የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ኅዳር ገጽ 2-7
  • በእርጅና ዘመናችሁ ደስታችሁን ጠብቁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በእርጅና ዘመናችሁ ደስታችሁን ጠብቁ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እርጅና ደስታችሁን ሊያሳጣችሁ የሚችለው እንዴት ነው?
  • ደስተኛ ሆናችሁ መቀጠል የምትችሉት እንዴት ነው?
  • ሌሎች እርዳታ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?
  • ታማኝ አረጋውያንን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • ታማኝ ሰዎች ከተናገሯቸው የስንብት ቃላት ተማሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ይሖዋ አረጋዊ ለሆኑ አገልጋዮቹ በጥልቅ ያስባል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ኅዳር ገጽ 2-7

የጥናት ርዕስ 44

መዝሙር 138 ሽበት ያለው ውበት

በእርጅና ዘመናችሁ ደስታችሁን ጠብቁ

‘ባረጁ ጊዜ ያብባሉ።’—መዝ. 92:14

ዓላማ

አረጋውያን ደስታቸውን ጠብቀው መኖራቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግ የሚችሉትስ እንዴት ነው?

1-2. ይሖዋ በዕድሜ ለገፉ ታማኝ አገልጋዮቹ ምን አመለካከት አለው? (መዝሙር 92:12-14፤ ሥዕሉንም ተመልከት።)

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎች ለእርጅና የተለያየ አመለካከት አላቸው። ለምሳሌ በፀጉራችሁ ላይ የመጀመሪያዋን ሽበት ያያችሁበት ጊዜ ትዝ ይላችኋል? ማንም ሰው ሳያይባችሁ በፊት ሽበቷን ለመንቀል ተፈትናችሁ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሽበትን መንቀል ፀጉራችሁ እንዳይሸብት እንደማያደርገው መገንዘባችሁ አይቀርም። ይህ ምሳሌ ብዙዎች እርጅናን መቀበል እንደሚከብዳቸው ያሳያል።

2 ይሁንና የሰማዩ አባታችን በዕድሜ ለገፉ አገልጋዮቹ ምን ዓይነት አመለካከት አለው? (ምሳሌ 16:31) ይሖዋ አረጋውያንን ከሚያብቡ ዛፎች ጋር አመሳስሏቸዋል። (መዝሙር 92:12-14ን አንብብ።) ይህ ንጽጽር ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው? በቅጠሎችና ማራኪ የሆነ መዓዛ ባላቸው አበቦች የተሞሉ ዛፎች ብዙውን ጊዜ በርካታ አሥርተ ዓመታትን ያስቆጠሩ ናቸው። ለምሳሌ ጃፓን ውስጥ የሚበቅል ለረጅም ዘመን የሚኖር አንድ ዛፍ አለ። አንዳንዶቹ ዛፎች ዕድሜያቸው ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ ሲሆን በጣም ያምራሉ። እንደነዚህ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ሁሉ በዕድሜ የገፉ ታማኝ ሰዎችም በተለይ በአምላክ ዓይን በጣም ውብ ናቸው። ይሖዋ የሚመለከተው ሽበታቸውን ብቻ አይደለም። አረጋውያን ያሏቸውን መልካም ባሕርያት ያደንቃል፤ ጽናታቸውን፣ ታማኝነታቸውን እንዲሁም ለበርካታ ዓመታት ያቀረቡትን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከታል።

አንድ አረጋዊ ባልና ሚስት ደጅ ባለ ወንበር ላይ ተቀምጠው፤ በዙሪያቸው በአበባ የተሞሉ ዛፎች አሉ።

ማበባቸውን እንደሚቀጥሉና ውብ እንደሆኑ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ታማኝ አረጋውያንም ውብ ናቸው፤ ማበባቸውንም ይቀጥላሉ (አንቀጽ 2ን ተመልከት)


3. ይሖዋ ዓላማውን ለማስፈጸም በዕድሜ የገፉ ሰዎችን እንደተጠቀመ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

