የሕይወት ታሪክ
“ውጊያው የይሖዋ ነው”
ዕለቱ ጥር 28, 2010 ነበር፤ በዚያ ቀዝቃዛ ቀን ውብ በሆነችው የፈረንሳይ ከተማ በስትራስበርግ ነበርኩ። ሆኖም እዚያ የሄድኩት አገር ለመጎብኘት አይደለም። እዚያ የሄድኩት በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ፊት ለይሖዋ ምሥክሮች ጥብቅና ለመቆም ከተመደበው ቡድን ጋር ነበር። የተነሳው ጉዳይ፣ የፈረንሳይ መንግሥት 64 ሚሊዮን ዩሮ (89,000,000 የአሜሪካ ዶላር) የሚያህል እጅግ ከፍተኛ ግብር በወንድሞቻችን ላይ መጣሉ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋ ስም፣ የሕዝቡ መልካም ስም እንዲሁም የአምልኮ ነፃነታቸው ጥያቄ ላይ ወድቆ ነበር። በዚያ ችሎት ላይ ያጋጠመን ነገር ‘ውጊያው የይሖዋ እንደሆነ’ አረጋግጦልናል። (1 ሳሙ. 17:47) እስቲ ታሪኩን ልንገራችሁ።
ክርክሩ የጀመረው በ1990ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነው፤ በዚህ ወቅት የፈረንሳይ መንግሥት የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ ከ1993 እስከ 1996 ባሉት ዓመታት ባገኘው መዋጮ ላይ አግባብነት የሌለው ግብር ጣለ። ፈረንሳይ ካሉ ፍርድ ቤቶች ፍትሕ ለማግኘት ብንሞክርም አልተሳካልንም። በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ከተሸነፍን በኋላ መንግሥት ከፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ የባንክ ሒሳብ ከአራት ሚሊዮን ተኩል ዩሮ (6,300,000 የአሜሪካ ዶላር) በላይ ወረሰ። የመጨረሻ ተስፋችን የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ነበር። ሆኖም ፍርድ ቤቱ በክርክሩ ላይ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት እኛና የመንግሥት ጠበቆች በፍርድ ቤቱ ተወካይ ፊት ተደራድረን ስምምነት ላይ ለመድረስ እንድንሞክር ጠየቀን።
የፍርድ ቤቱ ተወካይ ከተጠየቅነው ገንዘብ ውስጥ የተወሰነውን ለመክፈል በመስማማት ለጉዳዩ እልባት እንድንሰጥ ጫና እንደምታደርግብን አስበን ነበር። ሆኖም አንድ ዩሮ እንኳ መክፈል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መጣስ እንደሚሆን ተገንዝበን ነበር። ወንድሞችና እህቶች መዋጮ ያደረጉት የአምላክን መንግሥት ጉዳዮች ለመደገፍ ስለሆነ መዋጮአቸው የመንግሥት ንብረት አይደለም። (ማቴ. 22:21) ያም ቢሆን፣ ለፍርድ ቤቱ ደንብ ያለንን አክብሮት ለማሳየት በድርድሩ ላይ ተገኘን።
የሕግ ቡድናችን በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ፊት ቆሞ፣ 2010
ግርማ ሞገስ ከተላበሱት የፍርድ ቤቱ አዳራሾች በአንዱ ተሰበሰብን። አጀማመሩ ጥሩ አልነበረም። ተወካይዋ በመክፈቻ ሐሳቧ ላይ በፈረንሳይ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከተጣለባቸው ግብር የተወሰነውን መክፈል አለባቸው ብላ እንደምታምን ተናገረች። በዚህ ጊዜ እንዲህ ብለን ለመጠየቅ ውስጣችን ገፋፋን፦ “መንግሥት ቀድሞውንም ከባንክ ሒሳባችን ከአራት ሚሊዮን ተኩል ዩሮ በላይ መውረሱን አውቀሻል?”
