የጥናት ርዕስ 40
መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ
ይሖዋ “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል”
“የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል፤ ቁስላቸውን ይፈውሳል።”—መዝ. 147:3
ዓላማ
ይሖዋ የስሜት ቁስል ለደረሰባቸው አገልጋዮቹ በጥልቅ ያስባል። ይህ ርዕስ፣ ይሖዋ የሚያጽናናን እንዲሁም ሌሎችን እንድናጽናና የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
1. ይሖዋ ስለ አገልጋዮቹ ምን ይሰማዋል?
ይሖዋ ምድር ላይ ያሉ አገልጋዮቹን ሲመለከት ምን ነገሮችን ያስተውላል? ስንደሰትና ስናዝን ይመለከታል። (መዝ. 37:18) ከስሜት ሥቃይ ጋር እየታገልንም እንኳ አቅማችን በፈቀደ መጠን እያገለገልነው እንደሆነ ሲያይ በጣም ይደሰታል። ከዚህም በተጨማሪ ሊደግፈንና ሊያጽናናን ይጓጓል።
2. ይሖዋ የተሰበረ ልብ ላላቸው ሰዎች ምን ያደርግላቸዋል? ከእንክብካቤው መጠቀም የሚችሉትስ እንዴት ነው?
2 መዝሙር 147:3 ይሖዋ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ሰዎች ‘ቁስል እንደሚፈውስ’ ይገልጻል። እዚህ ጥቅስ ላይ፣ ይሖዋ የስሜት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በርኅራኄ እንደሚንከባከብ ተገልጿል። ከይሖዋ እንክብካቤ ለመጠቀም ምን ማድረግ ይኖርብናል? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ጥሩ ችሎታ ያለው ሐኪም የአንድ ሰው ቁስል እንዲድን መርዳት ይችላል። ሆኖም ጉዳት የደረሰበት ሰው መዳን ከፈለገ የሐኪሙን መመሪያ በጥንቃቄ መከተል አለበት። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የስሜት ሥቃይ ለደረሰባቸው ሰዎች ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ምን ምክር እንደሚሰጣቸው እንዲሁም ይህን ፍቅራዊ ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
ይሖዋ በእሱ ዘንድ ያለንን ዋጋ ያስታውሰናል
3. አንዳንዶች ዋጋ ቢስ እንደሆኑ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?
3 የምንኖረው ፍቅር በጠፋበት ዓለም ውስጥ ነው። በዚህም የተነሳ ብዙዎች የዋጋ ቢስነት ስሜት ይሰማቸዋል። ሄለንa የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ያደግኩት ፍቅር በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቴ ዓመፀኛ ሰው ነበር። ምንም እንደማንረባ በየቀኑ ይነግረናል።” ምናልባት አንተም እንደ ሄለን ግፍ ተፈጽሞብህ፣ በተደጋጋሚ ትችት ተሰንዝሮብህ ወይም ሰዎች ዋጋ ቢስ እንደሆንክ እንዲሰማህ አድርገውህ ሊሆን ይችላል። በዚህም የተነሳ ማንም ሰው ከልቡ እንደማያስብልህ ይሰማህ ይሆናል።
4. በመዝሙር 34:18 ላይ ይሖዋ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?
4 ሌሎች ዝቅ አድርገው ቢመለከቱህም እንኳ ይሖዋ እንደሚወድህና ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥህ ልትተማመን ትችላለህ። እሱ “ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው።” (መዝሙር 34:18ን አንብብ።) ‘መንፈስህ ሲደቆስብህ’ ይሖዋ በልብህ ውስጥ መልካም ነገር አይቶ በግለሰብ ደረጃ ወደ ራሱ እንደሳበህ አስታውስ። (ዮሐ. 6:44) በእሱ ዘንድ ውድ ስለሆንክ ምንጊዜም ሊረዳህ ዝግጁ ነው።
5. ኢየሱስ በሌሎች የተናቁ ሰዎችን ከያዘበት መንገድ ምን እንማራለን?
