የሕይወት ታሪክ
ከዓይናፋርነት ወደ ሚስዮናዊነት
በልጅነቴ ዓይናፋር ነበርኩ፤ ሰዎችንም እፈራ ነበር። ውሎ አድሮ ግን ይሖዋ ሰው ተኮር ሚስዮናዊ እንድሆን ረድቶኛል። እንዴት? በመጀመሪያ አባቴ በሰጠኝ ሥልጠና፣ ቀጥሎም አንዲት ወጣት እህት በተወችልኝ ግሩም ምሳሌ፣ በመጨረሻም ባለቤቴ በተናገራቸው ደግነትና ትዕግሥት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት አማካኝነት ነው። የሕይወት ታሪኬን እስቲ ልንገራችሁ።
የተወለድኩት በ1951 በቪየና፣ ኦስትሪያ ነው። ቤተሰቦቼ ካቶሊኮች ነበሩ። ዓይናፋር ብሆንም በአምላክ አምንና አዘውትሬ እጸልይ ነበር። የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እናቴም አብራው ማጥናት ጀመረች።
ከእህቴ ከኤሊዛቤት ጋር (በስተ ግራ)
ብዙም ሳይቆይ፣ በቪየና የሚገኘውን የዶብሊንግ ጉባኤ ተቀላቀልን። በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን ብዙ ነገር እናደርግ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን እናነባለን እንዲሁም እናጠናለን፤ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንገኛለን፤ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይም ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነን እናገለግላለን። ገና በልጅነቴ አባቴ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር እንዲያድርብኝ ረድቶኛል። እንዲያውም አባቴ እኔና እህቴ አቅኚዎች እንድንሆን ሁልጊዜ ይጸልይ ነበር። እኔ ግን በወቅቱ አቅኚ የመሆን ግብ አልነበረኝም።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ
በ1965 በ14 ዓመቴ ተጠመቅኩ። ሆኖም አገልግሎት ላይ የማላውቃቸውን ሰዎች ቀርቦ ማነጋገር ይከብደኝ ነበር። በተጨማሪም የበታችነት ስሜት ይሰማኝ ስለነበር በእኩዮቼ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። ስለዚህ ከተጠመቅኩ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋን ከማያገለግሉ ልጆች ጋር መቀራረብ ጀመርኩ። ከእነሱ ጋር መሆኔ ቢያስደስተኝም የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ ልጆች ጋር ብዙ ጊዜ በማሳለፌ ሕሊናዬ ይወቅሰኝ ነበር። ሆኖም ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል አቅም አልነበረኝም። ታዲያ የረዳኝ ምንድን ነው?
ከዶሮቲ (በስተ ግራ) ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ
በዚያ ጊዜ አካባቢ፣ ዶሮቲ የተባለች የ16 ዓመት ልጅ ወደ ጉባኤያችን መጣች። ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል የነበራት ቅንዓት በጣም አስገረመኝ። እኔ ከእሷ በዕድሜ ትንሽ ብበልጥም እምብዛም በአገልግሎት አልካፈልም ነበር። እንዲህ ብዬ አሰብኩ፦ ‘የእኔ ወላጆች የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ ዶሮቲ ግን እውነት ውስጥ አንድም ቤተሰብ የላትም። እናቷ ታማሚ ነች። ሆኖም ዶሮቲ ሁልጊዜ አገልግሎት ትወጣለች።’ የእሷ ምሳሌ ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል አነሳሳኝ። ብዙም ሳይቆይ እኔና ዶሮቲ አብረን በአቅኚነት ማገልገል ጀመርን። በመጀመሪያ ረዳት አቅኚዎች ሆንን፤ በኋላም በዘወትር አቅኚነት አብረን ማገልገል ጀመርን። የዶሮቲ ቅንዓት የሚጋባ ነበር። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዳስጀምር የረዳችኝ እሷ ነች። ውሎ አድሮ ሰዎችን ከቤት ወደ ቤት፣ መንገድ ላይ ወይም በሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ ቀርቦ ማነጋገር እየቀለለኝ መጣ።
የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል በጀመርኩበት ዓመት ሃይንዝ የተባለ ኦስትሪያዊ ወንድም ወደ ጉባኤያችን መጣ። ሃይንዝ እውነትን የሰማው የይሖዋ ምሥክር የሆነውን ወንድሙን ለመጠየቅ ወደ ካናዳ በሄደበት ወቅት ነው። ሃይንዝ በቪየና በሚገኘው ጉባኤያችን ውስጥ ልዩ አቅኚ ሆኖ እንዲያገለግል ተመደበ። ገና እንደመጣ ነው የወደድኩት። ሆኖም እሱ ሚስዮናዊ መሆን ይፈልግ ነበር፤ እኔ ደግሞ በሚስዮናዊነት የማገልገል ሐሳብ አልነበረኝም። ስለዚህ መጀመሪያ ላይ ለእሱ ያለኝን ስሜት ለመደበቅ ሞከርኩ። በኋላ ግን እኔና ሃይንዝ መጠናናት ጀመርን። ከዚያም ተጋብተን አብረን ኦስትሪያ ውስጥ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርን።
ሚስዮናዊነትን ግብ ማድረግ
ሃይንዝ ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት እንዳለው ብዙ ጊዜ ይነግረኝ ነበር። ጫና ሊያሳድርብኝ ሞክሮ ባያውቅም አንዳንድ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ፍላጎቴን ለመቀስቀስ ይሞክር ነበር። ለምሳሌ “ልጆች ስለሌሉን ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት ማስፋት እንችል ይሆን?” ይለኛል። ዓይናፋር ስለነበርኩ ሚስዮናዊ መሆን ያስፈራኝ ነበር። በአቅኚነት አገለግል የነበረ ቢሆንም በሚስዮናዊነት ማገልገል ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ሆኖም ሃይንዝ ሚስዮናዊነትን ግብ እንዳደርግ በትዕግሥት ረዳኝ። በተጨማሪም ስለ ራሴ ከመጨነቅ ይልቅ ሰዎችን በመርዳት ላይ እንዳተኩር አበረታታኝ። የሰጠኝ ምክር በጣም ጠቅሞኛል።
ሃይንዝ በሳልዝበርግ፣ ኦስትሪያ በሚገኝ በዩጎዝላቪያኛ የሚመራ ትንሽ ጉባኤ ውስጥ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ሲመራ፣ 1974
ቀስ በቀስ በሚስዮናዊነት የማገልገል ፍላጎት አደረብኝ። ስለዚህ በጊልያድ ትምህርት ቤት ለመማር አመለከትን። ሆኖም የቅርንጫፍ ቢሮው አገልጋይ በመጀመሪያ እንግሊዝኛዬን እንዳሻሽል ሐሳብ አቀረበልኝ። ለሦስት ዓመት ያህል እንግሊዝኛዬን ለማሻሻል ጥረት ሳደርግ ከቆየሁ በኋላ ሳልዝበርግ፣ ኦስትሪያ ውስጥ በሚገኝ በዩጎዝላቪያኛ ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ ውስጥ እንድናገለግል ስንመደብ በጣም ተገረምን። በዚያ መስክ ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት አገለገልን። አንዱን ዓመት ያሳለፍነው በወረዳ ሥራ ነው። ቋንቋው ከባድ ቢሆንም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ነበሩን።
ከዚያም በ1979 “ለእረፍት” ወደ ቡልጋሪያ እንድንሄድ ተጠየቅን። በቡልጋሪያ የስብከቱ ሥራ ታግዶ ነበር። ስለዚህ በዚያ ጉብኝት ወቅት አልሰበክንም። ሆኖም በመዲናዋ በሶፊያ ለሚኖሩት አምስት እህቶች በትናንሹ የተዘጋጁ ጽሑፎችን በድብቅ አስገባንላቸው። በጣም ፈርቼ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ ይህን አስደሳች ኃላፊነት እንድወጣ ረድቶኛል። የእነዚያን እህቶች ድፍረት እንዲሁም ተይዘው ሊታሰሩ እንደሚችሉ ቢያውቁም እንኳ የነበራቸውን ደስታ ስመለከት በጣም ተገረምኩ። የእነሱ ምሳሌነት እኔም የይሖዋ ድርጅት የሰጠኝን ማንኛውንም ሥራ አቅሜ በፈቀደ መጠን ማከናወን እንደምችል እንድተማመን ረዳኝ።
በዚያ መሃል ለጊልያድ ትምህርት ቤት በድጋሚ አመለከትን። ከዚያም በትምህርት ቤቱ እንድንካፈል ተጋበዝን። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በእንግሊዝኛ በሚካሄደው ትምህርት ቤት እንደምንማር አስበን ነበር። ሆኖም ኅዳር 1981 በቪስባደን፣ ጀርመን ውስጥ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ የጊልያድ ትምህርት ቤት ቅርንጫፍ ተከፈተ። በመሆኑም ትምህርቱን በጀርመንኛ መከታተል ቻልን፤ ይህም ለመረዳት ቀላል አድርጎልኛል። ይሁንና የት እንመደብ ይሆን?
