የጥናት ርዕስ 41
መዝሙር 108 የአምላክ ታማኝ ፍቅር
የአምላክ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል
“ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—መዝ. 136:1
ዓላማ
የይሖዋ ፍቅር መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሆኑን ማስታወሳችን መከራ ሲያጋጥመን ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
1-2. ብዙ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል?
በኃይለኛ ማዕበል ውስጥ የሚጓዝን አንድ ጀልባ ለማሰብ ሞክር። ሞገዱ ጀልባውን ወዲያና ወዲህ እያናወጠው ነው። አንድ ሰው የጀልባውን መልሕቅ ካልጣለ በቀር ጀልባው ሞገዱ ወደወሰደው መሄዱ አይቀርም። መልሕቅ ማዕበሉ ባይቆምም ጀልባው ባለበት እንዲቆይ ያደርገዋል።
2 የሚያናውጥ መከራ ሲገጥምህ እንደዚህ ጀልባ እንደሆንክ ሊሰማህ ይችላል። ስሜትህ ወዲያው ወዲያው ሊቀያየር ይችላል። አንዳንድ ቀን፣ ይሖዋ እንደሚወድህና እንደሚደግፍህ እርግጠኛ ትሆናለህ። አንዳንድ ቀን ደግሞ፣ ያለህበትን ሁኔታ ጨርሶ እንደማያይ ሊሰማህ ይችላል። (መዝ. 10:1፤ 13:1) ምናልባት አንድ ጓደኛህ ሲያበረታታህ ስሜትህ ይረጋጋ ይሆናል። (ምሳሌ 17:17፤ 25:11) ብዙም ሳይቆይ ግን ጥርጣሬው ይመለስብሃል። ይባስ ብሎም፣ ይሖዋ ጨርሶ እንደተወህ ሊሰማህ ይችላል። ታዲያ መከራ ሲያጋጥምህ በምሳሌያዊ ሁኔታ መልሕቅህን መጣል የምትችለው እንዴት ነው? በሌላ አባባል፣ ይሖዋ እንደሚወድህና እንደሚደግፍህ እርግጠኛ መሆንና እርግጠኛ ሆነህ መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው?
3. በመዝሙር 31:7 እና 136:1 ላይ የሚገኘው “ታማኝ ፍቅር” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? ታማኝ ፍቅር በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ ነው የምንለውስ ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
3 መከራ ሲያጋጥምህ መልሕቅህን መጣል የምትችልበት አንዱ መንገድ የይሖዋን ታማኝ ፍቅር በማስታወስ ነው። (መዝሙር 31:7፤ 136:1ን አንብብ።) “ታማኝ ፍቅር” የሚለው አገላለጽ በሁለት አካላት መካከል የሚኖረውን ጥልቅና ዘላቂ የሆነ ቁርኝት ያመለክታል። ታማኝ ፍቅር በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ‘ታማኝ ፍቅሩ እጅግ ብዙ እንደሆነ’ ይናገራል። (ዘፀ. 34:6, 7) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “አንተን ለሚጠሩ ሁሉ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን የለውም።” (መዝ. 86:5) ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስብ፦ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን መቼም ቢሆን አይተዋቸውም! ይሖዋ ታማኝ መሆኑን ማስታወስህ የሚያናውጥ ፈተና ሲያጋጥምህ እንደ መልሕቅ አጽንቶ ያቆምሃል።—መዝ. 23:4
መልሕቅ ማዕበል ሲነሳ አንድ ጀልባ ቦታውን እንዳይለቅ እንደሚከላከል ሁሉ ይሖዋ እንደሚወደን እርግጠኞች መሆናችን መከራ ሲደርስብን እንዳንናወጥ ይረዳናል (አንቀጽ 3ን ተመልከት)
የይሖዋ ፍቅር መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደሆነ አስታውስ
4. መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? የማንጠራጠራቸውስ ለምንድን ነው?
