የጥናት ርዕስ 20
መዝሙር 67 “ቃሉን ስበክ”
በፍቅር ተነሳስታችሁ መስበካችሁን ቀጥሉ!
“አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።”—ማር. 13:10
ዓላማ
ፍቅር በቅንዓትና በሙሉ ልብ በስብከቱ ሥራ እንድንካፈል የሚያነሳሳን እንዴት ነው?
1. በ2023 ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ምን ተምረናል?
በ2023 ዓመታዊ ስብሰባa ላይ በምናምንባቸው ነገሮች ረገድ አስደናቂ ማስተካከያዎች ተደርገዋል፤ በተጨማሪም ከአገልግሎታችን ጋር የተያያዙ አስደሳች ማስታወቂያዎችን ሰምተናል። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላም እንኳ ከይሖዋ ሕዝቦች ጎን የመሰለፍ አጋጣሚ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተምረናል። ከዚህም ሌላ፣ ከኅዳር 2023 አንስቶ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ሁሉንም የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ሪፖርት ማድረግ እንደማይጠበቅባቸው ተገልጿል። እነዚህ ማስተካከያዎች አገልግሎታችን ያለውን አስፈላጊነት ወይም አጣዳፊነት ይቀንሱታል? በፍጹም!
2. ቀን አልፎ ቀን ሲተካ አገልግሎታችን ይበልጥ አጣዳፊ እየሆነ የሚሄደው ለምንድን ነው? (ማርቆስ 13:10)
2 ቀን አልፎ ቀን ሲተካ አገልግሎታችን ይበልጥ አጣዳፊ እየሆነ ይሄዳል። ለምን? ምክንያቱም ጊዜው እያለቀ ነው። ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ስለሚከናወነው የስብከት ሥራ ምን እንዳለ ልብ በል። (ማርቆስ 13:10ን አንብብ።) ማቴዎስ በጻፈው ዘገባ መሠረት ኢየሱስ ምሥራቹ “መጨረሻው” ከመምጣቱ በፊት በመላው ምድር እንደሚሰበክ ተናግሯል። (ማቴ. 24:14) ይህ አገላለጽ፣ የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የሚጠፋበትን ጊዜ ያመለክታል። ይሖዋ በቅርቡ ለሚከሰቱት ክንውኖች “ቀንና ሰዓት” ወስኗል። (ማቴ. 24:36፤ 25:13፤ ሥራ 1:7) እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር ወደዚህ ዕለት እየተጠጋን ነው። (ሮም 13:11) እስከዚያው ግን፣ መጨረሻው እስኪመጣ ድረስ መስበካችንን መቀጠል ይኖርብናል።
3. ለመስበክ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
3 ስለ አገልግሎታችን ስናስብ የሚከተለውን ወሳኝ ጥያቄ መጠየቅ ይኖርብናል፦ ምሥራቹን የምንሰብከው ለምንድን ነው? በቀላል አነጋገር፣ እንድንሰብክ የሚያነሳሳን ፍቅር ነው። የስብከቱ ሥራችን ለምሥራቹ ያለንን ፍቅር፣ ለሰዎች ያለንን ፍቅር፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለይሖዋና ለስሙ ያለንን ፍቅር ያንጸባርቃል። እስቲ እነዚህን ነገሮች አንድ በአንድ እንመልከት።
ለምሥራቹ ያለን ፍቅር ለመስበክ ያነሳሳናል
4. ምሥራች ስንሰማ ምን ይሰማናል?
4 አንድ ምሥራች ስትሰማ ምን ይሰማሃል? ለምሳሌ አንድ የቤተሰብህ አባል ልጅ እንደወለደ ወይም ስትጓጓለት የነበረውን ሥራ እንዳገኘህ ስትሰማ ምን ተሰምቶህ እንደነበር ታስታውሳለህ? ይህን ምሥራች ለቤተሰብህና ለጓደኞችህ ለመናገር እንደጓጓህ ምንም ጥያቄ የለውም። ከሁሉ የላቀውን ዜና ማለትም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በሰማህበት ጊዜስ እንደዚህ ተሰምቶህ ነበር?
5. በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለመጀመሪያ ጊዜ ስትማር ምን ተሰምቶህ ነበር? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
5 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሰማ ምን ተሰምቶህ እንደነበር ለማስታወስ ሞክር። የሰማዩ አባትህ እንደሚወድህ፣ አገልጋዮቹን ያቀፈውን ቤተሰብ እንድትቀላቀል እንደሚፈልግ፣ መከራንና ሥቃይን ለማስወገድ ቃል እንደገባ፣ በሞት ያጣሃቸው ወዳጅ ዘመዶችህ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከሞት ተነስተው ልታገኛቸው እንደምትችል እንዲሁም ሌሎች ብዙ ነገሮችን ተማርክ። (ማር. 10:29, 30፤ ዮሐ. 5:28, 29፤ ሮም 8:38, 39፤ ራእይ 21:3, 4) እነዚህ እውነቶች ልብህን ነኩት። (ሉቃስ 24:32) የተማርከውን ነገር በጣም ስለወደድከው እነዚህን ውድ እውነቶች ለሌሎች ለመንገር ተነሳሳህ።—ከኤርምያስ 20:9 ጋር አወዳድር።
ምሥራቹን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰማንበት ወቅት እነዚያን ውድ እውነቶች ለሌሎች ለመናገር ተነሳስተናል (አንቀጽ 5ን ተመልከት)
6. ከኧርነስትና ከሮዝ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
6 እስቲ አንድ ተሞክሮ እንመልከት። ኧርነስትb የተባለ አንድ ወንድም የአሥር ዓመት ልጅ ሳለ አባቱን በሞት አጣ። ኧርነስት እንዲህ ብሏል፦ “‘ወደ ሰማይ ሄዶ ይሆን? ወይስ ከዚህ በኋላ ጨርሶ ዳግም በሕይወት የመኖር ተስፋ አይኖረውም?’ እያልኩ አስብ ነበር። አባት ባላቸው ልጆች እቀና ነበር።” ኧርነስት ብዙ ጊዜ አባቱ ወደተቀበረበት ቦታ ሄዶ በአባቱ መቃብር ላይ ይንበረከክና “አምላክ ሆይ፣ እባክህ አባቴ ያለበትን ቦታ አሳውቀኝ” ብሎ ይጸልይ ነበር። ኧርነስት አባቱ ከሞተ ከ17 ዓመት ገደማ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ግብዣ ቀረበለት፤ እሱም ግብዣውን በደስታ ተቀበለ። የሞቱ ሰዎች ልክ በከባድ እንቅልፍ ላይ ያሉ ያህል ምንም እንደማያውቁ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት የትንሣኤ ተስፋ እንዳለ እንደሚያስተምር ሲያውቅ በጣም ተደሰተ። (መክ. 9:5, 10፤ ሥራ 24:15) ለረጅም ጊዜ ሲያሳስቡት ለነበሩት ጥያቄዎች በስተ መጨረሻ መልስ አገኘ! ኧርነስት ለሚማረው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከፍተኛ ፍቅር ነበረው። ባለቤቱ ሮዝም አብራው ማጥናት ጀመረች፤ እሷም ለመንግሥቱ መልእክት ፍቅር አደረባት። በ1978 ተጠመቁ። ከፍ አድርገው የሚመለከቷቸውን እውነቶች ለቤተሰቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው እንዲሁም ሰሚ ጆሮ ላለው ሁሉ ይናገሩ ነበር። በዚህም የተነሳ ኧርነስትና ሮዝ ከ70 የሚበልጡ ሰዎች እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ረድተዋል።
7. ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለን ፍቅር በልባችን ውስጥ ሥር ሲሰድ ምን ለማድረግ እንነሳሳለን? (ሉቃስ 6:45)