በዚህ ጊዜ በጣም ደነገጠች። የመንግሥት ጠበቆች የፈረንሳይ መንግሥት ይህን ማድረጉን ሲያረጋግጡላት ለጉዳዩ ያላት አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። ጠበቆቹን ከወቀሰቻቸው በኋላ ስብሰባውን ወዲያውኑ ደመደመችው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ፈጽሞ ባልጠበቅነው መንገድ የፍርድ ሂደቱን አቅጣጫ እንደለወጠው ተገነዘብኩ። የሆነውን ነገር ማመን አቃተን። ከስብሰባው የወጣነው በጣም ተደስተን ነው።
ሰኔ 30, 2011 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በሙሉ ድምፅ ፈረደልን። መንግሥት የጣለብንን ግብር እንዲሰርዝና የወሰደውን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲመልስ ትእዛዝ ሰጠ። ይህ ታሪካዊ ብይን እስካሁን ድረስ ፈረንሳይ ውስጥ ንጹሕ አምልኮ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል። ሳንዘጋጅበት የጠየቅነው ያ አንድ ጥያቄ በጎልያድ ግንባር ውስጥ እንደተቀረቀረው ድንጋይ የክርክሩን አቅጣጫ ቀይሮታል። ድል ያገኘነው ለምንድን ነው? ዳዊት ለጎልያድ እንደነገረው ‘ውጊያው የይሖዋ ስለሆነ’ ነው።—1 ሳሙ. 17:45-47
ያገኘነው ድል ይህ ብቻ አይደለም። ከሃይማኖታዊና ከፖለቲካዊ መሪዎች ከባድ ተቃውሞ ቢኖርም እስካሁን ድረስ በ70 አገራት የሚገኙ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ከ1,225 ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈርደዋል። እነዚህ ድሎች መሠረታዊ መብቶቻችንን ያስከብራሉ፤ ይህም እንደ ሃይማኖት ሕጋዊ እውቅና የማግኘት መብታችንን፣ በሕዝባዊ አገልግሎት የመካፈል መብታችንን፣ ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች ያለመካፈል መብታችንን እንዲሁም ደም ያለመውሰድ መብታችንን ያካትታል።
በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት እያገለገልኩ አውሮፓ ውስጥ በተካሄደ የፍርድ ሂደት የተካፈልኩት እንዴት ነው?
ቀናተኛ ሚስዮናውያን ቀርጸውኛል
ወላጆቼ ጆርጅ እና ሉሲል ከጊልያድ ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍል የተመረቁ ሲሆን እኔ በ1956 ስወለድ በኢትዮጵያ እያገለገሉ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኖረው በወንጌላዊው ፊልጶስ ስም “ፊሊፕ” ብለው ሰየሙኝ። (ሥራ 21:8) በቀጣዩ ዓመት መንግሥት ሥራችንን አገደ። በወቅቱ ገና ሕፃን የነበርኩ ቢሆንም ቤተሰቦቼ በድብቅ አምልኳቸውን ሲያከናውኑ በደንብ ትዝ ይለኛል። ልጅ ስለነበርኩ ሁኔታው ያስደስተኝ ነበር። የሚያሳዝነው በ1960 ባለሥልጣናቱ ከአገሪቱ አባረሩን።
ናታን ኖር (በስተ ግራ) በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ቤተሰባችንን ሲጎበኝ፣ 1959
ቤተሰባችን ወደ ዊቺታ፣ ካንሳስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ተዛውሮ መኖር ጀመረ። በዚህ ጊዜም ወላጆቼ ሚስዮናውያን ሳሉ የነበራቸው ቅንዓት አልጠፋም። ወላጆቼ ለእውነት ከፍተኛ ፍቅር ነበራቸው። በእኔ፣ በታላቅ እህቴ በጁዲና በታናሽ ወንድሜ በሌስሊ ውስጥም መንፈሳዊ እሴቶችን ቀርጸውብናል። ወንድሜም ሆነ እህቴ የተወለዱት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። በ13 ዓመቴ ተጠመቅኩ። ከሦስት ዓመት በኋላ ቤተሰባችን ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ወደ አሬኪፓ፣ ፔሩ ተዛወረ።