3 አንድ ሰው በዕድሜ እየገፋ ሲሄድ በይሖዋ ዘንድ ያለው ዋጋ እየቀነሰ አይሄድም።a እንዲያውም ይሖዋ ብዙውን ጊዜ ዓላማውን ለማስፈጸም በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ይጠቀማል። ለምሳሌ ይሖዋ፣ ሣራ የአንድ ኃያል ብሔር እናትና የመሲሑ ቅድመ አያት እንደምትሆን በተናገረበት ጊዜ ሣራ በዕድሜ ገፍታ ነበር። (ዘፍ. 17:15-19) ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብፅ እንዲያወጣ በይሖዋ ሲሾም ዕድሜው ገፍቶ ነበር። (ዘፀ. 7:6, 7) ሐዋርያው ዮሐንስም በይሖዋ መንፈስ ተመርቶ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ሲጽፍ አርጅቶ ነበር።

4. በምሳሌ 15:15 መሠረት በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚገጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም ምን ይረዳቸዋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 አረጋውያን ከዕድሜ መግፋት ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ብዙ ጊዜ “እርጅና ብቻህን ና” ሲባል እንሰማለን። ሆኖም አረጋውያን ደስተኞችb ሆነው መቀጠላቸው በዕድሜ መግፋት ሳቢያ የሚመጡ ችግሮችን ለመቋቋም ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 15:15ን አንብብ።) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ደስታቸውን ጠብቀው ለመኖር የትኞቹን ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚችሉ እንመለከታለን። እንዲሁም ሌሎቻችን በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶችን መርዳት የምንችልበትን መንገድ እናያለን። በመጀመሪያ ግን፣ ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ደስታችንን መጠበቅ ተፈታታኝ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመልከት።

ቀደም ባለው ሥዕል ላይ የታዩት ባልና ሚስት በአበባ በተሞላ ዛፍ ሥር እጅ ለእጅ ተያይዘው ቆመዋል፤ ፊታቸው ላይ ፈገግታ ይነበባል።

አረጋውያን ደስተኞች መሆናቸው ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን በጽናት እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል (አንቀጽ 4ን ተመልከት)


እርጅና ደስታችሁን ሊያሳጣችሁ የሚችለው እንዴት ነው?

5. አንዳንድ አረጋውያን ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል?

5 ተስፋ እንድትቆርጡ ሊያደርጋችሁ የሚችለው ምንድን ነው? በአንድ ወቅት ታደርጓቸው የነበሩ ነገሮችን ማድረግ አለመቻላችሁ ሊያሳዝናችሁ ይችላል። ወጣትና ጤናማ የነበራችሁበትን ጊዜ ትናፍቁ ይሆናል። (መክ. 7:10) ለምሳሌ ሩቢ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ሁለመናዬን ስለሚያመኝ እንዲሁም ሰውነቴ ስለማይታዘዝልኝ ልብስ ለመልበስ እቸገራለሁ። እግሬን አንስቼ ካልሲ እንደማድረግ ያሉ ቀላል ነገሮች እንኳ በጣም ይከብዱኛል። እጄን ይደነዝዘኛል፤ እንዲሁም አርትራይተስ አለብኝ፤ ይህ ደግሞ ትናንሽ ነገሮችን እንኳ እንዳላከናውን አግዶኛል።” በቤቴል ያገለግል የነበረው ሃሮልድ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ሌላ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል፤ ይህም አንዳንድ ጊዜ ያበሳጨኛል። ወጣት እያለሁ በጣም ጠንካራ ነበርኩ። በትርፍ ጊዜዬ ቤዝቦል መጫወት በጣም ነበር የምወደው። አብረውኝ የሚጫወቱት ሰዎች ‘ለሃሮልድ ኳሱን ስጡት፤ እሱ ፈጽሞ አይስትም’ ይሉ ነበር። አሁን ግን ኳሱን መወርወር የምችል እንኳ አይመስለኝም።”

