የጥናት ርዕስ 34
መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን
ይሖዋ ይቅር እንዳለህ አምነህ ተቀበል
“ስህተቴንና ኃጢአቴን ይቅር አልክ።”—መዝ. 32:5
ዓላማ
ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር እንደሚል የሚያረጋግጥልንስ እንዴት ነው?
1-2. ይሖዋ ይቅር እንዳለን ስናውቅ ምን ይሰማናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
ንጉሥ ዳዊት ቀደም ሲል በፈጸማቸው ኃጢአቶች የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት ተውጦ ነበር። (መዝ. 40:12፤ 51:3፤ አናት ላይ ያለው መግለጫ) ያም ቢሆን ከልቡ ንስሐ ገብቷል፤ ይሖዋም ይቅር ብሎታል። (2 ሳሙ. 12:13) በዚህም የተነሳ ዳዊት የይሖዋ ይቅርታ የሚያስገኘውን እፎይታ ጠንቅቆ ያውቃል።—መዝ. 32:1
2 እኛም ልክ እንደ ዳዊት የይሖዋ ምሕረት የሚያስገኘውን እፎይታ ማጣጣም እንችላለን። ይሖዋ ከባድ ኃጢአት ብንሠራም እንኳ እኛን ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆኑን ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! ከልባችን ንስሐ ከገባን፣ ኃጢአታችንን ከተናዘዝንና ስህተታችንን ላለመድገም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ካደረግን ይቅር ይለናል። (ምሳሌ 28:13፤ ሥራ 26:20፤ 1 ዮሐ. 1:9) እንዲሁም ይሖዋ ይቅር ካለን በኋላ ድጋሚ በዚያ ኃጢአት እንደማይጠይቀን ማወቃችን በጣም ያስደስታል።—ሕዝ. 33:16
ንጉሥ ዳዊት የይሖዋን ይቅር ባይነት የሚገልጹ በርካታ መዝሙሮችን አቀናብሯል (አንቀጽ 1-2ን ተመልከት)
3-4. አንዲት እህት ከተጠመቀች በኋላ ምን ተሰምቷት ነበር? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 አንዳንዶች ግን ይሖዋ ይቅር እንዳላቸው መቀበል ይከብዳቸው ይሆናል። የጄኒፈርን ምሳሌ እስቲ እንመልከት። ጄኒፈር ያደገችው እውነት ውስጥ ቢሆንም በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለች መጥፎ ድርጊት መፈጸምና ሁለት ዓይነት ሕይወት መምራት ጀመረች። ከዓመታት በኋላ ግን ወደ ይሖዋ ተመለሰች፤ ውሎ አድሮም ለመጠመቅ ብቃቱን አሟላች። እንዲህ ብላለች፦ “የቀድሞ ሕይወቴ በፍቅረ ንዋይ፣ በፆታ ብልግና፣ በስካርና በብስጭት የተሞላ ነበር። ይሖዋ ይቅር እንዲለኝ ከለመንኩትና ንስሐ ከገባሁ በኋላ የክርስቶስ መሥዋዕት ንጹሕ እንዳደረገኝ አውቃለሁ። ሆኖም ይሖዋ ይቅር እንዳለኝ ልቤን ማሳመን አልቻልኩም።”
4 አንተስ ይሖዋ ቀደም ሲል ለሠራሃቸው ስህተቶች ይቅር እንዳለህ ልብህን ማሳመን አንዳንድ ጊዜ ይከብድሃል? ይሖዋ ልክ እንደ ዳዊት የእሱን ይቅርታ እንዳገኘን እንድንተማመን ይፈልጋል። ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን መቀበል ያለብን ለምን እንደሆነ እንዲሁም እንዲህ ለማድረግ የሚረዳን ምን እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።
ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው?