በ1974 ገና የ18 ዓመት ወጣት ሳለሁ የፔሩ ቅርንጫፍ ቢሮ እኔንና አራት ሌሎች ወንድሞችን በልዩ አቅኚነት እንድናገለግል መደበን። የተመደብነው በአንዲስ ተራራ ጫፍ በሚገኙ ያልተነኩ ክልሎች እንድናገለግል ነው። ይህም ቀደምት የአገሬው ተወላጆች ለሆኑት ለኬችዋ እና ለአይማራ ማኅበረሰቦች መስበክን ይጨምራል። የምንኖረው መኪናችን ውስጥ ነበር። መኪናው የሣጥን ቅርጽ ስለነበረው “የኖኅ መርከብ” ብለን እንጠራው ነበር። ለቀደምት የአገሬው ተወላጆች መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሜ ይሖዋ በቅርቡ ድህነትን፣ ሕመምንና ሞትን እንደሚያስወግድ ሳሳያቸው የነበረው ሁኔታ ጥሩ ትዝታ ጥሎብኛል። (ራእይ 21:3, 4) ብዙዎች የመንግሥቱን መልእክት ተቀብለዋል።
“የኖኅ መርከብ፣” 1974
ጉዞ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የነበረው ወንድም አልበርት ሽሮደር በ1977 ፔሩን በጎበኘበት ወቅት በዋናው መሥሪያ ቤት በሚገኘው ቤቴል ለማገልገል እንዳመለክት አበረታታኝ። እኔም አመለከትኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሰኔ 17, 1977 በብሩክሊን ቤቴል ማገልገል ጀመርኩ። በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ በጽዳትና በጥገና ክፍል ውስጥ አገልግያለሁ።
በሠርጋችን ቀን፣ 1979
ሰኔ 1978 በኒው ኦርሊየንስ፣ ሉዊዚያና በተደረገ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ከኤሊዛቤት አቫሎን ጋር ተዋወቅኩ። የእሷም ወላጆች እንደ እኔ ወላጆች እውነትን በጣም ይወዱ ነበር። ኤሊዛቤት የዘወትር አቅኚ ሆና ለአራት ዓመት አገልግላለች። በመላው ሕይወቷ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል ግብ ነበራት። ግንኙነታችን ቀጠለ። ብዙም ሳይቆይ በጣም ተዋደድን። ጥቅምት 20, 1979 ተጋባንና አንድ ላይ በቤቴል ማገልገል ጀመርን።
መጀመሪያ በተመደብንበት ጉባኤ ማለትም በብሩክሊን ስፓንኛ ጉባኤ ውስጥ የነበሩት ወንድሞችና እህቶች ልባቸውን ወለል አድርገው ከፈቱልን። ከዚያ ወዲህ ባሉት ዓመታት በሦስት ሌሎች ጉባኤዎች ውስጥ አገልግለናል። በሦስቱም ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞች በፍቅር ሞቅ አድርገው ተቀብለውናል፤ በቤቴል አገልግሎታችንም ደግፈውናል። በጉባኤያችን ድጋፍ ያደረጉልንን ወንድሞች እንዲሁም ወላጆቻችንን በእርጅና ዘመናቸው ለመንከባከብ የረዱንን ወዳጅ ዘመዶቻችንን ከልብ እናመሰግናቸዋለን።
በብሩክሊን ስፓንኛ ጉባኤ የሚያገለግሉ ቤቴላውያን፣ 1986
የሕግ ትግሉን መቀላቀል
ጥር 1982 ቤቴል በሚገኘው የሕግ ክፍል ውስጥ እንዳገለግል ስመደብ በጣም ተገረምኩ። ከሦስት ዓመት በኋላ፣ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሕግ ተምሬ የጠበቃነት ፈቃድ እንዳወጣ ተጠየቅኩ። በትምህርቴ ወቅት፣ በዩናይትድ ስቴትስም ሆነ በሌሎች አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እንደ ቀላል ነገር የሚቆጥሯቸው መሠረታዊ ነፃነቶች የይሖዋ ምሥክሮች በፍርድ ቤት ተከራክረው ባገኟቸው ድሎች ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ ተገነዘብኩ። ይህም በጣም አስገረመኝ። ስለ እነዚህ ወሳኝ የፍርድ ሂደቶች ትምህርት ቤት ውስጥ በስፋት ተምረናል።