4 በፈተና ወቅት መልሕቅህን መጣል የምትችልበት ሌላኛው መንገድ የይሖዋ ፍቅር መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደሆነ በማስታወስ ነው። “መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት” የሚለውን አገላለጽ ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባት ከአምላክ ቃል የተማርካቸውን መሠረተ ትምህርቶች ታስታውስ ይሆናል። ለምሳሌ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ፣ ኢየሱስ የአምላክ አንድያ ልጅ እንደሆነ፣ ሙታን ምንም እንደማያውቁ እንዲሁም ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆንና ሰዎች ለዘላለም በምድር ላይ እንደሚኖሩ ተምረሃል። (መዝ. 83:18፤ መክ. 9:5፤ ዮሐ. 3:16፤ ራእይ 21:3, 4) እነዚህን ትምህርቶች አንዴ ከተቀበልክ በኋላ በእነዚህ ትምህርቶች ላይ ጥርጣሬ አላደረብህም። ለምን? ምክንያቱም ትምህርቶቹ የተመሠረቱት በእውነታ ላይ እንደሆነ ተገንዝበሃል። የይሖዋ ፍቅር መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደሆነ ማስታወስህ ይሖዋ ስላለህበት ሁኔታ ግድ እንደማይሰጠው ወይም ጨርሶ እንደማያየው ሲሰማህ ይህን ስሜት ለማሸነፍ የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
5. የሐሰት ትምህርቶች የሚደረመሱት እንዴት እንደሆነ ግለጽ።
5 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር የሐሰት ትምህርቶችን ለመተው የረዳህ ምንድን ነው? የቀድሞ ሃይማኖትህ ያስተማረህን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ነገር ጋር ማነጻጸርህ ጠቅሞህ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው ብለህ ታምን ነበር እንበል። መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ግን ‘ይህ ትምህርት በእርግጥ እውነት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠየቅክ። ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን ከመረመርክ በኋላ ትምህርቱ እውነት እንዳልሆነ ተገነዘብክ። ከዚያም ያንን የሐሰት ትምህርት በሚከተለው ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ተካኸው፦ ኢየሱስ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” እና ‘የአምላክ አንድያ ልጅ’ ነው። (ቆላ. 1:15፤ ዮሐ. 3:18) እርግጥ ነው፣ የሐሰት ትምህርቶች እንደ “ምሽግ” ለመደርመስ አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ። (2 ቆሮ. 10:4, 5) አንዴ ካፈረስካቸው በኋላ ግን ወደተውካቸው የሐሰት ትምህርቶች አልተመለስክም።—ፊልጵ. 3:13
6. የይሖዋ ‘ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር’ መተማመን የምትችለው ለምንድን ነው?
6 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ፍቅር ከሚያስተምረው ነገር ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ ዘዴ መጠቀም ትችላለህ። መከራ አጋጥሞህ ይሖዋ እንደሚወድህ መጠራጠር ከጀመርክ ‘አስተሳሰቤ ጤናማ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ስለ ይሖዋ ፍቅር የተፈጠረብህን ጥርጣሬ የዚህ የጥናት ርዕስ የጭብጥ ጥቅስ ከሆነው ከመዝሙር 136:1 አንጻር እየው። ይሖዋ ፍቅሩ “ታማኝ” እንደሆነ የገለጸው ለምንድን ነው? “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” የሚለው አገላለጽ እዚያ መዝሙር ላይ 26 ጊዜ የተደጋገመው ለምንድን ነው? እስካሁን እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ ለሕዝቡ የሚያሳየው ታማኝ ፍቅር መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው። በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙትና አምነን ከተቀበልናቸው መሠረተ ትምህርቶች አንዱ ነው። ‘ይሖዋ አይወድህም’ ወይም ‘ቦታ አይሰጥህም’ የሚለው ሐሳብ የሐሰት ትምህርት ነው። ሌሎቹን የሐሰት ትምህርቶች እንደምትቃወመው ሁሉ ይህንንም ትምህርት አጥብቀህ ተቃወመው!
