የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w23 የካቲት ገጽ 8-13
  • ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችሁ የተሟላ ጥቅም አግኙ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችሁ የተሟላ ጥቅም አግኙ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የምታነቡትን ለመረዳት ጥረት አድርጉ
  • ስታነቡ ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማግኘት ጥረት አድርጉ
  • የምታነቡት ነገር እንዲቀርጻችሁ ፍቀዱ
  • ቃሉን ማንበብ ደስታ ያስገኛል
  • በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ መጠቀም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ለማንበብ ትጋ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለመጠቀም የሚረዱ ሰባት ዘዴዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • ማንበብና ያነበቡትን ማስታወስ የሚቻልበት መንገድ
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
w23 የካቲት ገጽ 8-13

የጥናት ርዕስ 7

ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችሁ የተሟላ ጥቅም አግኙ

“ምን ትረዳለህ?”—ሉቃስ 10:26

መዝሙር 97 የአምላክ ቃል ሕይወት ነው

ማስተዋወቂያa

1. ኢየሱስ ለቅዱሳን መጻሕፍት ትልቅ ቦታ ይሰጥ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

ኢየሱስ ሲያስተምር ማዳመጥ ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስቡት። ቅዱሳን መጻሕፍትን በተደጋጋሚ በቃሉ ይጠቅስ ነበር! እንዲያውም ከተጠመቀ በኋላ የተናገራቸው ተመዝግበው የሚገኙት የመጀመሪያዎቹ ቃላትም ሆኑ ልክ ከመሞቱ በፊት ከተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት መካከል አንዳንዶቹ ከቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ ነበሩ።b (ዘዳ. 8:3፤ መዝ. 31:5፤ ሉቃስ 4:4፤ 23:46) በእነዚህ ሁለት ክንውኖች መካከል ባሉት ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜያት ውስጥ ደግሞ በሕዝብ ፊት በተደጋጋሚ ቅዱሳን መጻሕፍትን አንብቧል፣ ጠቅሷል እንዲሁም አብራርቷል።—ማቴ. 5:17, 18, 21, 22, 27, 28፤ ሉቃስ 4:16-20

ምስሎች፦ 1. ኢየሱስ በልጅነቱ ወላጆቹ ሲያነጋግሩት ሲሰማ። 2. ኢየሱስ ከፍ ካለ በኋላ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ ምኩራብ ሄዶ ቅዱሳን መጻሕፍት ሲነበቡ በትኩረት ሲያዳምጥ። 3. ኢየሱስ አዋቂ ከሆነ በኋላ ጥቅልል ሲያነብ።

ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደሚወድ አሳይቷል፤ ቅዱሳን መጻሕፍት ድርጊቱን እንዲቀርጹትም ፈቅዷል (አንቀጽ 2⁠ን ተመልከት)

2. ኢየሱስ ከልጅነቱ አንስቶ ቅዱሳን መጻሕፍትን በደንብ እንዲያውቅ የረዳው ምንድን ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

2 ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ባሉት ዓመታት የአምላክን ቃል በተደጋጋሚ ያነብና ያዳምጥ ነበር። ቤት ውስጥ ማርያምና ዮሴፍ በየዕለቱ ከቤተሰቡ ጋር በሚጨዋወቱበት ጊዜ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ሲጠቅሱ እንደሰማ ምንም ጥርጥር የለውም።c (ዘዳ. 6:6, 7) ኢየሱስ በየሰንበቱ ከቤተሰቡ ጋር በምኩራብ ይገኝ እንደነበር እርግጠኛ መሆን እንችላለን። (ሉቃስ 4:16) እዚያ በሚገኝበት ወቅት ቅዱሳን መጻሕፍት ሲነበቡ በጥንቃቄ ያዳምጥ እንደነበር ግልጽ ነው። በጊዜ ሂደት ኢየሱስ እነዚህን ቅዱሳን መጻሕፍት ራሱ ማንበብ ቻለ። ይህም ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲያውቃቸው ብቻ ሳይሆን እንዲወዳቸውና ሕይወቱን በእነሱ መሠረት እንዲመራ አስችሎታል። ለምሳሌ ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለ በቤተ መቅደሱ የተከናወነውን ነገር ማስታወስ እንችላለን። የሙሴን ሕግ ጠንቅቀው ያውቁ የነበሩት መምህራን በኢየሱስ ‘የመረዳት ችሎታና በመልሱ ተደንቀው’ ነበር።—ሉቃስ 2:46, 47, 52