በጦርነት በምትታመስ አገር ውስጥ ማገልገል
በኬንያ እንድናገለግል ተመደብን። ሆኖም የኬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ጎረቤት አገር በሆነችው በኡጋንዳ ለማገልገል ፈቃደኞች መሆናችንን ጠየቀን። ከአሥር ዓመት ገደማ በፊት የኡጋንዳ መንግሥት በጄነራል ኢዲ አሚን በሚመራው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተገልብጦ ነበር። በቀጣዮቹ ዓመታት የኢዲ አሚን አምባገነናዊ አስተዳደር በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞትና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች መከራ መንስኤ ሆኗል። በ1979 ደግሞ የኡጋንዳ መንግሥት በድጋሚ ተገለበጠ። በጦርነት ወደምትታመሰው ወደዚህች አገር መሄድ ምን ያህል አስፈርቶኝ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ሆኖም ጊልያድ በይሖዋ እንድንታመን አስተምሮናል። ስለዚህ ምድቡን ተቀበልን።
በኡጋንዳ የነበረው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነበር። መንግሥት ውኃ፣ ኤሌክትሪክና ሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን ማቅረብ አልቻለም። ስልክ አይሠራም ነበር። በተለይ ሌሊት ላይ ተኩስ እና ዝርፊያ የተለመደ ነገር ነበር። ቀኑ ሲጨልም ሁሉም ሰው ቤቱ ክትት ብሎ ዘራፊዎች ወይም ወንበዴዎች እንዳይመጡበት ይጸልያል። እነዚህ ሁሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም የአካባቢው ወንድሞች በመንፈሳዊ እያደጉ ነበር።
በሳም እና ክርስቲና ዋይስዋ ቤት ውስጥ ምግብ ስናበስል
በ1982 እኔና ሃይንዝ የኡጋንዳ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ካምፓላ ሄድን። የመጀመሪያዎቹን አምስት ወራት የቆየነው በሳም እና በክርስቲና ዋይስዋ ቤት ውስጥ ነው። ሳም እና ክርስቲና የሚኖሩት ከአምስት ልጆቻቸውና ከአራት ዘመዶቻቸው ጋር ነበር። ቤተሰቡ አብዛኛውን ጊዜ የሚመገበው በቀን አንዴ ብቻ ነበር። በመሆኑም እንግዳ ተቀባይነታቸው በጣም አስደነቀን። እነሱ ቤት ውስጥ በነበረን ቆይታ እኔና ሃይንዝ ለሚስዮናዊነት አገልግሎታችን የሚጠቅሙን ብዙ ትምህርቶች አግኝተናል። ለምሳሌ ጥቂት ሊትር ውኃ ብቻ ተጠቅመን ገላችንን በመታጠብ ከዚያም የታጠብንበትን ውኃ መጸዳጃ ቤት በመድፋት ውኃ መቆጠብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተማርን። በ1983 እኔና ሃይንዝ ካምፓላ ውስጥ አንጻራዊ ደህንነት ባለበት ቦታ ቤት አገኘን።
አገልግሎቱን በጣም ወደድነው። በአንድ ወር ውስጥ ከ4,000 መጽሔት በላይ አበርክተን እንደነበር ትዝ ይለኛል። ሆኖም በጣም የወደድነው ሰዎቹን ነው። ለአምላክ አክብሮት ነበራቸው፤ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየትም ይፈልጉ ነበር። እኔና ሃይንዝ እያንዳንዳችን ከ10 እስከ 15 ጥናቶችን እንመራ ነበር። ከጥናቶቻችንም ብዙ ትምህርት አግኝተናል። ለምሳሌ በየሳምንቱ ወደ ስብሰባ የሚሄዱትም ሆነ ከስብሰባ የሚመለሱት በእግራቸው ቢሆንም ፈጽሞ አያጉረመርሙም፤ ፈገግታ ከፊታቸው አይለይም።
በ1985 እና በ1986 ኡጋንዳ ውስጥ ሁለት ሌሎች ጦርነቶች ተነሱ። መሣሪያ ታጥቀው ኬላዎችን የሚጠብቁ ሕፃናት ወታደሮችን ብዙ ጊዜ እናይ ነበር። በዚያ ወቅት አገልግሎት ወጥተን ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ስንፈልግ ይሖዋ ማስተዋል እንዲሰጠንና ልባችንን እንዲያረጋጋልን እንጸልይ ነበር። ይሖዋም ጸሎታችንን መልሶልናል። አብዛኛውን ጊዜ፣ ለመንግሥቱ መልእክት በጎ ምላሽ የሚሰጥ ሰው ስናገኝ ፍርሃታችንን ወዲያውኑ እንረሳዋለን።
