ባለበት እሱን የማገልገል መብት ይኖራቸዋል! (1 ቆሮ. 15:51-53፤ 1 ዮሐ. 3:2) ቅቡዓኑ ያገኙት ጥሪ፣ በሰማይ እንዲህ ያሉ መብቶች እንደሚያስገኝላቸው ያውቃሉ። ሰማይ እንዲሄዱ የሚፈቀድላቸው ግን እስከ ዕለተ ሞታቸው በታማኝነት ከጸኑ ነው። (2 ጢሞ. 4:7, 8) ቅቡዓኑ በሰማያዊ ተስፋቸው ላይ ማሰላሰላቸው በጣም ያስደስታቸዋል። (ቲቶ 2:13) ‘ሌሎች በጎችስ?’ (ዮሐ. 10:16) በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ሌሎች በጎች በዓሉ ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው?

6. ሌሎች በጎች በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው?

6 ሌሎች በጎች በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙት የበዓሉ ተካፋዮች ሆነው ሳይሆን ታዳሚዎች ሆነው ነው። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ የተጋበዙት በ1938 ነው። የመጋቢት 1, 1938 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዟል፦ “[ሌሎች በጎች] እንዲህ ባለው ስብሰባ ላይ መገኘታቸውና በፕሮግራሙ ላይ መታደማቸው በጣም ትክክለኛና ተገቢ ነው። . . . ይህ ለእነሱም ቢሆን የደስታ ወቅት ነው፤ ሊሆንም ይገባል።” በአንድ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኙ የሚጋበዙ እንግዶች እንደሚደሰቱ ሁሉ ሌሎች በጎችም በመታሰቢያው በዓል ላይ ታዳሚ ሆነው በመገኘታቸው ደስተኛ ናቸው።

7. ሌሎች በጎች የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ዕለት የሚቀርበውን ንግግር ለማዳመጥ የሚጓጉት ለምንድን ነው?

7 ሌሎች በጎችም በተስፋቸው ላይ ያሰላስላሉ። የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ዕለት የሚሰጠውን ንግግር ለማዳመጥ ይጓጓሉ፤ ምክንያቱም ንግግሩ በአብዛኛው የሚያተኩረው ክርስቶስ እና 144,000 ተባባሪ ገዢዎቹ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ለታማኝ የሰው ልጆች በሚያደርጉት ነገር ላይ ነው። እነዚህ ተባባሪ ገዥዎች በንጉሣቸው በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው ምድር ገነት እንድትሆን እንዲሁም የሰው ዘር ፍጽምና ደረጃ ላይ እንዲደርስ በሚከናወነው ሥራ ትልቅ እገዛ ያበረክታሉ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት የመታሰቢያው በዓል ታዳሚዎች እንደ ኢሳይያስ 35:5, 6፤ 65:21-23 እና ራእይ 21:3, 4 ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ላይ በማሰላሰል ምን ያህል እንደሚደሰቱ አስቡት። ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖራቸውን ሕይወት በዓይነ ሕሊናቸው መሣላቸው የወደፊቱ ተስፋቸው ይበልጥ እውን እንዲሆንላቸው ያደርጋል፤ ይሖዋን እስከ መጨረሻው ለማገልገል ያላቸው ቁርጠኝነትም ይጠናከራል።—ማቴ. 24:13፤ ገላ. 6:9

8. ሌሎች በጎች በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙበት ሌላው ምክንያት ምንድን ነው?

8 ሌሎች በጎች በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙበትን ሌላም ምክንያት እንመልከት። ለቅቡዓኑ ፍቅራቸውን እና ድጋፋቸውን ማሳየት ይፈልጋሉ። የአምላክ ቃል በቅቡዓኑ እና ምድራዊ ተስፋ ባላቸው መካከል የጠበቀ ዝምድና እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

9. በዘካርያስ 8:23 ላይ የሚገኘው ትንቢት ሌሎች በጎች ስለ ቅቡዓኑ ያላቸውን ስሜት በተመለከተ ምን ይጠቁማል?