5 የኢየሱስን ምሳሌ በመመርመር ስለ ይሖዋ ስሜት መማር እንችላለን። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሌሎች ዝቅ አድርገው ለሚመለከቷቸው ሰዎች ትኩረት ሰጥቷል፤ እንዲሁም በርኅራኄ ይዟቸዋል። (ማቴ. 9:9-12) አንዲት ሴት ካለባት የሚያሠቃይ ሕመም ለመፈወስ ብላ ልብሱን በነካች ጊዜ ኢየሱስ አጽናንቷታል፤ እምነት በማሳየቷም አድንቋታል። (ማር. 5:25-34) ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) በመሆኑም ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከትህ እንዲሁም እምነትህንና ለእሱ ያለህን ፍቅር ጨምሮ ያሉህን መልካም ባሕርያት እንደሚያስተውል መተማመን ትችላለህ።
6. አንድ ሰው የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማው ከሆነ ምን ማድረግ ይችላል?
6 ብዙ ጊዜ የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? በይሖዋ ዘንድ ያለህን ዋጋ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አንብብ፤ እንዲሁም አሰላስልባቸው።b (መዝ. 94:19) አንድ ግብ ላይ መድረስ ወይም የሌሎችን ያህል መሥራት ባለመቻልህ ተስፋ ከቆረጥክ ማከናወን ባልቻልከው ነገር ላይ አታተኩር። ይሖዋ ከአንተ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነው። (መዝ. 103:13, 14) አካላዊ፣ ስሜታዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት ደርሶብህ ከሆነ ለደረሰብህ ነገር ራስህን አትውቀስ። ጥፋተኛው አንተ አይደለህም! ይሖዋ ተጠያቂ የሚያደርገው ጥፋተኞችን እንጂ ተበዳዮችን አይደለም። (1 ጴጥ. 3:12) በልጅነቷ ጥቃት ተፈጽሞባት የነበረችው ሳንድራ እንዲህ ብላለች፦ “ለራሴ ሚዛናዊ አመለካከት ማለትም የእሱን ዓይነት አመለካከት ለማዳበር እንዲረዳኝ ይሖዋን አዘውትሬ እጠይቀዋለሁ።”
7. በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙን ነገሮች ከይሖዋ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሊጠቅሙን የሚችሉት እንዴት ነው?
7 ይሖዋ ሌሎችን ለመርዳት ሊጠቀምብህ እንደሚችል አትጠራጠር። በክርስቲያናዊ አገልግሎት ከእሱ ጋር አብረህ እንድትሠራ በመጋበዝ አክብሮሃል። (1 ቆሮ. 3:9) በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠመህ ነገር ለሌሎች አዘኔታ እንድታዳብርና ስሜታቸውን እንድትረዳ እንዳስቻለህ ምንም ጥያቄ የለውም። ስለዚህ እነሱን መርዳት ትችላለህ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሄለን እርዳታ ካገኘች በኋላ እሷም ሌሎችን መርዳት ችላለች። እንዲህ ብላለች፦ “የዋጋ ቢስነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። አሁን ግን ይሖዋ እንደምወደድና ጠቃሚ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርጓል።” ሄለን በአሁኑ ጊዜ የዘወትር አቅኚ ሆና በደስታ እያገለገለች ነው።
ይሖዋ ይቅርታውን እንድንቀበል ይፈልጋል
8. ኢሳይያስ 1:18 ላይ ምን ዋስትና እናገኛለን?