እኔና ሃይንዝ ከታትያና ጋር (መሃል ላይ)
ከውጭ አገር ለመጡ ሰዎች መስበክም ያስደስተን ነበር። ለምሳሌ ከታታርስታን (ማዕከላዊ ሩሲያ) የመጡትን ሙራት እና ዲልባር ኢባቱሊን የተባሉ ባልና ሚስት እናስጠና ነበር። ሙራት የሕክምና ባለሙያ ነው። ባልና ሚስቱ ወደ እውነት መጡ፤ አሁንም ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ነው። ከጊዜ በኋላ ደግሞ፣ ከዩክሬን ከመጣችው ከታትያና ቪሌስካ ጋር ተዋወቅኩ። ታትያና ራሷን ለማጥፋት እያሰበች ነበር። ታትያና ከተጠመቀች በኋላ ወደ ዩክሬን ተመለሰች፤ በኋላም ተርጓሚ ሆና ጽሑፎቻችንን በመተርጎሙ ሥራ ተካፍላለች።a
አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች
በ1991 እኔና ሃይንዝ ለእረፍት ኦስትሪያ ሄደን ሳለ ቅርንጫፍ ቢሮው በቡልጋሪያ አዲስ ምድብ እንደተሰጠን ነገረን። በምሥራቅ አውሮፓ ኮሚኒዝም ከወደቀ በኋላ ቡልጋሪያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ ነበር። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት፣ እኔና ሃይንዝ ቡልጋሪያ ውስጥ ሥራው ታግዶ በነበረበት ወቅት ጽሑፎችን በድብቅ ወደ አገሪቱ አስገብተናል። አሁን ግን እዚያ የተላክነው እንድንሰብክ ነው።
ወደ ኡጋንዳ እንዳንመለስ ተነገረን። ስለዚህ ወደ ቤታችን ተመልሰን ዕቃችንን ሳንሸክፍም ሆነ ጓደኞቻችንን ሳንሰናበት በጀርመን ወደሚገኘው ቤቴል ሄድን። ከዚያም መኪና ተቀብለን ወደ ቡልጋሪያ ተጓዝን። ሶፊያ ውስጥ በሚገኝ 20 ገደማ አስፋፊዎችን ባቀፈ ቡድን ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን።
ቡልጋሪያ ውስጥ በርካታ አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውናል። በመጀመሪያ ደረጃ ቋንቋውን አናውቅም። በተጨማሪም በቡልጋሪያኛ የተዘጋጁት ጽሑፎች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት እና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባሉት መጻሕፍት ብቻ ነበሩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመርም ከባድ ነበር። እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ቀናተኛ አስፋፊዎችን የያዘው ትንሹ ቡድናችን እድገት እያደረገ ነበር። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይህን ባስተዋለች ጊዜ ለተጨማሪ ችግሮች ተዳረግን።
በ1994 የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅናቸውን ተነጠቁ፤ ከዚያ በኋላ እንደ አደገኛ ኑፋቄ መታየት ጀመሩ። አንዳንድ ወንድሞች ታሰሩ። መገናኛ ብዙኃን ስለ እኛ ዘግናኝ ውሸቶችን ማሰራጨት ጀመሩ። የይሖዋ ምሥክሮች ልጆችን እንደሚገድሉ እንዲሁም ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን እንዲያጠፉ እንደሚያበረታቱ ገለጹ። እኔና ሃይንዝ እዚያ መስበክ በጣም ከባድ ሆነብን። አገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች ይጮኹብን፣ ፖሊስ ይጠሩብን፣ አልፎ ተርፎም ዕቃ ይወረውሩብን ነበር። ጽሑፎችን ወደ አገሪቱ ማስገባት አልቻልንም፤ ስብሰባ የምናደርግበት አዳራሽ መከራየትም ከባድ ሆነብን። እንዲያውም በአንድ ወቅት ትልቅ ስብሰባ እያደረግን ሳለ ፖሊሶች መጥተው አስቆሙን። እንዲህ ያለው ጥላቻ ለእኔና ለሃይንዝ አዲስ ነገር ነበር። ኡጋንዳ ውስጥ ከለመድነው ፍሬያማና አስደሳች መስክ በጣም የተለየ ነበር! ታዲያ ለውጡን ለማስተናገድ የረዳን ምንድን ነው?