7 በእርግጥም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያለን ፍቅር በልባችን ውስጥ ሥር ከሰደደ ዝም ማለት አንችልም። (ሉቃስ 6:45ን አንብብ።) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ዓይነት ስሜት ይሰማናል። እነዚህ ደቀ መዛሙርት “ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም” ብለዋል። (ሥራ 4:20) እውነትን በጣም ስለምንወደው በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ልናካፍለው እንፈልጋለን።
ለሰዎች ያለን ፍቅር ለመስበክ ያነሳሳናል
8. ለሰዎች ምሥራቹን ለመናገር የሚያነሳሳን ምንድን ነው? (“ሰዎችን ውደዱ—ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
8 እንደ ይሖዋና እንደ ልጁ እኛም ሰዎችን እንወዳለን። (ምሳሌ 8:31፤ ዮሐ. 3:16) “ያለተስፋና ያለአምላክ” ለሚኖሩ ሰዎች ጥልቅ ርኅራኄ ይሰማናል። (ኤፌ. 2:12) እነዚህ ሰዎች በሚያጋጥሟቸው ችግሮች የተነሳ በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ እንዳሉ ሊቆጠር ይችላል። እኛ ግን ከጉድጓዱ ሊያወጣቸው የሚችል ገመድ አለን፤ እሱም የአምላክ መንግሥት ምሥራች ነው። እንዲህ ላሉት ሰዎች ያለን ፍቅርና ርኅራኄ ምሥራቹን ለእነሱ ለመናገር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል። ይህ ውድ መልእክት ልባቸው በተስፋ እንዲሞላ፣ በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት መምራት እንዲችሉ እንዲሁም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ እንዲኖራቸው ያስችላል።—1 ጢሞ. 6:19
ለሰዎች ያለን ፍቅርና ርኅራኄ ለእነሱ ምሥራቹን ለመናገር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል (አንቀጽ 8ን ተመልከት)
9. የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ምን ማስጠንቀቂያ እንሰጣለን? ለምንስ? (ሕዝቅኤል 33:7, 8)
9 ለሰዎች ያለን ፍቅር እየቀረበ ስላለው የዚህ ክፉ ዓለም መጨረሻ እንድናስጠነቅቃቸውም ያነሳሳናል። (ሕዝቅኤል 33:7, 8ን አንብብ።) ለጎረቤቶቻችን እንዲሁም አማኝ ላልሆኑት ቤተሰቦቻችን እናዝንላቸዋለን። ብዙዎቹ በቅርቡ “ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ” እንደሚመጣ ሳያውቁ የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን ይገፋሉ። (ማቴ. 24:21) በዚያ የፍርድ ወቅት የሚከናወነውን ነገር እንዲያውቁ እንፈልጋለን። የሐሰት ሃይማኖት ይጠፋል፤ እሱን ተከትሎ ደግሞ ይህ ክፉ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። (ራእይ 16:14, 16፤ 17:16, 17፤ 19:11, 19, 20) በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ለማስጠንቀቂያችን ምላሽ በመስጠት ከአሁኑ በንጹሕ አምልኮ አብረውን መካፈል እንዲጀምሩ እንጸልያለን። ይሁንና የምንወዳቸውን ቤተሰቦቻችንን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ይህን ማስጠንቀቂያ ልብ ስለማይሉ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል?
10. ማስጠንቀቂያውን ማሰማታችንን መቀጠላችን አንገብጋቢ የሆነው ለምንድን ነው?