8 አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ከመጠመቃቸው በፊት ወይም ከተጠመቁ በኋላ በፈጸሙት ድርጊት የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃያሉ። ይሁንና ይሖዋ በጣም ስለሚወደን ቤዛውን እንዳዘጋጀልን ማስታወስ አለብን። ስለዚህ ስጦታውን እንድንቀበል እንደሚፈልግ ጥያቄ የለውም። ይሖዋ በእኛና በእሱ ‘መካከል የተፈጠረውን ችግር ከፈታን’c በኋላ በኃጢአታችን እንደማይጠይቀን ቃል ገብቶልናል። (ኢሳይያስ 1:18ን አንብብ።) ይሖዋ ቀደም ሲል የፈጸምናቸውን ኃጢአቶች መርሳቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያሳያል! በሌላ በኩል ደግሞ የሠራነውን መልካም ነገር አይረሳም።—መዝ. 103:9, 12፤ ዕብ. 6:10
9. ካለፈው ጊዜ ይልቅ በአሁኑና በወደፊቱ ጊዜ ላይ ለማተኮር ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
9 ቀደም ሲል የፈጸምከው ነገር የሚጸጽትህ ከሆነ ባለፈው ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ በአሁኑና በወደፊቱ ጊዜ ላይ ለማተኮር ሞክር። የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ክፉኛ በማሳደዱ ተጸጽቶ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ ይቅር እንዳለው ያውቃል። (1 ጢሞ. 1:12-15) ታዲያ ቀደም ሲል በሠራው ኃጢአት መብሰልሰሉን ቀጥሏል? እንዲህ እንዳላደረገ ምንም ጥያቄ የለውም። በአይሁድ እምነት ያገኛቸውን ስኬቶች እንዳላስታወሰ ሁሉ በዚህም ነገር ላይ እንዳላተኮረ ግልጽ ነው። (ፊልጵ. 3:4-8, 13-15) ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ አገልግሎቱን በቅንዓት አከናውኗል፤ እንዲሁም በወደፊቱ ጊዜ ላይ አተኩሯል። እንደ ጳውሎስ ሁሉ አንተም ያለፈውን መቀየር አትችልም። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ አቅምህ በፈቀደ መጠን ይሖዋን ማስከበር እንዲሁም ወደፊት ቃል የገባልህን አስደሳች ጊዜ በተስፋ መጠባበቅ ትችላለህ።
10. ቀደም ሲል በፈጸምነው ድርጊት የተነሳ ሌሎች ተጎድተው ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን?
10 ቀደም ሲል የፈጸምከው ስህተት ሌሎችን በመጉዳቱ የተነሳ ትረበሽ ይሆናል። ታዲያ ምን ሊረዳህ ይችላል? የተፈጠረውን ችግር ለማስተካከል አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ሞክር፤ ይህም ከልብ ይቅርታ መጠየቅን ይጨምራል። (2 ቆሮ. 7:11) ይሖዋ የጎዳሃቸውን ሰዎች እንዲረዳቸው በጸሎት ጠይቀው። ይሖዋ፣ አንተም ሆንክ የጎዳሃቸው ሰዎች እንድትጸኑና ሰላማችሁ እንዲመለስላችሁ ሊረዳችሁ ይችላል።
11. ከነቢዩ ዮናስ ምሳሌ ምን እንማራለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 ካለፈው ስህተትህ ተማር፤ እንዲሁም ይሖዋ በመረጠው መንገድ እንዲጠቀምብህ ፈቃደኛ ሁን። ነቢዩ ዮናስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዮናስ፣ አምላክ ባዘዘው መሠረት ወደ ነነዌ ከመሄድ ይልቅ ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ሸሸ። ይሖዋ ለዮናስ ተግሣጽ ሰጥቶታል፤ እሱም ከስህተቱ ተምሯል። (ዮናስ 1:1-4, 15-17፤ 2:7-10) ይሖዋ በዮናስ ላይ ተስፋ አልቆረጠበትም። ወደ ነነዌ የሚሄድበት ሌላ አጋጣሚ ሰጠው። ዮናስም ወዲያውኑ ታዘዘ። ቀደም ሲል በሠራው ስህተት የተነሳ የተሰማው ጸጸት ይሖዋ የሰጠውን ኃላፊነት ከመቀበል እንዲያግደው አልፈቀደም።—ዮናስ 3:1-3
ነቢዩ ዮናስ ከዓሣው ሆድ ውስጥ ከወጣ በኋላ ይሖዋ ወደ ነነዌ ሄዶ መልእክቱን እንዲያውጅ በድጋሚ ላከው (አንቀጽ 11ን ተመልከት)
ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ያጽናናናል
12. አስከፊ መከራ ወይም ሐዘን ሲደርስብን ይሖዋ ሰላም የሚሰጠን እንዴት ነው? (ፊልጵስዩስ 4:6, 7)