6. (ሀ) አንዳንድ አረጋውያን ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጓቸው ሌሎች ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) አረጋውያን መኪና መንዳታቸውን ማቆም ይኖርባቸው እንደሆነ ለመወሰን ምን ይረዳቸዋል? (በዚህ መጽሔት ውስጥ የሚገኘውን “መኪና መንዳቴን ማቆም ይኖርብኝ ይሆን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።)

6 የሌሎች ጥገኛ እንደሆናችሁ ከተሰማችሁ ተስፋ ልትቆርጡ ትችላላችሁ። በተለይ ደግሞ የሚንከባከባችሁ ሰው ካስፈለጋችሁ ወይም ልጆቻችሁ ጋር ለመኖር ከተገደዳችሁ እንዲህ ሊሰማችሁ ይችላል። የጤናችሁ ሁኔታ ወይም የማየት ችሎታችሁ በማሽቆልቆሉ የተነሳ ወደተለያዩ ቦታዎች ብቻችሁን መሄድ ወይም መኪና መንዳት ባለመቻላችሁ በጣም ልታዝኑ ትችላላችሁ። ሆኖም በይሖዋና በሌሎች ዘንድ ያላችሁ ዋጋ የተመካው ራሳችሁን መንከባከብ፣ ብቻችሁን መኖር ወይም መኪና መንዳት በመቻላችሁ ላይ እንዳልሆነ ማስታወሳችሁ ይረዳችኋል። በተጨማሪም ይሖዋ ስሜታችሁን እንደሚረዳላችሁ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ። ይሖዋ የሚመለከተው ውስጣዊ ማንነታችሁን ነው። ለእሱም ሆነ ለእምነት አጋሮቻችሁ ያላችሁን ፍቅርና አድናቆት ከፍ አድርጎ ይመለከታል።—1 ሳሙ. 16:7

7. እስከ ሥርዓቱ ፍጻሜ በሕይወት ላይቆዩ እንደሚችሉ በማሰብ የሚያዝኑ አረጋውያንን ምን ሊረዳቸው ይችላል?

7 ምናልባት እስከ ሥርዓቱ ፍጻሜ ድረስ በሕይወት ላትቆዩ እንደምትችሉ በማሰብ ልታዝኑ ትችላላችሁ። እንዲህ የሚሰማችሁ ከሆነ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት የሚያጠፋበትን ጊዜ በትዕግሥት እየተጠባበቀ ያለው በምክንያት እንደሆነ ለማስታወስ ሞክሩ። (ኢሳ. 30:18) ይሁንና ይሖዋ የታገሠበት ምክንያት ምንድን ነው? እሱ በመታገሡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እሱን ማወቅና ማገልገል የሚችሉበት ጊዜና አጋጣሚ አግኝተዋል። (2 ጴጥ. 3:9) በመሆኑም አርማጌዶን ቶሎ አለመምጣቱ ሲያሳስባችሁ ይሖዋ በመታገሡ ምን ያህል ሰዎች ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ለማሰብ ሞክሩ። ምናልባትም ከእነዚህ መካከል የቤተሰባችሁ አባላት ይገኙበት ይሆናል።

8. አረጋውያን በሚያጋጥሟቸው የጤና ችግሮች የተነሳ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

8 ወጣቶችም ሆንን አረጋውያን፣ በምንታመምበት ጊዜ የምንጸጸትበትን ነገር የመናገራችን ወይም የማድረጋችን አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። (መክ. 7:7፤ ያዕ. 3:2) ለምሳሌ ታማኙ ኢዮብ መከራ በደረሰበት ወቅት ‘እንዳመጣለት’ ተናግሯል። (ኢዮብ 6:1-3) በመሆኑም አረጋውያን ባለባቸው የጤና እክል ወይም በሚወስዱት መድኃኒት ምክንያት ከባሕርያቸው ውጭ የሆኑ ነገሮችን ሊናገሩ ወይም ሊያደርጉ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ ዕድሜያችን ወይም የጤንነታችን ሁኔታ ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ለመናገር ወይም ሁልጊዜ የሆነ ነገር እንዲደረግልን ለመጠበቅ ሰበብ ሊሆን አይገባም። እንዲሁም አንድን ሰው ፍቅር በጎደለው መንገድ እንዳነጋገርነው ከተሰማን ይቅርታ ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት አይኖርብንም።—ማቴ. 5:23, 24

ደስተኛ ሆናችሁ መቀጠል የምትችሉት እንዴት ነው?