7. ይሖዋ እንደሚወደን የሚያረጋግጡ አንዳንድ ጥቅሶችን ጥቀስ።
7 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ እንደሚወደን የሚያረጋግጡ ሌሎች በርካታ ሐሳቦችንም ይዟል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ተከታዮቹን “እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 10:31) ይሖዋ ራሱም ሕዝቡን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤ በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ።” (ኢሳ. 41:10) እነዚህ አገላለጾች የማያሻሙ እንደሆኑ ልብ በል። ኢየሱስ ‘የላቀ ዋጋ ሊኖራችሁ ይችላል’ አላለም፤ ይሖዋም ቢሆን ‘እረዳህ ይሆናል’ አላለም። ከዚህ ይልቅ ሁለቱም ያሉት “የላቀ ዋጋ አላችሁ” እንዲሁም “እረዳሃለሁ” ነው። መከራ በሚያጋጥምህ ጊዜ ይሖዋ የሚወድህ መሆኑን ከተጠራጠርክ እንዲህ ያሉት ጥቅሶች ይሖዋ እንደሚወድህ እንዲሰማህ ከማድረግ ባለፈ እሱ እንደሚወድህ እርግጠኛ እንድትሆንም ይረዱሃል። ጥቅሶቹ በእውነታ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በጸሎት ታግዘህ በዚህ ላይ የምታሰላስል ከሆነ በ1 ዮሐንስ 4:16 ላይ የሚገኙትን የሚከተሉትን ቃላት ለማስተጋባት ትነሳሳለህ፦ “አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል፤ እንዲሁም አምነናል።”a
8. ይሖዋ የሚወድህ መሆኑን አልፎ አልፎ የምትጠራጠር ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?
8 ሆኖም እነዚህን ነገሮች አድርገህም አልፎ አልፎ ይሖዋ የሚወድህ መሆኑን ብትጠራጠርስ? የሚሰማህን ስሜት ከምታውቀው ነገር ጋር አወዳድር። ስሜት የእውነታን ያህል አስተማማኝ አይደለም። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚናገሩት ይሖዋ የሚወደን መሆኑ እውነታ ነው። ይህን አለመቀበል የይሖዋን ዋነኛ ባሕርይ ይኸውም ፍቅሩን እንደ መርሳት ይቆጠራል።—1 ዮሐ. 4:8
ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ፍቅር በተናገረው ነገር ላይ አሰላስል
9-10. በዮሐንስ 16:26, 27 ላይ የሚገኘው “አብ ራሱ ይወዳችኋል” የሚለው ጥቅስ አውድ ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
9 ኢየሱስ ለተከታዮቹ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ በመመርመር ስለ ይሖዋ ፍቅር ይበልጥ መማር እንችላለን፦ “አብ ራሱ ይወዳችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 16:26, 27ን አንብብ።) ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ደቀ መዛሙርቱ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ብቻ አይደለም። እንዲያውም ከአውዱ እንደምንረዳው ኢየሱስ በዚያ ወቅት እየተናገረ የነበረው ስለ ስሜታቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ እየተናገረ የነበረው ስለ ሌላ ጉዳይ ይኸውም ስለ ጸሎት ነው።
10 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ሳይሆን በእሱ በኩል መጸለይ እንዳለባቸው ነገራቸው። (ዮሐ. 16:23, 24) ይህን ማወቃቸው በጣም አስፈላጊ ነበር። ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ለመጸለይ ሊፈተኑ ይችላሉ። ምክንያቱም ኢየሱስ ወዳጃቸው ነው። እነሱን ስለሚወዳቸው ልመናቸውን ሰምቶ ወደ አባቱ ለማቅረብ እንደሚነሳሳ ሊያስቡ ይችሉ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ብለው ማሰብ እንደሌለባቸው ነገራቸው። ለምን? ኢየሱስ ምክንያቱን ሲገልጽ “አብ ራሱ ይወዳችኋል” አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸሎት ከሚያስተምራቸው ነገሮች አንዱ ይህ ነው። ታዲያ ይህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ኢየሱስን ማወቅና መውደድ ችለሃል። (ዮሐ. 14:21) ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ደቀ መዛሙርት ይሖዋ ‘ራሱ እንደሚወድህ’ በመተማመን በልበ ሙሉነት ወደ እሱ መጸለይ ትችላለህ። ወደ ይሖዋ በጸለይክ ቁጥር በእነዚህ ቃላት ላይ ያለህን እምነት እያሳየህ ነው።—1 ዮሐ. 5:14
ይሖዋ ‘ራሱ እንደሚወድህ’ በመተማመን በልበ ሙሉነት ወደ እሱ መጸለይ ትችላለህ (አንቀጽ 9-10ን ተመልከት)b
ጥርጣሬ የሚመነጨው ከየት እንደሆነ ተረዳ
11. ይሖዋ የሚወደን መሆኑን ብንጠራጠር ሰይጣን የሚደሰተው ለምንድን ነው?