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 እኛም ቅዱሳን መጻሕፍትን አዘውትረን የምናነብ ከሆነ የአምላክን ቃል ልናውቀውና ልንወደው እንችላለን። ሆኖም ከምናነበው ነገር የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ኢየሱስ ጸሐፍትን፣ ፈሪሳውያንንና ሰዱቃውያንን ጨምሮ ሕጉን ያውቁ ለነበሩት ሰዎች ከተናገረው ነገር ትምህርት ማግኘት እንችላለን። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ደጋግመው ያነቡ ነበር፤ ሆኖም ከሚያነቡት ነገር ጥቅም ማግኘት አልቻሉም። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ከቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅም ማግኘት ከፈለጉ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ሦስት ነገሮችን ጠቁሟል። ለእነሱ የተናገረው ሐሳብ (1) የምናነበውን ነገር በመረዳት፣ (2) ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን በማግኘት እንዲሁም (3) የአምላክ ቃል እንዲቀርጸን በመፍቀድ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንድንችል ይረዳናል።

የምታነቡትን ለመረዳት ጥረት አድርጉ

4. ሉቃስ 10:25-29 ላይ ያለው ዘገባ የአምላክን ቃል ስለማንበብ ምን ያስተምረናል?

4 በአምላክ ቃል ውስጥ የምናነበውን ነገር ትርጉም መረዳት እንፈልጋለን። አለዚያ ከምናነበው ነገር ሙሉ ጥቅም ላናገኝ እንችላለን። ኢየሱስ ‘ከአንድ ሕግ አዋቂ’ ጋር ያደረገውን ውይይት እንደ ምሳሌ እንመልከት። (ሉቃስ 10:25-29⁠ን አንብብ።) ሰውየው የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለበት ሲጠይቀው ኢየሱስ “በሕጉ ላይ የተጻፈው ምንድን ነው? አንተስ ምን ትረዳለህ?” በማለት ወደ አምላክ ቃል መራው። ሰውየው አምላክንና ባልንጀራን ስለመውደድ የሚናገሩትን ጥቅሶች በመጥቀስ ትክክለኛውን መልስ መስጠት ችሏል። (ዘሌ. 19:18፤ ዘዳ. 6:5) ግን ቀጥሎ ምን እንዳለ ልብ በሉ፤ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” በማለት ጠይቋል። ይህ ጥያቄው እንደሚጠቁመው ሰውየው ያነበበውን ነገር በደንብ አልተረዳውም። በዚህም የተነሳ ጥቅሶቹን በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጋቸው አላወቀም።

የምናነበውን ነገር የመረዳት ችሎታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ሊሄድ ይችላል

5. መጸለያችሁና ረጋ ብላችሁ ማንበባችሁ የምታነቡትን ነገር ይበልጥ ለመረዳት የሚያግዛችሁ እንዴት ነው?

5 ጥሩ የንባብ ልማድ ማዳበራችን የአምላክን ቃል ይበልጥ ለመረዳት ያስችለናል። ከዚህ በታች በዚህ ረገድ የሚረዱን አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮች ቀርበዋል። ማንበብ ከመጀመራችሁ በፊት ጸልዩ። ቅዱሳን መጻሕፍትን ለመረዳት የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል፤ ስለዚህ ትኩረታችንን ለመሰብሰብ እንዲረዳን ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ልንጠይቀው እንችላለን። ከዚያም ረጋ ብላችሁ አንብቡ። ይህም የምታነቡትን ነገር ለመረዳት ያስችላችኋል። ጮክ ብላችሁ ወይም የመጽሐፍ ቅዱሱ የድምፅ ቅጂ በቋንቋችሁ የሚገኝ ከሆነ የድምፅ ቅጂውን እያዳመጣችሁ ማንበቡን ጠቃሚ ሆኖ ልታገኙት ትችላላችሁ። የማየትና የመስማት ችሎታችሁን አጣምራችሁ መጠቀማችሁ የአምላክ ቃል በአእምሯችሁና በልባችሁ ላይ ይበልጥ እንዲቀረጽ ይረዳችኋል። (ኢያሱ 1:8) አንብባችሁ ከጨረሳችሁ በኋላ በድጋሚ በመጸለይ ቃሉን ስለሰጣችሁ ይሖዋን አመስግኑት፤ እንዲሁም ያነበባችሁትን ነገር ተግባር ላይ ለማዋል እንዲረዳችሁ ለምኑት።