5. ሰይጣን ምን እንድናምን ይፈልጋል? ምሳሌ ስጥ።
5 ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን መቀበላችን በሰይጣን ወጥመድ ከመያዝ ይጠብቀናል። ሰይጣን ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም ለማድረግ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለስ አስታውስ። ሰይጣን ይህን ግብ ለማሳካት ሲል፣ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንደማይለን ሊያሳምነን ይሞክራል። በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ፣ የፆታ ብልግና በመፈጸሙ የተነሳ ከጉባኤ የተወገደውን ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (1 ቆሮ. 5:1, 5, 13) ግለሰቡ በኋላ ላይ ንስሐ ሲገባ ሰይጣን በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ይቅር እንዳይሉትና እሱን ለመቀበል አሻፈረን እንዲሉ ፈልጎ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ሰይጣን፣ ንስሐ የገባው ሰው ይቅር እንደማይባል እንዲሰማውና ‘ከልክ በላይ በሐዘን ተውጦ’ ይሖዋን ማገልገሉን እንዲያቆም ፈልጎ ነበር። ሰይጣን ግቡንም ሆነ ዘዴዎቹን አልቀየረም። ሆኖም ‘እሱ የሚሸርበውን ተንኮል ስለምናውቅ’ ልናሸንፈው እንችላለን።—2 ቆሮ. 2:5-11
6. ከበደለኝነት ስሜት እፎይታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን ከተቀበልን ሸክም ከሆነው የበደለኝነት ስሜት እፎይታ ማግኘት እንችላለን። ኃጢአት ስንፈጽም የበደለኝነት ስሜት ይሰማናል። (መዝ. 51:17) ይህ ጥሩ ነገር ነው። ሕሊናችን አካሄዳችንን ለማረም የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይችላል። (2 ቆሮ. 7:10, 11) ሆኖም ለኃጢአታችን ንስሐ ከገባን ከረጅም ጊዜ በኋላም የበደለኝነት ስሜት የሚያሠቃየን ከሆነ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን ስንቀበል የበደለኝነት ስሜትን ከላያችን አንስተን መጣል እንችላለን። ከዚያም ይሖዋን እሱ በሚፈልገው መንገድ፣ ማለትም በንጹሕ ሕሊናና በደስታ ማገልገል እንችላለን። (ቆላ. 1:10, 11፤ 2 ጢሞ. 1:3) ሆኖም ይሖዋ ይቅር እንዳለን ልባችንን ማሳመን የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን ለመቀበል ምን ሊረዳን ይችላል?
7-8. ይሖዋ ራሱን ለሙሴ የገለጸው እንዴት ነው? ይህስ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል? (ዘፀአት 34:6, 7)
7 ይሖዋ ራሱን በገለጸበት መንገድ ላይ አሰላስል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ ሙሴን ምን እንዳለው ልብ በል።a (ዘፀአት 34:6, 7ን አንብብ።) ይሖዋ ስለ ባሕርያቱና ስለ ማንነቱ ብዙ ነገር ማለት ቢችልም ራሱን የገለጸው “መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ” ብሎ ነው። እንዲህ የመሰለው አምላክ፣ አንድ አገልጋዩ ከልቡ ንስሐ ከገባ በኋላ ይቅርታውን ሊነፍገው ይችላል? በፍጹም! እንዲህ ማድረግ ምሕረት የለሽነትና ጭካኔ ነው። ይሖዋ ደግሞ እንዲህ ያለውን ባሕርይ ጨርሶ ሊያሳይ አይችልም።
8 ይሖዋ የእውነት አምላክ ስለሆነ ስለ ራሱ የተሳሳተ ነገር ፈጽሞ ሊናገር እንደማይችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 31:5) ስለዚህ የተናገረውን ቃል ልናምን ይገባል። ቀደም ሲል በፈጸምከው ኃጢአት የተነሳ አሁንም በበደለኝነት ስሜት የምትሠቃይ ከሆነ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ይሖዋ በእርግጥ መሐሪና ሩኅሩኅ እንደሆነ እንዲሁም ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን በሙሉ ይቅር እንደሚል አምናለሁ? ታዲያ እኔን ይቅር እንዳለኝ አምኜ ልቀበል አይገባም?’
9. መዝሙር 32:5 ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ስለሚልበት መንገድ ምን ያስተምረናል?