11 ይሖዋ የሚወደን መሆኑን እንድንጠራጠር ሊያደርገን የሚችለው ምንድን ነው? እንዲህ ያለው ጥርጣሬ የሚመነጨው ከሰይጣን ነው ብለህ ትመልስ ይሆናል፤ ደግሞም ይህ በተወሰነ መጠን እውነትነት አለው። ዲያብሎስ ‘ሊውጠን ይፈልጋል’፤ እንዲሁም ይሖዋ የሚወደን መሆኑን ብንጠራጠር ደስ ይለዋል። (1 ጴጥ. 5:8) ይሖዋ ቤዛውን የሰጠን ስለሚወደን ነው፤ ሰይጣን ደግሞ ቤዛው እንደማይገባን ሆኖ እንዲሰማን ይፈልጋል። (ዕብ. 2:9) ይሖዋ የሚወደን መሆኑን ብንጠራጠር የሚጠቀመው ማን ነው? ሰይጣን ነው። ደግሞስ በችግር ጊዜ ተስፋ ብንቆርጥ የማን ዓላማ ነው የሚሳካው? የሰይጣን ነው። ሰይጣን፣ ይሖዋ እንደማይወደን እንድናስብ የሚፈልግ መሆኑ አያስገርምም? ይሖዋ የማይወደው ሰይጣንን ራሱን ነው። ሆኖም ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው “መሠሪ ዘዴዎች” አንዱ ይሖዋ እኛን እንደማይወደንና እንደማይፈልገን እንድናስብ ማድረግ ነው። (ኤፌ. 6:11) ጠላታችን ምን ለማድረግ እየሞከረ እንዳለ ስንገነዘብ ‘ዲያብሎስን ለመቃወም’ ያለን ቁርጠኝነት ይጠናከራል።—ያዕ. 4:7
12-13. የወረስነው ኃጢአት ይሖዋ የሚወደን መሆኑን እንድንጠራጠር ሊያደርገን የሚችለው እንዴት ነው?
12 ይሖዋ የሚወደን መሆኑን እንድንጠራጠር ሊያደርገን የሚችል ሌላም ነገር አለ። ምን ይሆን? የወረስነው ኃጢአት ነው። (መዝ. 51:5፤ ሮም 5:12) ኃጢአት የሰውን ዘር ከፈጣሪው አርቆታል። በአእምሯችን፣ በልባችንና በአካላችን ላይም ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል።
13 ኃጢአት በስሜታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ የበደለኝነት፣ የጭንቀት፣ የስጋትና የኀፍረት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። ኃጢአት ስንፈጽም እነዚህ ስሜቶች ሊሰሙን ይችላሉ። ሆኖም ኃጢአተኞች መሆናችንን ማሰባችን በራሱ እነዚህ ስሜቶች እንዲሰሙን ሊያደርግ ይችላል፤ ምክንያቱም ኃጢአት ይሖዋ ሰዎችን ከፈጠረበት መንገድ ጋር ፈጽሞ አይጣጣምም። (ሮም 8:20, 21) የተነፈሰ ጎማ ያለው መኪና በተገቢው መንገድ መንቀሳቀስ እንደማይችል ሁሉ እኛም ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ስንፈጠር በነበረን ሙሉ አቅም መሥራት አንችልም። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ የሚወደን መሆኑን ብንጠራጠር የሚያስገርም አይደለም። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመን ይሖዋ ‘ለሚወዱትና ትእዛዛቱን ለሚያከብሩ ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ ታላቅና የሚፈራ አምላክ’ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል።—ነህ. 1:5
14. በቤዛው ላይ ማሰላሰላችን ‘ይሖዋ ፈጽሞ ሊወደኝ አይችልም’ የሚለውን ሐሳብ ለማሸነፍ የሚረዳን እንዴት ነው? (ሮም 5:8) (“‘ኃጢአት ካለው የማታለል ኃይል’ ራስህን ጠብቅ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