በ1986 በ30 ዓመቴ የሕግ ክፍሉ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ገና ወጣት ስለነበርኩ ለዚህ መብቃቴ ትልቅ መብት እንደሆነ ተሰማኝ። በሌላ በኩል ደግሞ ሥራው በጣም ውስብስብ ከመሆኑ አንጻር ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር።
በ1988 ጠበቃ ሆንኩ። ሆኖም ይህ ትምህርት በመንፈሳዊነቴ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳስከተለ አልተገነዘብኩም ነበር። ከፍተኛ ትምህርት አንድ ሰው ትልቅ ቦታ የመድረስ ምኞት እንዲያድርበት ያደርጋል። እንዲሁም የእሱ ዓይነት እውቀት ከሌላቸው ሰዎች የላቀ እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል። ኤሊዛቤት ግን ከዚህ አደጋ ታደገችኝ። ከዩኒቨርሲቲ ትምህርቴ በፊት የነበረኝን መንፈሳዊ ልማድ በድጋሚ እንዳዳብር ረዳችኝ። ጊዜ ቢወስድብኝም ቀስ በቀስ በመንፈሳዊ አገገምኩ። ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር በዓለማዊ እውቀት የተሞላ ጭንቅላት እንዳልሆነ መመሥከር እችላለሁ። ለሕይወታችን እውነተኛ ዋጋ የሚሰጠው ከይሖዋ ጋር ያለን የቀረበ ዝምድና እንዲሁም ለእሱና ለሕዝቡ ያለን ጥልቅ ፍቅር ነው።
ለምሥራቹ መሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ማድረግ
የሕግ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ በቤቴል ያለውን የሕግ ክፍል በማደራጀትና ለመንግሥቱ ጉዳዮች በፍርድ ቤት በመሟገት ላይ አተኮርኩ። በፍጥነት የሚጓዘውን፣ የሚያድገውንና ተራማጅ የሆነውን ድርጅታችንን መደገፍ አስደሳችም ተፈታታኝም ነበር። ለምሳሌ ቀደም ሲል ጽሑፎቻችንን ስናበረክት ሰዎች የተወሰነ መጠን ያለው መዋጮ እንዲያደርጉ እንጠይቅ ነበር። በ1990 ግን የሕግ ክፍሉ ይህን አሠራር መቀየር የሚቻልበትን መንገድ እንዲፈልግ ተጠየቀ። ከዚያ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻቸውን ያለክፍያ ማበርከት ጀመሩ። ይህም በቤቴልና በመስኩ ያለውን ሥራ ያቀለለ ከመሆኑም ሌላ እስካሁን ድረስ ተገቢ ያልሆነ ግብር እንዳንከፍል አድርጓል። አንዳንዶች ይህ ማስተካከያ የድርጅቱን ገንዘብ እንደሚጨርሰውና በስብከቱ ሥራችን ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥር ተሰምቷቸው ነበር። ሆኖም ያጋጠመው ተቃራኒው ነው። ከ1990 ወዲህ የይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ሕይወት አድን የሆነውን መንፈሳዊ ምግብ ያለክፍያ ማግኘት ይችላሉ። ይህም ሆነ ሌሎች በርካታ ድርጅታዊ ማስተካከያዎች ስኬታማ ሊሆኑ የቻሉት ከይሖዋ ባገኘነው ብርታት እንዲሁም ታማኙ ባሪያ በሚሰጠው መመሪያ አማካኝነት እንደሆነ በገዛ ዓይኔ መመልከት ችያለሁ።—ዘፀ. 15:2፤ ማቴ. 24:45
አብዛኞቹን የሕግ ድሎች ያገኘንበት ዋነኛ ምክንያት ፍርድ ቤት ውስጥ ጥሩ አድርገን መከራከራችን አይደለም። ብዙውን ጊዜ የባለሥልጣናትን አመለካከት የሚቀይረው የይሖዋ ሕዝቦች የሚያሳዩት መልካም ምግባር ነው። ለምሳሌ በ1998 ሦስት የበላይ አካል አባላትና ሚስቶቻቸው በኩባ በተደረገ ልዩ የክልል ስብሰባ ላይ በተገኙበት ጊዜ የዚህን እውነተኝነት ማየት ችያለሁ። እነዚህ ወንድሞች ያሳዩት ደግነትና አክብሮት እኛ ከባለሥልጣናቱ ጋር ባደረግናቸው ስብሰባዎች ላይ ከተናገርነው ከየትኛውም ነገር ይበልጥ ባለሥልጣናቱን ስለ ገለልተኝነት አቋማችን አስገንዝቧቸዋል።