9 ዘካርያስ 8:23⁠ን አንብብ። ይህ ትንቢት ሌሎች በጎች ስለ ቅቡዓን ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ያላቸውን ስሜት በተመለከተ ልብ የሚነካ ምስል ይፈጥራል። “አይሁዳዊ” እና “እናንተ” የሚሉት ቃላት የሚያመለክቱት ቅቡዓን ቀሪዎችን ነው። (ሮም 2:28, 29) “ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ [የተውጣጡት] አሥር ሰዎች” ሌሎች በጎችን ያመለክታሉ። እነዚህ ሰዎች ቅቡዓኑን ‘አጥብቀው ይይዛሉ’ ወይም በታማኝነት ከእነሱ ጋር ይጣበቃሉ። ይህም በንጹሕ አምልኮ ከእነሱ ጋር እንደሚተባበሩ የሚያሳይ ነው። ከዚህ አንጻር የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ምሽት ሌሎች በጎች ከቅቡዓኑ ጋር ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝት ለማሳየት በፕሮግራሙ ላይ አብረዋቸው መገኘታቸው ምንም አያስገርምም።

10. በሕዝቅኤል 37:15-19, 24, 25 ላይ ባለው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ይሖዋ ምን አድርጓል?

10 ሕዝቅኤል 37:15-19, 24, 25⁠ን አንብብ። በዚህ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ይሖዋ በቅቡዓኑ እና በሌሎች በጎች መካከል የማይሰበር አንድነት እንዲኖር አድርጓል። በትንቢቱ ላይ ሁለት በትሮች ተጠቅሰዋል። ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች “ለይሁዳ” (የእስራኤል ነገሥታት የሚመረጡበት ነገድ ነው) እንደተባለው በትር ናቸው። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ደግሞ እንደ “ኤፍሬም” በትር ናቸው።d ይሖዋ ሁለቱን ቡድኖች አንድ ስለሚያደርጋቸው “አንድ በትር” ይሆናሉ። ይህም በአንድ ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር በአንድነት እንደሚያገለግሉ ያመለክታል። በየዓመቱ ቅቡዓኑ እና ሌሎች በጎች በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙት ሁለት የተለያዩ ቡድኖች ሆነው ሳይሆን ‘በአንድ እረኛ’ ሥር እንዳለ “አንድ መንጋ” ሆነው ነው።—ዮሐ. 10:16

11. በማቴዎስ 25:31-36, 40 ላይ የተጠቀሱት ‘በጎች’ ለክርስቶስ ወንድሞች ድጋፋቸውን ማሳየት የሚችሉበት ዋነኛው መንገድ ምንድን ነው?

11 ማቴዎስ 25:31-36, 40⁠ን አንብብ። በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት ‘በጎች’ የሚያመለክቱት በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ጻድቃንን ማለትም ሌሎች በጎችን ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች በምድር ላይ የቀሩትን በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ ወንድሞች በታማኝነት ይደግፋሉ። ይህን የሚያደርጉበት ዋነኛው መንገድ ከባድ ኃላፊነት በሆነው ዓለም አቀፍ የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ለእነሱ እገዛ ማድረግ ነው።—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20

12-13. ሌሎች በጎች ለክርስቶስ ወንድሞች ድጋፋቸውን የሚያሳዩባቸው ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው?

12 በየዓመቱ የመታሰቢያው በዓል ሲቃረብ ባሉት ሳምንታት፣ ሌሎች በጎች ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ዘመቻ የተሟላ ተሳትፎ በማድረግ የክርስቶስን ወንድሞች እንደሚደግፉ ያሳያሉ። (“የመታሰቢያው በዓል ለሚከበርበት ወቅት እየተዘጋጀህ ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በተጨማሪም በዓሉ በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ሁሉ እንዲከበር ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ። አብዛኞቹ ጉባኤዎች ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈል ሰው ባይኖራቸውም ይህን ዝግጅት ያደርጋሉ። ሌሎች በጎች በእነዚህ መንገዶች ለክርስቶስ ወንድሞች ድጋፍ በማድረጋቸው በጣም ደስተኞች ናቸው። እነዚህ በጎች ኢየሱስ ለቅቡዓን ወንድሞቹ ያደረጉትን ነገር ሁሉ ለእሱ እንደተደረገ አድርጎ እንደሚቆጥረው ያውቃሉ።—ማቴ. 25:37-40

13 ተስፋችን ምንም ይሁን ምን ሁላችንም በመታሰቢያው በዓል ላይ እንድንገኝ የሚያነሳሱን ሌሎች ምን ምክንያቶች አሉን?

በጌታ እራት ምሽት፣ ኢየሱስና ታማኝ ሐዋርያቱ በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰብስበው።

የመታሰቢያው በዓል ለሚከበርበት ወቅት እየተዘጋጀህ ነው?