በአበባ የተሞላ ዛፍ ቅርንጫፍ፤ በክቦቹ ውስጥ ያሉት ሥዕሎች በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች ደስታቸውን መጠበቅ የሚችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች ያሳያሉ። ሥዕሎቹ ከአንቀጽ 9-13 ባሉት አንቀጾች ላይ በድጋሚ ይታያሉ።

እርጅና የሚያስከትላቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ደስተኛ ሆናችሁ መቀጠል የምትችሉት እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 9-13ን ተመልከት)


9. የሌሎችን እርዳታ መቀበል የሚኖርባችሁ ለምንድን ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

9 የሌሎችን እርዳታ ተቀበሉ። (ገላ. 6:2) መጀመሪያ ላይ፣ እንዲህ ማድረግ ሊከብዳችሁ ይችላል። ግሬትል የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ከሌሎች እርዳታ መቀበል ይከብደኛል፤ ምክንያቱም ሸክም እንደሆንኩባቸው ይሰማኛል። አስተሳሰቤን ለማስተካከልና የሌሎች እርዳታ እንደሚያስፈልገኝ በትሕትና አምኜ ለመቀበል ጊዜ ወስዶብኛል።” የሌሎችን እርዳታ ስትቀበሉ በመስጠት የሚገኘውን ደስታ እንዲያጣጥሙ አጋጣሚ ትሰጧቸዋላችሁ። (ሥራ 20:35) እንዲሁም ሌሎች ምን ያህል እንደሚወዷችሁና እንደሚያስቡላችሁ ስትመለከቱ በጣም እንደምትደሰቱ ጥያቄ የለውም።

አንዲት አረጋዊት እህት የአንዲትን ወጣት እህት እጅ ይዛ አስቤዛ ስትሸምት።

(አንቀጽ 9ን ተመልከት)


10. አስታውሳችሁ አመስጋኝነታችሁን መግለጻችሁ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

10 አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ። (ቆላ. 3:15፤ 1 ተሰ. 5:18) ሌሎች ለሚያደርጉልን መልካም ነገር አመስጋኝ ልንሆን እንችላለን፤ ሆኖም አመስጋኝነታችንን ማሳየት እንረሳ ይሆናል። ነገር ግን ፈገግ ብለን “አመሰግናለሁ” ካልናቸው እርዳታቸውን እንደምናደንቅ ይገነዘባሉ። በቤቴል ያሉ አረጋውያንን የምትንከባከበው ሊያ እንዲህ ብላለች፦ “ከምንከባከባቸው እህቶች መካከል አንዷ አጫጭር የምስጋና መልእክቶችን ጽፋ ታስቀምጥልኛለች። መልእክቶቹ ረጅም አይደሉም፤ ግን ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ናቸው። መልእክቶቹን ሳነብ በጣም ደስ ይለኛል፤ የማደርግላትን እርዳታ እንደምታደንቅ ማየቴም ያስደስተኛል።”

አንዲት አረጋዊት እህት የምስጋና ፖስት ካርድ ላይ ስትጽፍ።

(አንቀጽ 10ን ተመልከት)