10 ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ የታላቂቱ ባቢሎንን ጥፋት ሲያዩ አቋማቸውን የሚያስተካክሉ ሰዎችን ለማዳን ሊወስን ይችላል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ ማስጠንቀቂያውን ማሰማታችንን መቀጠላችን ይበልጥ አንገብጋቢ ነው ማለት ነው። ይህን ልብ በል፦ አሁን የምንነግራቸው ነገር ወደፊት የሚያስታውሱት ነገር እንዲኖር ያደርጋል። (ከሕዝቅኤል 33:33 ጋር አወዳድር።) ምናልባትም ከእኛ የሰሙትን ማስጠንቀቂያ አስታውሰው ጊዜው ከማለፉ በፊት በንጹሕ አምልኮ አብረውን ለመካፈል ይነሳሱ ይሆናል። በፊልጵስዩስ የነበረው የእስር ቤት ጠባቂ አመለካከቱን የቀየረው “ከባድ የምድር ነውጥ” ከተከሰተ በኋላ እንደነበረ ሁሉ አሁን ምላሽ የማይሰጡ አንዳንድ ሰዎች ምድርን የሚያናውጥ ክንውን ከሆነው ከታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት በኋላ አመለካከታቸውን ይቀይሩ ይሆናል።—ሥራ 16:25-34
ለይሖዋና ለስሙ ያለን ፍቅር ለመስበክ ያነሳሳናል
11. ለይሖዋ ግርማ፣ ክብርና ኃይል የምንሰጠው እንዴት ነው? (ራእይ 4:11) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
11 ምሥራቹን ለመስበክ የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት ለይሖዋ አምላክና ለቅዱስ ስሙ ያለን ፍቅር ነው። አገልግሎታችንን የምንወደውን አምላክ ለማወደስ እንደሚያስችለን አጋጣሚ አድርገን እንመለከተዋለን። (ራእይ 4:11ን አንብብ።) ይሖዋ አምላክ ከታማኝ አገልጋዮቹ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ሊቀበል እንደሚገባው በሙሉ ልባችን እንስማማለን። እሱ ‘ሁሉንም ነገሮች እንደፈጠረ’ እንዲሁም በሕይወት ልንኖር የቻልነው በእሱ የተነሳ እንደሆነ የሚያሳየውን አሳማኝ ማስረጃ ለሰዎች በመናገር ግርማና ክብር እንሰጠዋለን። ሁኔታችን በፈቀደልን መጠን ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ገንዘባችንን ተጠቅመን በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ስናደርግ ኃይላችንን እንሰጠዋለን። (ማቴ. 6:33፤ ሉቃስ 13:24፤ ቆላ. 3:23) በአጭር አነጋገር፣ ስለምንወደው አምላክ መናገር ያስደስተናል። በተጨማሪም ስለ ስሙ እና ስሙ ስለሚወክለው አካል ለሌሎች ለመናገር እንገፋፋለን። ለምን?
ሁኔታችን በፈቀደልን መጠን ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ገንዘባችንን ተጠቅመን በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ በማድረግ ለይሖዋ ኃይላችንን እንሰጠዋለን (አንቀጽ 11ን ተመልከት)
12. በአገልግሎታችን የይሖዋን ስም የምናስቀድሰው እንዴት ነው?
12 ለይሖዋ ያለን ፍቅር ስሙን ለማስቀደስ ያነሳሳናል። (ማቴ. 6:9) ስሙ በሰይጣን መርዘኛ ውሸቶች የተነሳ ከተሰነዘረበት ነቀፋ ነፃ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንፈልጋለን። (ዘፍ. 3:1-5፤ ኢዮብ 2:4፤ ዮሐ. 8:44) በአገልግሎታችን ሰሚ ጆሮ ላላቸው ሁሉ ስለ አምላካችን እውነቱን በመናገር ለእሱ ጥብቅና ለመቆም እንጓጓለን። አምላክ ዋነኛ ባሕርይው ፍቅር እንደሆነ፣ አገዛዙ ጽድቅና ፍትሕ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ እንዲሁም መንግሥቱ በቅርቡ መከራን ሁሉ አስወግዶ ለመላው የሰው ዘር ሰላምና ደስታ እንደሚያሰፍን ሁሉም ሰው እንዲያውቅ እንፈልጋለን። (መዝ. 37:10, 11, 29፤ 1 ዮሐ. 4:8) በአገልግሎታችን ለይሖዋ ጥብቅና በመቆም ስሙን እናስቀድሰዋለን። ከዚህም ሌላ፣ እንደ ስማችን እየኖርን መሆኑን ማወቃችን ያስደስተናል። እንዴት?
13. የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን መጠራታችን የሚያኮራን ለምንድን ነው? (ኢሳይያስ 43:10-12)
13 ይሖዋ ‘ምሥክሮቹ’ እንድንሆን መርጦናል። (ኢሳይያስ 43:10-12ን አንብብ።) ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከበላይ አካሉ የተላከ አንድ ደብዳቤ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ማንኛችንም ልናገኘው ከምንችለው ክብር ሁሉ እጅግ የላቀው የይሖዋ ምሥክር ተብለን መጠራታችን ነው።”c እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት። ፍርድ ቤት ቀርቦ አንተ ምን ዓይነት ሰው እንደሆንክ የሚመሠክርልህ ሰው ብትፈልግ የምታውቀውና የምታምነው እንዲሁም መልካም ስም በማትረፉ ተአማኒነት ያለው ምሥክርነት ሊሰጥ የሚችል ሰው እንደምትመርጥ የታወቀ ነው። ይሖዋ ምሥክሮቹ እንድንሆን የመረጠን መሆኑ በደንብ እንደሚያውቀን እንዲሁም እሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ መሆኑን እንድንመሠክር እንደሚተማመንብን ያሳያል። የእሱ ምሥክር መሆናችን በጣም ስለሚያኮራን ስሙን ለማሳወቅ እንዲሁም ስለ እሱ የተነገሩትን በርካታ ውሸቶች ለማጋለጥ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በሙሉ እንጠቀምባቸዋለን። እንዲህ በማድረግ “የይሖዋ ምሥክሮች” የሚለውን የምንኮራበትን መጠሪያችንን በሚመጥን መንገድ እንመላለሳለን!—መዝ. 83:18፤ ሮም 10:13-15
እስከ መጨረሻው መስበካችንን እንቀጥላለን
14. ከፊታችን የትኞቹ አስደናቂ ነገሮች ይጠብቁናል?
14 ከፊታችን አስደናቂ ነገሮች ይጠብቁናል! በይሖዋ እርዳታ፣ ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ሌሎች ብዙ ሰዎች እውነትን እንደሚቀበሉ ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህም ሌላ፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ እጅግ ጨለማ ጊዜ በሆነው በታላቁ መከራ ወቅትም አንዳንድ ሰዎች ለመጥፋት ከተቃረበው የሰይጣን ዓለም ወጥተው አብረውን ይሖዋን ማወደስ ሊጀምሩ እንደሚችሉ በማወቃችን በጣም ተደስተናል!—ሥራ 13:48
15-16. ምን ማድረጋችንን እንቀጥላለን? እስከ መቼ?
15 እስከዚያው ድረስ ግን ማከናወን ያለብን ሥራ አለ። መቼም ቢሆን በማይደገመው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመላው ምድር የመስበኩ ሥራ የመካፈል መብት አግኝተናል። ከዚህም ሌላ ማስጠንቀቂያውን ማሰማታችንን መቀጠል ይኖርብናል። ሰዎች የዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ በፍጥነት እየቀረበ መሆኑን ማወቅ አለባቸው። አሁን ማስጠንቀቂያውን ካሰማን ያ የፍርድ ጊዜ ሲመጣ ሰዎች ስንሰብክ የነበረው መልእክት ከይሖዋ አምላክ የመጣ መሆኑን ይገነዘባሉ።—ሕዝ. 38:23
16 እንግዲያው ቁርጥ ውሳኔያችን ምንድን ነው? ለምሥራቹ ባለን ፍቅር፣ ለሰዎች ባለን ፍቅር፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለይሖዋ አምላክና ለስሙ ባለን ፍቅር ተነሳስተን ምሥራቹን ይሖዋ “በቃ” እስኪል ድረስ በጉጉት፣ በጥድፊያ ስሜትና በቅንዓት መስበካችንን እንቀጥላለን!
መዝሙር 54 “መንገዱ ይህ ነው”
a ዓመታዊ ስብሰባው ጥቅምት 7, 2023 በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኒውበርግ የይሖዋ ምሥክሮች የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ተካሂዶ ነበር። ሙሉው ስብሰባ ከጊዜ በኋላ JW ብሮድካስቲንግ ላይ ወጥቷል፤ ክፍል 1 የወጣው ኅዳር 2023 ሲሆን ክፍል 2 የወጣው ደግሞ ጥር 2024 ነበር።
b በየካቲት 1, 2015 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ግልጽና አሳማኝ መልስ አስደነቀኝ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c የመጋቢት 2007 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 3ን ተመልከት።