ከበዓሉ በፊት

  • ሌሎች ሰዎች በዚህ ወሳኝ በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው ዘመቻ የቻልከውን ያህል የተሟላ ተሳትፎ አድርግ። መጋበዝ የምትፈልጋቸውን ሰዎች ስም ጻፍ።

  • በዓሉ በሚከበርበት ሰሞን ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትችል እንደሆነ በጸሎት አስብበት።

  • ለመታሰቢያው በዓል፣ ለቤዛው እንዲሁም ይሖዋ እና ኢየሱስ ላሳዩን ፍቅር ያለንን አድናቆት የሚያሳድጉ ርዕሶችን ወይም ሌሎች መረጃዎችን ከልስ። ለምሳሌ ያህል፣ ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 14 እና 23 እንዲሁም “ተከታዬ ሁን” የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 መጠቀም ትችላለህ።

  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር የተባለው ቡክሌት ላይ የሚገኘውን የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ተከትለህ አንብብ። ኢየሱስ ምድር ላይ ስላሳለፋቸው የመጨረሻዎቹ ቀናት፣ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው በሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ ጊዜ መድበህ አሰላስል።

በበዓሉ ምሽት

  • ወደ በዓሉ የሚመጡ እንግዶችንና የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን ሞቅ አድርገህ ለመቀበል በጊዜ ድረስ።

  • ንግግሩን በትኩረት አዳምጥ፤ እንዲሁም ተናጋሪው ጥቅሶችን እያነበበ ሲያብራራ መጽሐፍ ቅዱስህን ይዘህ ተከታተል።

  • ፕሮግራሙ ካበቃ በኋላ በዓሉ ላይ የተገኘን እንግዳ ለማነጋገር ሞክር፤ ጥያቄዎች ካሉት መልስለት። ግለሰቡ ፍላጎት ካሳየ አንተ ወይም ሌላ ሰው እንደገና አግኝታችሁ እንድታነጋግሩት ዝግጅት አድርግ።

ከበዓሉ በኋላ

ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን አነጋግራቸው። ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ተጠቅመህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ጋብዝ።

አንድ ባልና ሚስት ወደ አንድ ሰው ቤት ሄደው “ለዘላለም በደስታ ኑር!” የተባለውን ብሮሹር ሲሰጡት።

ሁላችንም በበዓሉ ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?

14. ይሖዋ እና ኢየሱስ ታላቅ ፍቅር ያሳዩን እንዴት ነው?

14 ይሖዋ እና ኢየሱስ ላሳዩን ፍቅር አመስጋኝ ነን። ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ፍቅሩን አሳይቶናል፤ ይህን ያደረገበት ከሁሉ የላቀ አንድ መንገድ ግን አለ። እሱም ለእኛ ሲል እንዲሠቃይና እንዲሞት የሚወደውን ልጁን በመላክ ያሳየን ታላቅ ፍቅር ነው። (ዮሐ. 3:16) ኢየሱስም ለእኛ ሲል ሕይወቱን በፈቃደኝነት መስጠቱ ታላቅ የፍቅር መገለጫ እንደሆነ እንገነዘባለን። (ዮሐ. 15:13) ይሖዋ እና ኢየሱስ የዋሉልንን ውለታ መቼም ቢሆን መክፈል አንችልም። ሆኖም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን አመስጋኝነታችንን ማሳየት እንችላለን። (ቆላ. 3:15) እንዲሁም እነሱ ለእኛ ያሳዩንን ፍቅር ለማሰብም ሆነ ለእነሱ ያለንን ፍቅር ለማሳየት በመታሰቢያው በዓል ላይ እንገኛለን።

15. ቅቡዓኑም ሆኑ ሌሎች በጎች ለቤዛው ስጦታ ከፍተኛ አድናቆት ያላቸው ለምንድን ነው?

15 ለቤዛው ስጦታ ከፍተኛ አድናቆት አለን። (ማቴ. 20:28) ቅቡዓኑ አስደናቂ ተስፋ እንዲያገኙ መንገድ ስለከፈተላቸው ቤዛውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ ያላቸውን እምነት መሠረት በማድረግ ይሖዋ ጻድቃን ናችሁ ብሏቸዋል፤ ልጆቹ አድርጎም ወስዷቸዋል። (ሮም 5:1፤ 8:15-17, 23) ሌሎች በጎችም ለቤዛው አድናቆት አላቸው። በፈሰሰው የክርስቶስ ደም ላይ እምነት ስላላቸው በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም አግኝተዋል፤ ለእሱ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ ይችላሉ፤ እንዲሁም “ታላቁን መከራ አልፈው” በሕይወት የመኖር ተስፋ አላቸው። (ራእይ 7:13-15) ቅቡዓኑም ሆኑ ሌሎች በጎች ለቤዛው ያላቸውን አድናቆት ማሳየት የሚችሉበት አንዱ መንገድ በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት ነው።

16. በመታሰቢያው በዓል ላይ የምንገኝበት ሌላው ምክንያት ምንድን ነው?