በአካባቢው ካሉት ወንድሞችና እህቶች ጋር ጊዜ ማሳለፋችን ደስተኛ ለመሆን ረድቶናል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች እውነትን በማግኘታቸው ደስተኛ ነበሩ። እኛ ለምናደርግላቸው እርዳታም አድናቆት ነበራቸው። ሁሉም እርስ በርስ ይቀራረቡ እንዲሁም ይደጋገፉ ነበር። በዚያ ካሳለፍነው ተሞክሮ እንደተማርነው በሰዎች ላይ ማተኮራችንን እስከቀጠልን ድረስ በየትኛውም የአገልግሎት ምድብ ደስታ ማግኘት እንችላለን።
በቡልጋሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ፣ 2007
ይሁንና ውሎ አድሮ ሁኔታዎች መሻሻል ጀመሩ። በ1998 ድርጅታችን በድጋሚ ሕጋዊ እውቅና አገኘ። ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በቡልጋሪያኛ በርካታ ጽሑፎች ተዘጋጁ። ከዚያም በ2004 አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ ተወሰነ። በአሁኑ ጊዜ ቡልጋሪያ ውስጥ 2,953 አስፋፊዎችን ያቀፉ 57 ጉባኤዎች ይገኛሉ። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት 6,475 ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተዋል። በአንድ ወቅት ሶፊያ ውስጥ የነበሩት አምስት እህቶች ብቻ ቢሆኑም አሁን ግን ዘጠኝ ጉባኤዎች አሉ። በእርግጥም “ጥቂት የሆነው ሺህ” ሲሆን ተመልክተናል።—ኢሳ. 60:22
ከግል ችግሮች ጋር መታገል
በሕይወቴ ውስጥ በርካታ የጤና እክሎች አጋጥመውኛል። በተለያዩ የአካሌ ክፍሎች ውስጥ ዕጢዎች ተገኝተው ነበር። ለምሳሌ በአንድ ወቅት በጭንቅላቴ ውስጥ ዕጢ ተገኝቷል። የጨረር ሕክምና ወስጃለሁ፤ እንዲሁም አብዛኛውን የዕጢውን ክፍል ለማውጣት ሕንድ ውስጥ 12 ሰዓት የፈጀ ቀዶ ሕክምና አድርጌያለሁ። በሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ቆይቼ ካገገምኩ በኋላ ቡልጋሪያ ወዳለው ምድባችን ተመለስን።
ሃይንዝ ደግሞ የሃንቲንግተን በሽታ ተብሎ በሚጠራ እምብዛም ያልተለመደ በዘር የሚተላለፍ ሕመም ተያዘ። መራመድ፣ መናገር እንዲሁም እንቅስቃሴውን መቆጣጠር እየከበደው መጣ። ሕመሙ እየተባባሰ ሲሄድ የእኔ እርዳታ ይበልጥ ያስፈልገው ጀመር። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታው ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፤ ስለ ወደፊቱ ጊዜም ስጋት ያድርብኝ ጀመር። ሆኖም ቦቢ የተባለ ወጣት ወንድም ሃይንዝን ብዙ ጊዜ አገልግሎት ይጋብዘው ነበር። ቦቢ የሃይንዝ አነጋገርም ሆነ እንቅስቃሴውን መቆጣጠር አለመቻሉ አላሳፈረውም። እኔ ሃይንዝን መርዳት በማልችልበት ጊዜ ሁሉ ሐሳቤን በቦቢ ላይ እጥል ነበር። እኔና ሃይንዝ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ልጆች ላለመውለድ ብንወስንም ይሖዋ ቦቢን እንደ ልጃችን አድርጎ እንደሰጠን ተሰማን።—ማር. 10:29, 30