12 አስከፊ መከራ ወይም ሐዘን ሲደርስብን ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ያጽናናናል። ሮን እና ካሮል ያጋጠማቸውን ነገር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ልጃቸው ራሱን ባጠፋበት ወቅት ከባድ ሐዘን ገጥሟቸው ነበር። እንዲህ ብለዋል፦ “ከዚህ ቀደም ብዙ መከራዎች አጋጥመውናል። ይሄኛው ግን ከሁሉም የከፋው ነው። እንቅልፍ አጥተን ባደርንባቸው ብዙ ሌሊቶች ወደ ይሖዋ እንጸልይ ነበር፤ በዚያ ወቅት በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የተጠቀሰውን ሰላም በእርግጥ ማጣጣም ችለናል።” (ጥቅሱን አንብብ።) ልብ የሚሰብር መከራ አጋጥሞህ ከሆነ በማንኛውም ጊዜ እንዲሁም ለፈለግከው ያህል ሰዓት ወደ ይሖዋ መጸለይ ትችላለህ። (መዝ. 86:3፤ 88:1) ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ በተደጋጋሚ ጠይቀው። እሱ ጥያቄህን ፈጽሞ ችላ አይልም።—ሉቃስ 11:9-13
13. መንፈስ ቅዱስ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን እንድንቀጥል የሚረዳን እንዴት ነው? (ኤፌሶን 3:16)
13 የደረሰብህ ከባድ ፈተና አቅምህን አሟጦታል? መንፈስ ቅዱስ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገልህን እንድትቀጥል ኃይል ሊሰጥህ ይችላል። (ኤፌሶን 3:16ን አንብብ።) ፍሎራ የተባለች እህት ያጋጠማትን ነገር እስቲ እንመልከት። እሷና ባለቤቷ በሚስዮናዊነት ያገለግሉ ነበር። በዚህ ወቅት ባለቤቷ ምንዝር በመፈጸሙ ምክንያት ተፋቱ። እንዲህ ብላለች፦ “በፈጸመብኝ ክህደት የተነሳ የተሰማኝ ሐዘን አእምሮዬን ተቆጣጠረው። ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለመጽናት እንዲረዳኝ ጸለይኩ። ሁኔታው ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ ለማገገምና ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ሰጥቶኛል።” ፍሎራ፣ አምላክ በእሱ ይበልጥ እንድትተማመን እንደረዳት ይሰማታል፤ ወደፊትም ቢሆን ከጎኗ እንደማይለይ እርግጠኛ ነች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “በመዝሙር 119:32 ላይ የሚገኙት ቃላት እውነት መሆናቸውን በሕይወቴ ተመልክቻለሁ፦ ‘በልቤ ውስጥ ቦታ ስለሰጠኸው፣ የትእዛዛትህን መንገድ በጉጉት እከተላለሁ።’”
14. የአምላክ መንፈስ በእኛ ላይ እንዲሠራ መፍቀድ የምንችለው እንዴት ነው?
14 መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ካቀረብከው ልመና ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ የምትችለው እንዴት ነው? የአምላክ መንፈስ በአንተ ላይ እንዲሠራ በሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ተካፈል። ይህም በስብሰባዎች ላይ መገኘትንና ለሌሎች መስበክን ይጨምራል። በየዕለቱ የይሖዋን ቃል በማንበብ አእምሮህ በእሱ ሐሳቦች እንዲሞላ አድርግ። (ፊልጵ. 4:8, 9) ቃሉን ስታነብ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች መከራ ባጋጠማቸው ወቅት ይሖዋ እንዲጸኑ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሳንድራ በተደጋጋሚ ከባድ መከራ ደርሶባት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የዮሴፍ ታሪክ ልቤን ይነካዋል። የደረሰበት መከራና ግፍ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና እንዲያበላሽበት አልፈቀደም።”—ዘፍ. 39:21-23
ይሖዋ በእምነት አጋሮቻችን አማካኝነት ያጽናናናል
15. ከእነማን ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን? ሊረዱን የሚችሉትስ እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
15 መከራ ሲደርስብን የእምነት አጋሮቻችን ‘በእጅጉ ሊያጽናኑን’ ይችላሉ። (ቆላ. 4:11 ግርጌ) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የይሖዋ ፍቅር መገለጫዎች ናቸው። የእምነት አጋሮቻችን በጥሞና በማዳመጥ ወይም አብረውን በመሆን ሊያጽናኑን ይችላሉ። የሚያበረታታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሊያነቡልን ወይም አብረውን ሊጸልዩ ይችላሉ።d (ሮም 15:4) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የይሖዋን አስተሳሰብ እንድናስታውስ በማድረግ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ሊረዱን ይችላሉ። የእምነት አጋሮቻችን ተግባራዊ እርዳታ ሊሰጡንም ይችላሉ፤ ለምሳሌ በተጨነቅንበት ወቅት ምግብ ያመጡልን ይሆናል።