ፎቶግራፎች፦ 1. አንዲት እህት መጽሐፍ ቅዱሷ ላይ ማስታወሻ ስትጽፍ። 2. አንድ ወንድም ታብሌቱ ላይ እያጠና ያለውን ርዕስ ሲያቀልምና ማስታወሻ ሲይዝ። 3. አንዲት እህት “JW ላይብረሪ” የተባለውን አፕሊኬሽን ተጠቅማ መጽሐፍ ቅዱሷን ስታቀልምና ማስታወሻ ስትይዝ።

አጫጭር ማስታወሻዎችን መያዛችሁ የምታነቡትን ነገር ለመረዳትና ለማስታወስ የሚያግዛችሁ ለምንድን ነው? (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)

6. በምታነቡበት ጊዜ ጥያቄዎችን መጠየቃችሁና አጫጭር ማስታወሻዎችን መያዛችሁ የሚጠቅማችሁ እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ለመረዳት የሚያግዟችሁ ሌሎች ሁለት ነገሮች አሉ። ስለምታነቡት ነገር ራሳችሁን ጠይቁ። አንድን ዘገባ ስታነቡ እንዲህ እያላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ፦ ‘ዋና ዋናዎቹ ባለታሪኮች እነማን ናቸው? እየተናገረ ያለው ማን ነው? የሚናገረው ለማን ነው? ለምንስ? ድርጊቱ እየተከናወነ ያለው የትና መቼ ነው?’ እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች የምንባቡን ዋና ሐሳብ ለመረዳትና በደንብ ለማጤን ይረዷችኋል። በተጨማሪም ስታነቡ አጭር ማስታወሻ ያዙ። አንድን ሐሳብ ለመጻፍ ሐሳቡን ማቀናበር ያስፈልጋችኋል፤ ይህም ሐሳቡ በአእምሯችሁ ውስጥ ቁልጭ ብሎ እንዲቀመጥ ያደርጋል። የምታነቡትን ነገር መጻፋችሁ ያን ነገር ለማስታወስም ይረዳችኋል። ያሏችሁን ጥያቄዎች፣ ምርምር ስታደርጉ ያገኛችሁትን ነገር፣ ዋና ዋና ነጥቦችን፣ ያነበባችሁትን እንዴት ሥራ ላይ ልታውሉት እንደምትችሉ ወይም ያን ነገር ስታነቡ ምን ስሜት እንደተሰማችሁ ልትጽፉ ትችላላችሁ። እንዲህ ያሉ ማስታወሻዎችን መያዛችሁ የአምላክ ቃል ለእናንተ በግለሰብ ደረጃ የተጻፈላችሁ መልእክት እንደሆነ እንዲሰማችሁ ያደርጋል።

7. በምናነብበት ጊዜ የትኛው ባሕርይ ያስፈልገናል? ለምንስ? (ማቴዎስ 24:15)

7 ኢየሱስ ከአምላክ ቃል ላይ የምናነበውን ነገር መረዳት ከፈለግን ሊኖረን የሚገባ አንድ አስፈላጊ ባሕርይ እንዳለ ጠቁሟል፤ ይህም ማስተዋል ነው። (ማቴዎስ 24:15⁠ን አንብብ።) ማስተዋል ምንድን ነው? አንድ ሐሳብ ከሌላው ጋር የሚዛመደው ወይም የሚለያየው እንዴት እንደሆነ የመለየት እንዲሁም ፊት ለፊት የማይታይን ነገር የመረዳት ችሎታ ነው። ኢየሱስ እንደጠቆመው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ ለመረዳት ማስተዋል ያስፈልገናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከምናነበው ከእያንዳንዱ ሐሳብ የተሟላ ጥቅም ለማግኘትም ይህ ባሕርይ ያስፈልገናል።

8. በማስተዋል ማንበብ የምንችለው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ማስተዋል ይሰጣል። ስለዚህ ወደ እሱ በመጸለይ ይህን ባሕርይ ለማዳበር እንዲረዳችሁ ለምኑት። (ምሳሌ 2:6) ከጸሎታችሁ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ የምትችሉት እንዴት ነው? የምታነቡትን ነገር በጥንቃቄ አጢኑ፤ እንዲሁም ከምታውቋቸው ነገሮች ጋር እንዴት እንደሚዛመድ አስቡ። የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎቻችን በዚህ ረገድ ይረዷችኋል፤ ለምሳሌ የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን ጽሑፍ መጠቀም ትችላላችሁ። እነዚህ መሣሪያዎች የምታነቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ትርጉም እንዲሁም እንዴት ተግባራዊ ልታደርጉት እንደምትችሉ ለማስተዋል ይረዷችኋል። (ዕብ. 5:14) በማስተዋል የምታነቡ ከሆነ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ያላችሁ ግንዛቤ እያደገ ይሄዳል።

ስታነቡ ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማግኘት ጥረት አድርጉ

9. ሰዱቃውያን የትኛውን ወሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ችላ ብለው ነበር?