ሆኖም ሕግ ነክ ጉዳዮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ካልተቻለ ፍርድ ቤት ቀርበን ‘ለምሥራቹ መሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ማድረግ’ ይኖርብናል። (ፊልጵ. 1:7) ለምሳሌ ያህል ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በአውሮፓና በደቡብ ኮሪያ ያሉ ባለሥልጣናት በወታደራዊ አገልግሎት ያለመካፈል መብታችንን አላከበሩልንም። በመሆኑም በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አውሮፓ ውስጥ 18,000 ገደማ ወንድሞች፣ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ደግሞ ከ19,000 የሚበልጡ ወንድሞች ለእስር ተዳርገዋል።
በመጨረሻም ሐምሌ 7, 2011 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከሳሽ ባያትያን፣ ተከሳሽ አርሜንያ በተባለው ክስ ላይ ታሪካዊ ብይን አሳለፈ። ይህ ብይን በመላው አውሮፓ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የመስጠት መብትን ያስከብራል። ይህን ተከትሎም የደቡብ ኮሪያ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ሰኔ 28, 2018 ተመሳሳይ ውሳኔ አሳለፈ። ከወጣት ወንድሞቻችን መካከል ጥቂቶቹም እንኳ አቋማቸውን ቢያላሉ ኖሮ እነዚህ ድሎች አይገኙም ነበር።
በዋናው መሥሪያ ቤትም ሆነ በዓለም ዙሪያ ባሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚገኙ የሕግ ክፍሎች ለመንግሥቱ ጉዳዮች ጥብቅና ለመቆም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እየሠሩ ነው። የመንግሥት ተቃውሞ የገጠማቸውን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ወክሎ መከራከር ለእኛ ታላቅ ክብር ነው። በፍርድ ቤት ድል ብናገኝም ባናገኝም የፍርድ ሂደቱ ለገዢዎች፣ ለነገሥታትና ለአሕዛብ ለመመሥከር ያስችለናል። (ማቴ. 10:18) ዳኞች፣ የመንግሥት ወኪሎች፣ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ በቃልም ሆነ በጽሑፍ በምናቀርባቸው የመከራከሪያ ሐሳቦች ውስጥ የምንጠቅሳቸውን ጥቅሶች ለመመርመር ይገደዳሉ። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች እነማን እንደሆኑና እምነታቸው የተመሠረተው በምን ላይ እንደሆነ መማር ይችላሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የእምነት አጋሮቻችን ሆነዋል።
ይሖዋ፣ አመሰግንሃለሁ!
ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ከሕግ ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጋር ተባብሬ የመሥራት እንዲሁም በበርካታ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችና በከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት የመቅረብ መብት አግኝቻለሁ። በዋናው መሥሪያ ቤትም ሆነ በዓለም ዙሪያ ባሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ በሚገኙ የሕግ ክፍሎች የሚያገለግሉ የሥራ ባልደረቦቼን እወዳቸዋለሁ እንዲሁም አደንቃቸዋለሁ። ያሳለፍኩት ሕይወት በበረከት የተሞላና የሚያረካ ነው።
ኤሊዛቤት ላለፉት 45 ዓመታት በመልካሙም ሆነ በክፉው ጊዜ በታማኝነትና በፍቅር ደግፋኛለች። ለዚህም በጣም አደንቃታለሁ። ምክንያቱም ይህን ሁሉ ያደረገችው የሰውነቷን በሽታ የመከላከል አቅም ከሚያዳክምና ጉልበት ከሚያሟጥጥ ሕመም ጋር እየታገለች ነው።
ብርታትና ድል የሚገኘው በራሳችን ችሎታ እንዳልሆነ በግል ሕይወታችን አይተናል። ዳዊት እንዳለው “ይሖዋ ለሕዝቡ ብርታት ነው።” (መዝ. 28:8) በእርግጥም “ውጊያው የይሖዋ ነው።”