16 በመታሰቢያው በዓል ላይ የምንገኝበት ሌላው ምክንያት ኢየሱስን መታዘዝ ስለምንፈልግ ነው። ተስፋችን ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ባቋቋመበት ምሽት “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ በግለሰብ ደረጃ አክብደን እንመለከተዋለን።—1 ቆሮ. 11:23, 24

ሁላችንም በዓሉ ላይ መገኘታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

17. የመታሰቢያው በዓል ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ የሚረዳን እንዴት ነው?

17 ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን። (ያዕ. 4:8) ቀደም ሲል እንዳየነው የመታሰቢያው በዓል ይሖዋ ስለሰጠን ተስፋ ለማሰብ እንዲሁም እሱ ባሳየን ታላቅ ፍቅር ላይ ለማሰላሰል አጋጣሚ ይሰጠናል። (ኤር. 29:11፤ 1 ዮሐ. 4:8-10) አስተማማኝ በሆነው የወደፊቱ ተስፋችን እና አምላክ ለእኛ ባለው ጽኑ ፍቅር ላይ ስናሰላስል ለይሖዋ ያለን ፍቅር ይጨምራል፤ ከእሱ ጋር የመሠረትነው ዝምድናም ይጠናከራል።—ሮም 8:38, 39

18. ኢየሱስ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

18 የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል እንነሳሳለን። (1 ጴጥ. 2:21) በመታሰቢያው በዓል ሰሞን፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው የመጨረሻ ሳምንት፣ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን እናነባለን። በዓሉ በሚከበርበት ምሽት የሚሰጠው ንግግር ደግሞ ኢየሱስ ያሳየንን ፍቅር ያስታውሰናል። (ኤፌ. 5:2፤ 1 ዮሐ. 3:16) ኢየሱስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ስለተወው ምሳሌ ስናነብና ስናሰላስል “እሱ በተመላለሰበት መንገድ [ለመመላለስ]” እንነሳሳለን።—1 ዮሐ. 2:6

19. ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

19 ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ያለን ቁርጠኝነት ይጠናከራል። (ይሁዳ 20, 21) አምላክን ለመታዘዝ፣ ስሙን ለማስቀደስና ልቡን ለማስደሰት የምንችለውን ሁሉ በማድረግ በእሱ ፍቅር መኖር እንችላለን። (ምሳሌ 27:11፤ ማቴ. 6:9፤ 1 ዮሐ. 5:3) በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታችን፣ እያንዳንዱን ቀን ይሖዋን ‘መቼም ቢሆን ከአንተ ፍቅር መውጣት አልፈልግም!’ እንደምንለው በሚያሳይ መንገድ ለመኖር ይበልጥ ያነሳሳናል።

20. በመታሰቢያው በዓል ላይ ለመገኘት የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉን?

20 ተስፋችን ሰማይ መሄድም ሆነ ምድር ላይ ለዘላለም መኖር በመታሰቢያው በዓል ላይ የምንገኝበት በቂ ምክንያት አለን። በየዓመቱ በዚህ ዕለት አብረን ስንሰበሰብ፣ የምንወደውን ጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት እናስባለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ለእኛ ያሳየንን ከሁሉ የላቀ ፍቅር እናስታውሳለን። በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል የሚከበረው ዓርብ፣ ሚያዝያ 15, 2022 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው። ይሖዋን እና ልጁን እንወዳቸዋለን፤ በመሆኑም የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ፈጽሞ የማንቀርበት በዓል ነው!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ የሚያነሳሷቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

  • ሌሎች በጎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ የሚያነሳሷቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

  • ሁላችንም በበዓሉ ላይ መገኘታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

መዝሙር 16 ያህ ልጁን ሾሟል አወድሱት

a ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር በየዓመቱ የሚከበረው የመታሰቢያው በዓል በጉጉት የምንጠብቀው ወቅት ነው። ይህ ርዕስ በዚህ በዓል ላይ እንድንገኝ የሚያነሳሱንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ያብራራል፤ በተጨማሪም በበዓሉ ላይ መገኘታችን እንዴት እንደሚጠቅመን እንመለከታለን።

b ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን እና ስለ መንግሥት ቃል ኪዳን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በጥቅምት 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “‘የመንግሥት ካህናት’ ትሆናላችሁ” የሚለውን ርዕስ ከገጽ 15-17 ተመልከት።

c ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ቅቡዓን ቀሪዎች የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው በምድር ላይ በሕይወት ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ነው።

d በሕዝቅኤል ምዕራፍ 37 ስለሚገኘው ስለ ሁለት በትሮች የሚገልጽ ትንቢት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ! የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 130-135 አን. 3-17 ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