9 ሰዱቃውያን የመጀመሪያዎቹን አምስት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጠንቅቀው ቢያውቁም በመንፈስ መሪነት በተጻፉት በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን አስፈላጊ እውነቶች ችላ ብለዋቸዋል። ለምሳሌ ስለ ሙታን ትንሣኤ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ ምን ምላሽ እንደሰጣቸው እንመልከት። እንዲህ ሲል ጠይቋቸዋል፦ “ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ አምላክ ሙሴን ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ እንዳለው አላነበባችሁም?” (ማር. 12:18, 26) ሰዱቃውያን ይህን ዘገባ ብዙ ጊዜ አንብበውት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፤ ኢየሱስ ያነሳላቸው ጥያቄ ግን ወሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሆነውን የትንሣኤን ትምህርት ችላ ብለውት እንደነበር አጋልጧል።—ማር. 12:27፤ ሉቃስ 20:38d

10. በምናነብበት ጊዜ ለምን ነገር ንቁ መሆን አለብን?

10 ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ወይም ዘገባ ስናነብ ከዚያ ምንባብ የምናገኛቸውን ትምህርቶች ሁሉ ለመረዳት ንቁ መሆን አለብን። መሠረታዊ የሆኑ ትምህርቶችን ብቻ ሳይሆን በዘገባው ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ ጥልቀት ያላቸው እውነቶችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችንም ማስተዋል እንፈልጋለን።

11. በ2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 መሠረት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው?

11 መጽሐፍ ቅዱስን በምታነቡበት ጊዜ ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው? ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:16, 17 ምን እንደሚል ልብ በሉ። (ጥቅሱን አንብብ።) ጥቅሱ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ” ለሚከተሉት ነገሮች ‘እንደሚጠቅሙ’ ይናገራል፦ (1) ለማስተማር፣ (2) ለመውቀስ፣ (3) ነገሮችን ለማቅናትና (4) ለመገሠጽ። ብዙ ጊዜ ከማትጠቀሙባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትም እንኳ እነዚህን አራት ጥቅሞች ማግኘት ትችላላችሁ። ዘገባው ስለ ይሖዋ፣ ስለ ዓላማዎቹ ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምን እንደሚያስተምራችሁ ለማጤን ሞክሩ። ለመውቀስ የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ አስቡ። ይህን ማድረግ የምትችሉት ጥቅሶቹ የተሳሳቱ ዝንባሌዎችን ወይም አመለካከቶችን ለመለየትና ለማስወገድ እንዲሁም በታማኝነት ለመጽናት የሚረዷችሁ እንዴት እንደሆነ በማስተዋል ነው። ዘገባውን ነገሮችን ለማቅናት ወይም የተሳሳተ አመለካከትን ለማስተካከል እንዴት ልትጠቀሙበት እንደምትችሉ አስቡ፤ ምናልባትም አገልግሎት ላይ የምታገኟቸው ሰዎች ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ልታስቡ ትችላላችሁ። በተጨማሪም በጥቅሶቹ ውስጥ ራሳችሁን ለመገሠጽና የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ ለማንጸባረቅ የሚረዳችሁ ነጥብ እንዳለ ለማስተዋል ሞክሩ። እነዚህን አራት ጥቅሞች በአእምሯችሁ ከያዛችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችሁን ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱ ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ታገኛላችሁ።

የምታነቡት ነገር እንዲቀርጻችሁ ፍቀዱ

12. ኢየሱስ ፈሪሳውያኑን “አላነበባችሁም?” ብሎ የጠየቃቸው ለምን ነበር?