11. ሌሎችን መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

11 ሌሎችን ለመርዳት ጥረት አድርጉ። ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን ተጠቅማችሁ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ስታደርጉ በራሳችሁ ችግሮች ላይ እምብዛም አታተኩሩም። አረጋውያንን እንደ “ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻሕፍት” ልንቆጥራቸው እንችላለን፤ በውስጣቸው ብዙ የተከማቸ ጥበብ አለ። ይሁንና በመደርደሪያ ላይ የተቀመጡ መጻሕፍት ተገልጠው ካልተነበቡ ምንም ጥቅም አይኖራቸውም። በመሆኑም ቅድሚያውን ወስዳችሁ እውቀታችሁንና ተሞክሯችሁን ለወጣቶች ለማካፈል ጥረት አድርጉ። ጥያቄዎችን ጠይቋቸው፤ ከዚያም አዳምጧቸው። በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት ሁልጊዜም ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝና ደስተኛ እንደሚያደርጋቸው ንገሯቸው። ወጣቶችን ማጽናናታችሁና ማበረታታታችሁ ደስታ እንደሚሰጣችሁ ጥርጥር የለውም።—መዝ. 71:18

አንድ አረጋዊ ወንድም አንድ ወጣት ወንድም ስሜቱን ሲገልጽ ሲያዳምጠው።

(አንቀጽ 11ን ተመልከት)


12. በኢሳይያስ 46:4 መሠረት ይሖዋ ለአረጋውያን ምን እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

12 ይሖዋ ብርታት እንዲሰጣችሁ ጸልዩ። አካላችሁ ወይም ስሜታችሁ ሊዝል ቢችልም ይሖዋ ግን “ፈጽሞ አይደክምም ወይም አይዝልም።” (ኢሳ. 40:28) ታዲያ ይሖዋ ገደብ የለሽ የሆነ ኃይሉን የሚጠቀምበት እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ለታማኝ አረጋውያን ብርታት ለመስጠት ነው። (ኢሳ. 40:29-31) እንዲያውም እንደሚረዳቸው ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 46:4ን አንብብ።) ደግሞም ይሖዋ ሁሌም ቃሉን ይጠብቃል። (ኢያሱ 23:14፤ ኢሳ. 55:10, 11) ስትጸልዩ ይሖዋ የሚያስፈልጋችሁን እርዳታ ያደርግላችኋል፤ በዚህ መንገድ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ያሳያችሁን ፍቅር ስታጣጥሙ ደስተኞች ትሆናላችሁ።

አንድ አረጋዊ ወንድም ሲጸልይ።

(አንቀጽ 12ን ተመልከት)


13. በ2 ቆሮንቶስ 4:16-18 መሠረት ምን ማስታወስ ይኖርባችኋል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

13 ያላችሁበት ሁኔታ ጊዜያዊ እንደሆነ አስታውሱ። ያጋጠመን ከባድ ሁኔታ ጊዜያዊ እንደሆነ ካስታወስን ሁኔታውን በጽናት መቋቋም ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ እርጅናና ሕመም ጊዜያዊ ነገሮች እንደሆኑ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ኢዮብ 33:25፤ ኢሳ. 33:24) ስለዚህ ወደፊት፣ በወጣትነታችሁ ከነበራችሁ ይበልጥ ጤንነት፣ ጥንካሬና ውበት እንደሚኖራችሁ በማሰብ መደሰት ትችላላችሁ። (2 ቆሮንቶስ 4:16-18ን አንብብ።) ሆኖም እናንተን ለመርዳት ሌሎች ምን ማድረግ ይችላሉ?

አንዲት አረጋዊት እህት ዊልቼር ላይ ተቀምጣ መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ። በገነት ውስጥ ወጣት ሆና ከዊልቼሯ ተነስታ ስትራመድ በዓይነ ሕሊናዋ ይታያታል።

(አንቀጽ 13ን ተመልከት)


ሌሎች እርዳታ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?