9 የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ ይሖዋ ይቅር ባይነት በመንፈስ መሪነት በተናገሩት ነገር ላይ አሰላስል። ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ዳዊት ስለ ይሖዋ ይቅር ባይነት ምን እንዳለ እንመልከት። (መዝሙር 32:5ን አንብብ።) ዳዊት “ስህተቴንና ኃጢአቴን ይቅር አልክ” ብሏል። “ይቅር አልክ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ማንሳት፣” “መውሰድ” ወይም “መሸከም” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ይሖዋ ዳዊትን ይቅር ባለው ጊዜ በምሳሌያዊ ሁኔታ ኃጢአቱን ከላዩ አንስቶ ተሸክሞ ወስዶለታል ሊባል ይችላል። ከዚያ በኋላ ዳዊት ተሸክሞት ከነበረው ከባድ የበደለኝነት ስሜት እፎይታ አገኘ። (መዝ. 32:2-4) እኛም ተመሳሳይ እፎይታ ልናገኝ እንችላለን። ለፈጸምነው ኃጢአት ከልባችን ንስሐ ከገባን ይሖዋ ኃጢአቱን ከላያችን አንስቶ ስለሚያስወግደው ከዚያ በኋላ በበደለኝነት ስሜት ልንሠቃይ አይገባም።
10-11. ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ ነህ’ የሚለው አገላለጽ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? (መዝሙር 86:5)
10 መዝሙር 86:5ን አንብብ። እዚህ ላይ ዳዊት፣ ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ መሆኑን ገልጿል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ ስለዚህ አገላለጽ ሲናገር “እሱ ይቅር ባይ ነው፤ ይቅር ማለት ማንነቱ ነው” ብሏል። ይቅር ባይነት የይሖዋ ማንነት ክፍል የሆነው ለምንድን ነው? የጥቅሱ ቀጣይ ክፍል መልሱን ይሰጠናል፦ “አንተን ለሚጠሩ ሁሉ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን የለውም” ይላል። ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተማርነው ታማኝ ፍቅር ይሖዋ አገልጋዮቹን በጥልቅ እንዲወዳቸውና መቼም ቢሆን እንዳይተዋቸው ያነሳሳዋል። በታማኝ ፍቅሩ ተነሳስቶ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን በሙሉ “በነፃ ይቅር ይላል።” (ኢሳ. 55:7 ግርጌ) ይሖዋ ይቅር እንዳለህ አምነህ መቀበል ከከበደህ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ይቅር ባይነት የይሖዋ ማንነት ክፍል እንደሆነና ንስሐ ገብተው ምሕረቱን የሚለምኑትን ሁሉ ይቅር ለማለት ዝግጁ እንደሆነ በእርግጥ አምናለሁ? ታዲያ እኔስ የእሱን ምሕረት ለማግኘት ስለምነው ይቅር እንዳለኝ አምኜ ልቀበል አይገባም?’
11 ይሖዋ ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞች መሆናችንን ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳ ማወቃችን ያጽናናናል። (መዝ. 139:1, 2) ዳዊት በሌላ መዝሙሩ ላይ ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት። ይህም ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን እንድንቀበል ይረዳናል።
ይሖዋ የሚያስታውሰውን አትርሳ
12-13. በመዝሙር 103:14 መሠረት ይሖዋ ስለ እኛ ምን ያስታውሳል? ይህስ ምን እንዲያደርግ ያነሳሳዋል?