12 ኢየሱስ ፈሪሳውያን ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ያላቸው አረዳድ የተሳሳተ እንደሆነ ለማጋለጥም “አላነበባችሁም?” የሚለውን ጥያቄ ተጠቅሟል። (ማቴ. 12:1-7)e በዚያ ወቅት ፈሪሳውያኑ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሰንበትን እንደጣሱ ተናግረው ነበር። በምላሹም ኢየሱስ ሁለት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎችንና በሆሴዕ ላይ የሚገኝ ጥቅስ ጠቀሰላቸው፤ በዚህ መንገድ ኢየሱስ ፈሪሳውያኑ የሰንበትን ሕግ ዓላማ እንዳልተረዱና ምሕረት እንዳላሳዩ ጠቁሟል። እነዚህ ሰዎች በሚያነቡት የአምላክ ቃል ሊቀረጹ ያልቻሉት ለምን ነበር? ምክንያቱም ኩራተኞች የነበሩ ከመሆኑም ሌላ ቃሉን ያነቡ የነበረው ሌሎችን የመተቸት ዓላማ ይዘው ነው። ይህ ዝንባሌያቸው የሚያነቡትን ነገር እንዳያስተውሉ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።—ማቴ. 23:23፤ ዮሐ. 5:39, 40

13. መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያለብን በምን ዓይነት ዝንባሌ ነው? ለምንስ?

13 ኢየሱስ የተናገረው ነገር መጽሐፍ ቅዱስን በትክክለኛው ዝንባሌ ማንበብ እንዳለብን ያስተምረናል። ከፈሪሳውያኑ በተቃራኒ ቅኖችና ለመማር ዝግጁዎች መሆን አለብን። ‘በውስጣችን የሚተከለውን ቃል በገርነት ልንቀበል’ ይገባል። (ያዕ. 1:21) ገር ከሆንን የአምላክ ቃል በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ እንፈቅዳለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምሕረት፣ ስለ ርኅራኄና ስለ ፍቅር የሚያስተምረው ትምህርት ሊቀርጸን የሚችለው ኩራትንና የተቺነት ዝንባሌን ካስወገድን ብቻ ነው።

የአምላክ ቃል እንዲቀርጸን እየፈቀድን ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)f

14. መጽሐፍ ቅዱስ እንዲቀርጸን እየፈቀድን መሆን አለመሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

14 ሌሎችን የምንይዝበት መንገድ የአምላክ ቃል እንዲቀርጸን እየፈቀድን ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ሊጠቁም ይችላል። ፈሪሳውያኑ የአምላክ ቃል ወደ ልባቸው ዘልቆ እንዲገባ ስላልፈቀዱ “ምንም በደል ባልሠሩት ላይ [ይፈርዱ]” ነበር። (ማቴ. 12:7) በተመሳሳይ እኛም ሌሎችን የምናይበትና የምንይዝበት መንገድ የአምላክ ቃል እንዲቀርጸን መፍቀድ አለመፍቀዳችንን ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ሌሎች ጥሩ ጎን ከመናገር ይልቅ ደካማ ጎናቸውን መናገር ይቀናናል? መሐሪዎችና ይቅር ለማለት ዝግጁ ነን ወይስ ሌሎችን መተቸትና በእነሱ ላይ ቂም መያዝ ይቀናናል? በዚህ መንገድ ራሳችንን መመርመራችን የምናነበው ነገር አስተሳሰባችንን፣ ስሜታችንንና ድርጊታችንን እንዲቀርጸው እየፈቀድን መሆን አለመሆኑን ሊጠቁም ይችላል።—1 ጢሞ. 4:12, 15፤ ዕብ. 4:12

ቃሉን ማንበብ ደስታ ያስገኛል

15. ኢየሱስ ለቅዱሳን መጻሕፍት ምን አመለካከት ነበረው?

15 ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ይወድ ነበር። ይህ ስሜቱ መዝሙር 40:8 ላይ በትንቢት ተነግሯል፤ ጥቅሱ “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” ይላል። በዚህም የተነሳ በይሖዋ አገልግሎት ደስተኛና ስኬታማ ሊሆን ችሏል። እኛም የአምላክ ቃል ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባ የምንፈቅድ ከሆነ ደስተኛና ስኬታማ መሆን እንችላለን።—መዝ. 1:1-3

16. ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት በየትኞቹ ነገሮች ላይ ለመሥራት አስበሃል? (“ኢየሱስ የተናገረው ነገር የምታነቡትን ነገር ለመረዳት ያግዛችኋል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