14. አረጋውያንን ሄደን መጠየቃችን ወይም ለእነሱ መደወላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ለአረጋውያን ወንድሞችና እህቶች አዘውትራችሁ ደውሉላቸው፤ እንዲሁም ሄዳችሁ ጠይቋቸው። (ዕብ. 13:16) በዕድሜ የገፉ ሰዎች ብቸኝነት ሊሰማቸው ይችላል። ከቤት መውጣት የማይችል ካሚል የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ከጠዋት እስከ ማታ ቤት ውስጥ ነው የምውለው። ስለዚህ በጣም ይሰለቸኛል። አንዳንዴ በታጠረ ቤት ውስጥ እንዳለ ያረጀ አንበሳ የሆንኩ ይመስለኛል። በጭንቀትና በብስጭት እዋጣለሁ።” አረጋውያንን ሄደን ስንጠይቃቸው እንደሚያስፈልጉንና እንደምንወዳቸው እንዲሰማቸው እናደርጋለን። ሁላችንም በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኝን አንድ አረጋዊ ሄደን ለመጠየቅ ወይም ለእሱ ለመደወል ዕቅድ አውጥተን ሳይሳካልን የቀረበትን ጊዜ እናስታውስ ይሆናል። ሁላችንም የምንኖረው በውጥረት የተሞላ ሕይወት ነው። ታዲያ አረጋውያንን መጠየቅን ጨምሮ ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተን ለማወቅ’ ምን ሊረዳን ይችላል? (ፊልጵ. 1:10) በጉባኤያችን ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያን እንድንደውል ወይም የጽሑፍ መልእክት እንድንልክ እንዲያስታውሰን በቀን መቁጠሪያችን ላይ ምልክት ማድረግ እንችላለን። እነሱን ሄደን ለመጠየቅ ጊዜ መመደብም እንችላለን፤ ሁኔታዎች በራሳቸው እስኪመቻቹ መጠበቅ አይኖርብንም።

15. ወጣቶችና አረጋውያን አብረው ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

15 ወጣት ከሆናችሁ ከአረጋውያን ጋር ስለ ምን ልታወሩ ወይም በየትኞቹ እንቅስቃሴዎች ልትካፈሉ እንደምትችሉ ሊያሳስባችሁ ይችላል። ሆኖም ስለ እነዚህ ነገሮች ከልክ በላይ አትጨነቁ። ጥሩ ጓደኛ ለመሆን ጥረት አድርጉ። (ምሳሌ 17:17) ከጉባኤ ስብሰባዎች በፊትና በኋላ ከአረጋውያን ጋር ለመጨዋወት ጊዜ መድቡ። ምናልባት የሚወዱትን ጥቅስ ወይም በልጅነታቸው ያጋጠማቸውን አዝናኝ ገጠመኝ እንዲነግሯችሁ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። የJW ብሮድካስቲንግ ቪዲዮ አብረዋችሁ እንዲመለከቱም ልትጋብዟቸው ትችላላችሁ። በሌሎች ተግባራዊ መንገዶችም ልትረዷቸው ትችላላችሁ። ለምሳሌ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻቸው በትክክል መሥራታቸውን ልታረጋግጡላቸው ወይም አዳዲስ ጽሑፎችን ልታወርዱላቸው ትችላላችሁ። ካሮል የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ማድረግ የሚያስደስታችሁን ነገር አረጋውያን አብረዋችሁ እንዲያደርጉ ጋብዟቸው። ባረጅም እንኳ የሚያዝናኑ ነገሮችን ማድረግ እፈልጋለሁ። ወደ ገበያ አዳራሾች ሄጄ ዕቃ መሸመት፣ ምግብ ቤት ሄጄ መብላት እንዲሁም ወጣ ብዬ ተፈጥሮን ማድነቅ ያስደስተኛል።” ማይራ የተባለች እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከጓደኞቼ መካከል አንዷ 90 ዓመቷ ነው። በመካከላችን የ57 ዓመት የዕድሜ ልዩነት አለ። ሆኖም አብረን ስለምንስቅ እንዲሁም ፊልሞችን ስለምናይ የዕድሜ ልዩነት እንዳለን እረሳዋለሁ። ችግሮች ሲያጋጥሙን ደግሞ እርስ በርስ እንመካከራለን።”

16. አረጋውያን የሕክምና ቀጠሮ ሲኖራቸው አብረናቸው መሄዳችን ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