ሃይንዝ ከካንሰር ጋር መታገልም አስፈልጎታል። የሚያሳዝነው፣ ውዱ ባለቤቴ በ2015 አረፈ። ሃይንዝ ከሞተ በኋላ በከፍተኛ ፍርሃት ተዋጥኩ፤ እሱ አለመኖሩን መቀበል ከበደኝ። በአእምሮዬ ውስጥ ሃይንዝ አሁንም ሕያው ነው! (ሉቃስ 20:38) የዕለት ተዕለት ሕይወቴን ሳከናውን ሃይንዝ የተናገራቸውን ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላትና ጥበብ ያዘለ ምክሩን ብዙ ጊዜ አስታውሳለሁ። አብረን ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላሳለፍናቸው ዓመታት በጣም አመስጋኝ ነኝ።
ይሖዋ ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ
በእርግጥም ባጋጠሙኝ ፈተናዎች ሁሉ ይሖዋ ደግፎኛል። በተጨማሪም ዓይናፋርነትን አሸንፌ ሰው ተኮር ሚስዮናዊ እንድሆን ረድቶኛል። (2 ጢሞ. 1:7) በይሖዋ እርዳታ እኔም ሆንኩ ታናሽ እህቴ በአሁኑ ወቅት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈልን እንገኛለን። እህቴና ባለቤቷ አውሮፓ ውስጥ በሚገኝ የሰርቢያኛ ወረዳ እያገለገሉ ነው። አባቴ ከዚያ ሁሉ ዓመት በፊት ያቀረበው ጸሎት ተመልሶለታል።
መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ውስጣዊ ሰላም አገኛለሁ። አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ እንደ ኢየሱስ ‘ከበፊቱ ይበልጥ አጥብቄ’ መጸለይ እንዳለብኝ ተምሬያአለሁ። (ሉቃስ 22:44) ጸሎቴ መልስ የሚያገኝበት አንዱ መንገድ በናዴዥዳ፣ ሶፊያ ባለው ጉባኤ ውስጥ ያሉት ጓደኞቼ በሚያሳዩኝ ፍቅርና ደግነት አማካኝነት ነው። አብሬያቸው ጊዜ እንዳሳልፍ ይጋብዙኛል፤ እንዲሁም ብዙ ጊዜ አድናቆታቸውን ይገልጹልኛል። ይህም ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልኛል።
በትንሣኤ ተስፋ ላይ ብዙ ጊዜ አሰላስላለሁ። ወላጆቼ በሠርጋቸው ቀን የነበረውን ያህል ውብ ሆነው በቤታችን ፊት ለፊት ቆመው ይታዩኛል። እህቴ ምግብ ስታዘጋጅ ይታየኛል። ሃይንዝ ደግሞ ፈረሱ አጠገብ ቆሞ ይታየኛል። እንዲህ ያሉትን ነገሮች በዓይነ ሕሊናዬ መሣሌ አፍራሽ ስሜቶችን እንዳስወግድና ልቤ ለይሖዋ ባለኝ የአመስጋኝነት ስሜት እንዲሞላ ይረዳኛል።
ያሳለፍኩትን ሕይወት መለስ ብዬ ሳስታውስ እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሳስብ ዳዊት በመዝሙር 27:13, 14 ላይ በተናገራቸው በሚከተሉት ቃላት በሙሉ ልቤ እስማማለሁ፦ “በሕያዋን ምድር የይሖዋን ጥሩነት አያለሁ የሚል እምነት ባይኖረኝ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር! ይሖዋን ተስፋ አድርግ፤ ደፋር ሁን፤ ልብህም ይጽና። አዎ፣ ይሖዋን ተስፋ አድርግ።”
a የታትያና ቪሌስካን የሕይወት ታሪክ ለማንበብ የታኅሣሥ 2000 ንቁ! ከገጽ 26-30ን ተመልከት።