16 ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላትና ከተወው ምሳሌ ጋር በሚስማማ መልኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ችሎታችንን እናሻሽል። በመጸለይ፣ ረጋ ብለን በማንበብ፣ ጥያቄዎችን በመጠየቅና አጫጭር ማስታወሻዎችን በመያዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን የመረዳት ችሎታችንን ማሳደግ እንችላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን ተጠቅመን የምናነበውን ነገር በጥንቃቄ እናመዛዝን፤ ይህም በማስተዋል ለማንበብ ያስችለናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ውስጥ የሚገኙ ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማግኘት ጥረት እናድርግ፤ እንዲህ ማድረጋችን ብዙም ትኩረት የማንሰጣቸውን ዘገባዎች ጨምሮ ሙሉውን የአምላክን ቃል በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ይረዳናል። በተጨማሪም በትክክለኛው የልብ ዝንባሌ በማንበብ የአምላክ ቃል እንዲቀርጸን እንፍቀድ። በእነዚህ አቅጣጫዎች የቻልነውን ሁሉ ካደረግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን የተሟላ ጥቅም እናገኛለን፤ እንዲሁም ከምንጊዜውም ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንቀርባለን።—መዝ. 119:17, 18፤ ያዕ. 4:8

ኢየሱስ የተናገረው ነገር የምታነቡትን ነገር ለመረዳት ያግዛችኋል

  • የምታነቡትን ነገር ለመረዳት ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም እንዴት ተግባራዊ እንደምታደርጉት ለማወቅ የማስተዋል ችሎታችሁን አዳብሩ።—ማቴ. 24:15፤ ሉቃስ 10:25-37

  • ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማግኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በጥንቃቄ መርምሩ።—ማር. 12:18-27

  • የአምላክ ቃል እንዲቀርጻችሁ እንዲሁም ሌሎችን በምትይዙበት መንገድ ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ፍቀዱ።—ማቴ. 12:1-8

መጽሐፍ ቅዱስን በምታነቡበት ወቅት የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ የሚረዳችሁ ምንድን ነው?

  • የምታነቡትን ነገር ለመረዳት

  • ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማግኘት

  • የአምላክ ቃል እንዲቀርጻችሁ ለመፍቀድ

መዝሙር 95 ብርሃኑ እየደመቀ ነው

a ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ቃሉን በየዕለቱ ለማንበብ ጥረት ያደርጋሉ። ሌሎች ብዙ ሰዎችም መጽሐፍ ቅዱስን ያነብባሉ፤ ሆኖም የሚያነቡትን አይረዱትም። በኢየሱስ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎች ሁኔታም ተመሳሳይ ነበር። ኢየሱስ የአምላክን ቃል ለሚያነቡ ሰዎች የተናገረውን በመመርመር ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን የተሟላ ጥቅም ለማግኘት የሚረዱ ሐሳቦችን ማግኘት እንችላለን።

b ኢየሱስ በተጠመቀበትና በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት ወቅት ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት ስለነበረው ሕይወት ማስታወስ እንደቻለ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል።—ማቴ. 3:16

c ማርያም ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቃ ታውቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከእነሱ ላይ ትጠቅስ ነበር። (ሉቃስ 1:46-55) ዮሴፍና ማርያም የቅዱሳን መጻሕፍትን የግል ቅጂ ለማግኘት አቅማቸው እንደማይፈቅድ መገመት እንችላለን። ስለዚህ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማስታወስ እንዲረዳቸው ሲሉ የአምላክ ቃል በምኩራቦች ውስጥ ሲነበብ በጥንቃቄ አዳምጠው መሆን አለበት።

d የካቲት 1, 2013 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ወደ አምላክ ቅረብ—‘እሱ የሕያዋን አምላክ ነው’” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

e ማቴዎስ 19:4-6 ላይም ኢየሱስ ፈሪሳውያኑን “አላነበባችሁም?” በማለት ጠይቋቸዋል። እነዚህ ሰዎች ስለ ፍጥረት የሚገልጸውን ዘገባ ያነበቡ ቢሆንም ዘገባው አምላክ ለጋብቻ ስላለው አመለካከት የሚያስተምረውን ትምህርት አላስተዋሉም ነበር።

f የሥዕሉ መግለጫ፦ በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በሚደረግ ስብሰባ ላይ ኦዲዮ ቪዲዮ ላይ የሚሠራ አንድ ወንድም ብዙ ስህተት ይሠራል። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ግን ወንድሞች በሠራቸው ስህተቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ለጥረቱ ያመሰግኑታል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