14 እውነት ነው፣ አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ ፍቅር የሚገባን ሰዎች እንዳልሆንን ሊሰማን ይችላል። ደግሞም እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የአምላክ ፍቅር የሚገባን ሰዎች አይደለንም። የይሖዋን ፍቅር በጣም ልዩ የሚያደርገው ይህ ነው። ምንም ብናደርግ በራሳችን ጥረት የይሖዋን ፍቅር ማግኘት አንችልም። ያም ቢሆን ቤዛው ኃጢአታችንን ይሸፍንልናል፤ ይሖዋ ይህን ዝግጅት ያደረገው ደግሞ ስለሚወደን ነው። (1 ዮሐ. 4:10) በተጨማሪም ኢየሱስ የመጣው ፍጹም ሰዎችን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ለማዳን እንደሆነ አስታውስ። (ሮም 5:8ን አንብብ።) ማናችንም ነገሮችን ፍጹም በሆነ መንገድ ማከናወን አንችልም፤ ይሖዋም ቢሆን እንዲህ እንድናደርግ አይጠብቅብንም። ኃጢአተኛ መሆናችን ይሖዋ የሚወደን መሆኑን እንድንጠራጠር ሊያደርገን እንደሚችል ስንገነዘብ ኃጢአት አስተሳሰባችንን እንዳይቆጣጠረው መታገላችንን ለመቀጠል ይበልጥ ቁርጠኞች እንሆናለን።—ሮም 7:24, 25
ምንጊዜም ታማኝ ለመሆን ምረጥ
15-16. ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ከቀጠልን ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን እንችላለን? ለምንስ? (2 ሳሙኤል 22:26)
15 ይሖዋ “ከእሱ ጋር በመጣበቅ” ትክክለኛ ምርጫ እንድናደርግ ይፈልጋል። (ዘዳ. 30:19, 20) እንዲህ ካደረግን እሱም ለእኛ ምንጊዜም ታማኝ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። (2 ሳሙኤል 22:26ን አንብብ።) ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እስከቀጠልን ድረስ በሕይወታችን ውስጥ በሚያጋጥመን በማንኛውም ሁኔታ እንደሚረዳን ልንተማመንበት እንችላለን።
16 እስካሁን እንደተመለከትነው፣ መከራ ሲያጋጥመን በምሳሌያዊ ሁኔታ መልሕቃችንን ጥለን ተረጋግተን ለመኖር የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት አለን። ይሖዋ እንደሚወደንና እንደሚደግፈን እናውቃለን። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ይህንኑ ነው። ይሖዋ የሚወደን መሆኑን ከተጠራጠርን በስሜታችን ላይ ከማተኮር ይልቅ ስለ ይሖዋ ፍቅር በምናውቀው ነገር ላይ ማሰላሰል እንችላለን። እንግዲያው የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተማምነን እንኑር።
መዝሙር 159 ለይሖዋ ክብር ስጡ
a ሌሎች ምሳሌዎችን ለማግኘት ዘዳግም 31:8ን፣ መዝሙር 94:14ን እና ኢሳይያስ 49:15ን አንብብ።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም የታመመች ሚስቱን ለመንከባከብ፣ ገንዘቡን በጥበብ ለመያዝ እንዲሁም ልጁ ይሖዋን እንድትወድ ለማሠልጠን እንዲረዳው ወደ አምላክ ሲጸልይ።