12 መዝሙር 103:14ን አንብብ። ዳዊት ስለ ይሖዋ ሲናገር “አፈር መሆናችንን ያስታውሳል” ብሏል። ዳዊት በዚህ ጥቅስ ላይ፣ ይሖዋ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር እንዲል የሚያነሳሳውን አንድ ምክንያት ገልጿል። ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኛ መሆናችንን ሁሌም ያስታውሳል። ይህን በደንብ ለመረዳት ዳዊት የተጠቀመባቸውን ቃላት በጥልቀት እንመርምር።
13 ዳዊት፣ ይሖዋ ‘እንዴት እንደተሠራን በሚገባ እንደሚያውቅ’ ተናግሯል። አዳምን የሠራው “ከምድር አፈር” ነው። በመሆኑም ፍጹም የሆኑ ሰዎች እንኳ ተፈጥሯዊ ገደቦች እንዳሉባቸው በሚገባ ያውቃል፤ ለምሳሌ መብላት፣ መተኛትና መተንፈስ ያስፈልጋቸዋል። (ዘፍ. 2:7) ሆኖም አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ‘አፈር መሆን’ የሚለው አገላለጽ ተጨማሪ ትርጉም ኖረው። እኛም የእነሱ ዘሮች እንደመሆናችን መጠን ከእነሱ ኃጢአትን ወርሰናል፤ በመሆኑም መጥፎ ነገር መሥራት ይቀናናል። ይሖዋ ኃጢአተኛ መሆናችንን በማወቅ ብቻ አይወሰንም፤ ከዚህ ይልቅ ዳዊት እንደገለጸው ኃጢአተኛ መሆናችንን “ያስታውሳል።” ይሖዋ ኃጢአተኞች መሆናችንን ስለሚያስታውስ ምንጊዜም በርኅራኄ ይይዘናል። ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ በዚህ መልኩ ልናጠቃልለው እንችላለን፦ ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት መሥራታችን እንደማይቀር ያውቃል፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ ከልባችን ንስሐ እስከገባን ድረስ ምሕረት ሊያደርግልንና ይቅር ሊለን ይፈልጋል።—መዝ. 78:38, 39
14. (ሀ) ዳዊት የይሖዋ ይቅርታ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ የገለጸው እንዴት ነው? (መዝሙር 103:12) (ለ) የዳዊት ታሪክ ይሖዋ ይቅር የሚለው ሙሉ በሙሉ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው? (“ይሖዋ ይቅር ካለን በኋላ ኃጢአታችንን የሚረሳው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
14 የይሖዋ ይቅር ባይነት ምን ያህል ታላቅ ነው? (መዝሙር 103:12ን አንብብ።) ዳዊት፣ ይሖዋ ይቅር ስለሚልበት መንገድ ሲናገር “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ በደላችንን ከእኛ አራቀ” ብሏል። ምሥራቅና ምዕራብ በተለያየ ጽንፍ የሚገኙ አቅጣጫዎች ስለሆኑ ፈጽሞ ሊገናኙ አይችሉም። ይህ ሐሳብ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ስለሚልበት መንገድ ምን ይነግረናል? አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ የሚከተለውን ምሳሌ ተጠቅሟል፦ “ኃጢአታችን ከእኛ እጅግ ከመራቁ የተነሳ ሽታው፣ ርዝራዡ እንዲሁም ትዝታው ሙሉ በሙሉ ይጠፋል።” ሽታ አንድን ትዝታ ሊቀሰቅስ ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ይቅር ሲለን የኃጢአቱ ሽታ እንኳ ሙሉ በሙሉ ስለሚጠፋ ኃጢአቱን አስታውሶ እኛ ላይ እርምጃ እንዲወስድ የሚያደርገው ምንም ነገር አይኖርም።—ሕዝ. 18:21, 22፤ ሥራ 3:19
15. ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ኃጢአቶች የተነሳ የበደለኝነት ስሜት አሁንም የሚያሠቃየን ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን?
15 ዳዊት በመዝሙር 103 ላይ የተናገራቸው ቃላት ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን እንድንቀበል የሚረዱን እንዴት ነው? ቀደም ሲል በሠራነው ኃጢአት የተነሳ አሁንም የበደለኝነት ስሜት የሚሰማን ከሆነ ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፦ ‘ይሖዋ የሚያስታውሰውን ነገር እየረሳሁ ነው? ማለትም ይሖዋ ስወለድ ጀምሮ ኃጢአተኛ መሆኔን እንደሚያስታውስና ንስሐ ከገባሁ ይቅር እንደሚለኝ እየረሳሁ ነው? በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ለመርሳት የመረጠውን ነገር እያስታወስኩ ነው? ማለትም ይሖዋ ይቅር ያላቸውንና ዳግመኛ የማያነሳቸውን ኃጢአቶቼን እያስታወስኩ ነው?’ ይሖዋ ቀደም ሲል በሠራናቸው ኃጢአቶች ላይ አያተኩርም። እኛም እንዲህ ልናደርግ አይገባም። (መዝ. 130:3) ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን ስንቀበል ቀደም ሲል ለሠራናቸው ስህተቶች ራሳችንን ይቅር ማለትና ይሖዋን ማገልገላችንን መቀጠል እንችላለን።
16. ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች ላይ ማተኮራችን ያለውን አደጋ በምሳሌ አስረዳ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)
16 እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ኃጢአቶች ላይ ማተኮር ወደ ኋላ መመልከቻ መስታወት እያዩ ወደፊት ለመንዳት ከመሞከር ጋር ይመሳሰላል። ወደ ኋላ መመልከቻ መስታወቱን አልፎ አልፎ መመልከቱ ጠቃሚ ነው፤ ከኋላችን ያሉ አደገኛ ሁኔታዎችን ለማስተዋል ይረዳናል። ሆኖም አደጋ ሳናደርስ ወደ ፊት ለመጓዝ ከፊታችን ባለው መንገድ ላይ ማተኮር አለብን። በተመሳሳይም ቀደም ሲል የሠራናቸውን ስህተቶች አልፎ አልፎ ማስታወሳችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፤ ከስህተታችን ለመማርና ስህተታችንን ላለመድገም ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር ይረዳናል። ሆኖም ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች ላይ ማተኮራችንን ከቀጠልን፣ የሚሰማን የጥፋተኝነት ስሜት በአሁኑ ጊዜ ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት ሊገድብብን ይችላል። እንግዲያው ከፊታችን ባለው መንገድ ላይ ትኩረት ማድረጋችንን እንቀጥል። አምላክ ቃል ወደገባው አዲስ ዓለም በሚወስደው የሕይወት መንገድ ላይ እየተጓዝን ነው፤ እዚያ ስንደርስ ሁሉም መጥፎ ትዝታዎች “አይታሰቡም።”—ኢሳ. 65:17፤ ምሳሌ 4:25
አንድ ሹፌር ወደ ኋላ ከሚያሳየው መስታወት ይልቅ ከፊቱ ባለው መንገድ ላይ ማተኮር እንዳለበት ሁሉ እኛም ይበልጥ ማተኮር ያለብን ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች ላይ ሳይሆን ወደፊት በምናገኛቸው በረከቶች ላይ ነው (አንቀጽ 16ን ተመልከት)
ልብህን ማሳመንህን ቀጥል
17. ይሖዋ እንደሚወደንና ይቅር እንዳለን ልባችንን ማሳመናችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
17 ይሖዋ እንደሚወደንና ይቅር እንዳለን ልባችንን ማሳመናችንን መቀጠል ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 3:19 ግርጌ) ለምን? ምክንያቱም ሰይጣን፣ ይሖዋ እንደማይወደን እንዲሁም ይቅር እንዳላለን እኛን ለማሳመን ሁልጊዜ ጥረት ያደርጋል። ዞሮ ዞሮ የሰይጣን ፍላጎት አንድ ነው፦ ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም ማድረግ። ሰይጣን የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ስለሚያውቅ ጥረቱን አፋፍሞ እንደሚቀጥል መጠበቅ እንችላለን። (ራእይ 12:12) ፈጽሞ እንዲያሸንፍ ልንፈቅድለት አይገባም!
18. ይሖዋ እንደሚወድህና ይቅር እንዳለህ ልብህን ለማሳመን ምን ማድረግ ትችላለህ?
18 ይሖዋ እንደሚወድህ ያለህን እምነት ለማጠናከር ባለፈው ርዕስ ላይ የቀረቡትን ምክሮች ተግባራዊ አድርግ። ይሖዋ ይቅር እንዳለህ ልብህን ለማሳመን ይሖዋ ራሱን በገለጸበት መንገድ ላይ አሰላስል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ ይሖዋ ይቅር ባይነት በመንፈስ መሪነት በጻፉት ነገር ላይ አሰላስል። ይሖዋ ስትወለድ ጀምሮ ኃጢአተኛ መሆንህን እንደሚያስታውስና በምሕረት እንደሚይዝህ አትዘንጋ። በተጨማሪም ይሖዋ ይቅር የሚለው ሙሉ በሙሉ እንደሆነ አስታውስ። እንዲህ ካደረግክ፣ እንደ ዳዊት በይሖዋ ምሕረት ሙሉ በሙሉ በመተማመን እንዲህ ማለት ትችላለህ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ‘ስህተቴንና ኃጢአቴን’ ይቅር ስላልክ አመሰግንሃለሁ!”—መዝ. 32:5
መዝሙር 1 የይሖዋ ባሕርያት
a በግንቦት 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ወደ አምላክ ቅረብ—ይሖዋ ባሕርያቱን ሲገልጽ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።