16 የሕክምና ቀጠሮ ሲኖራቸው አብራችኋቸው ሂዱ። አረጋውያንን ወደ ሕክምና ቦታ ከመውሰድ በተጨማሪ የሕክምና ባለሙያዎቹ በአክብሮት እንደሚይዟቸውና የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት እንደሚሰጧቸው አረጋግጡ። (ኢሳ. 1:17) ሐኪሙ የሚናገረውን ነገር ማስታወሻ በመያዝ አረጋውያኑን ልትረዷቸው ትችላላችሁ። ሩት የተባለች አንዲት አረጋዊት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ብዙውን ጊዜ ለሕክምና ቀጠሮ ብቻዬን ስሄድ ሐኪሙ የምናገረውን ነገር በቁም ነገር አይመለከተውም። አንዳንድ ጊዜ ሐኪሞች ‘ችግርሽ ሥነ ልቦናዊ ነው፤ በምናብሽ የፈጠርሽው ነው’ ይሉኛል። ከሌላ ሰው ጋር አብሬ ስሄድ ግን ሐኪሙ እኔን የሚይዝበት መንገድ በጣም ይቀየራል። ጊዜያቸውን ሠውተው አብረውኝ የሚሄዱትን ወንድሞቼንና እህቶቼን ማመስገን እፈልጋለሁ።”

17. ከአረጋውያን ጋር በየትኞቹ የአገልግሎት ዘርፎች መካፈል ትችላላችሁ?

17 በአገልግሎት አብራችኋቸው ተካፈሉ። አንዳንድ አረጋውያን ከቤት ወደ ቤት ሄደው ለማገልገል አካላዊ ጥንካሬ ላይኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ አንዲትን አረጋዊት እህት በጋሪ ምሥክርነት አብራችሁ እንድትካፈል ልትጋብዟት ትችሉ ይሆን? ምናልባትም በጋሪው አጠገብ እንድትቀመጥ ወንበር ልታመጡላት ትችሉ ይሆናል። አሊያም ደግሞ አንድን አረጋዊ ወንድም ጥናት መጋበዝ ትችሉ ይሆን? ጥናቱን በቤቱ ውስጥ መምራትም ትችሉ ይሆናል። ሽማግሌዎች የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች በአረጋውያን ቤት እንዲካሄዱ ማመቻቸት ይችላሉ፤ ይህም እነዚህ ወንድሞች በአገልግሎት መካፈል ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። አረጋውያንን ለማክበር የምናደርገው ማንኛውም ጥረት አያስቆጭም።—ምሳሌ 3:27፤ ሮም 12:10

18. በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

18 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ይሖዋ አረጋውያንን እንደሚወዳቸውና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ተመልክተናል። ደግሞም በጉባኤ ውስጥ ያለን ሁላችንም እንዲህ ይሰማናል! እርጅና ከባድ ነው፤ ሆኖም በይሖዋ እርዳታ ደስታችሁን ጠብቃችሁ መኖር ትችላላችሁ። (መዝ. 37:25) ወደፊት ደግሞ እስከዛሬ ከኖራችሁት ሁሉ የላቀ ሕይወት እንደሚጠብቃችሁ ማወቃችሁ ምንኛ የሚያበረታታ ነው! ሆኖም አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ሌላ ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። በዕድሜ የገፋ የቤተሰባቸውን አባል፣ ልጃቸውን ወይም የታመመ ጓደኛቸውን መንከባከብ ይጠበቅባቸዋል። ታዲያ ደስታቸውን ጠብቀው መኖር የሚችሉት እንዴት ነው? በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ለዚህ ጥያቄ መልስ እናገኛለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች ደስታቸውን እንዲያጡ የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል?

  • አረጋውያን ደስታቸውን ጠብቀው መኖር የሚችሉት እንዴት ነው?

  • በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያንን መደገፍ የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ

a አረጋውያን—ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላላችሁ የተባለውን ቪዲዮ jw.org ወይም JW ላይብረሪ ላይ ተመልከት።

b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ደስታ ከአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ነው። (ገላ. 5:22) እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና በመመሥረት ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