እምነት የሚጣልባቸው የጎለመሱ ወዳጆቻችን ከፍተኛ ድጋፍና ማጽናኛ ሊሰጡን ይችላሉ (አንቀጽ 15ን ተመልከት)
16. ከሌሎች እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 ከሌሎች እርዳታ ማግኘት ከፈለግን እርዳታቸውን መጠየቅ ሊያስፈልገን ይችላል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስለሚወዱን እኛን መርዳት ይፈልጋሉ። (ምሳሌ 17:17) ሆኖም ምን እንደሚሰማን አሊያም ምን እንደሚያስፈልገን ላያውቁ ይችላሉ። (ምሳሌ 14:10) ጭንቀት ካጋጠመህ የሚሰማህን ነገር ለጎለመሱ ወዳጆችህ ለመናገር ፈቃደኛ ሁን። በምን መንገድ ሊረዱህ እንደሚችሉ ንገራቸው። የምትቀርባቸውን አንድ ወይም ሁለት ሽማግሌዎች ማነጋገር ትችላለህ። አንዳንድ እህቶች ለጎለመሰች እህት ስሜታቸውን አውጥተው መናገራቸው አጽናንቷቸዋል።
17. ማበረታቻ እንዳናገኝ እንቅፋት ሊሆኑብን የሚችሉ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው? ልንወጣቸው የምንችለውስ እንዴት ነው?
17 ራስህን አታግልል። ባለብህ የስሜት ሥቃይ የተነሳ ከሌሎች ጋር ጊዜ የማሳለፍ ፍላጎት ላይኖርህ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የእምነት አጋሮችህ ስሜትህን ላይረዱልህ ወይም ደግሞ ሳያስቡት በንግግራቸው ሊጎዱህ ይችላሉ። (ያዕ. 3:2) እንዲህ ያሉት ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚያስፈልግህን ማበረታቻ ከማግኘት እንዲያግዱህ አትፍቀድ። ከመንፈስ ጭንቀት ጋር የሚታገል ጋቪን የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ ከጓደኞቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍ አያሰኘኝም።” ያም ቢሆን ጋቪን ስሜቱ ተጽዕኖ እንዲያደርግበት ከመፍቀድ ይልቅ ከወዳጆቹ ጋር ጊዜ ያሳልፋል፤ ይህም በጣም ጠቅሞታል። ኤሚ የተባለች እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ቀደም ሲል ባጋጠሙኝ ነገሮች የተነሳ ሰዎችን ማመን ይከብደኛል። ሆኖም እንደ ይሖዋ ወንድሞቼንና እህቶቼን ለመውደድና እነሱን ለማመን ጥረት እያደረግኩ ነው። ይህ ይሖዋን እንደሚያስደስተው አውቃለሁ፤ እኔንም ያስደስተኛል።”
ይሖዋ የሰጠን ተስፋ ያጽናናናል
18. የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ የምንችለው ለምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜስ ምን ማድረግ እንችላለን?
18 ይሖዋ በቅርቡ ከሁሉም ዓይነት አካላዊና ስሜታዊ ሥቃይ እንደሚፈውሰን ስለምናውቅ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን። (ራእይ 21:3, 4) በአሁኑ ጊዜ ስሜታችንን የጎዱት ነገሮች ያኔ “ወደ ልብም አይገቡም።” (ኢሳ. 65:17) እስካሁን እንደተመለከትነው ይሖዋ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ‘ቁስላችንን ይፈውሳል።’ ይሖዋ አንተን ለመርዳትና ለማጽናናት በፍቅር ተነሳስቶ ባደረጋቸው ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቀም። ‘እሱ እንደሚያስብልህ’ ለአፍታም እንኳ አትጠራጠር።—1 ጴጥ. 5:7
መዝሙር 7 ይሖዋ ኃይላችን
a ስሞቹ ተቀይረዋል።
b “ይሖዋ አንተን ከፍ አድርጎ ይመለከትሃል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
c በእኛና በይሖዋ ‘መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት’ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን በመጠየቅና ምግባራችንን በማስተካከል ንስሐ መግባታችንን ማሳየት ይኖርብናል። ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታም መጠየቅ ይኖርብናል።—ያዕ. 5:14, 15