ነቅታችሁ ጠብቁ!
ክርስቲያን መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ሰዎች ክርስቲያን እንደሆኑ በኩራት ይናገራሉ፤ ያም ሆኖ ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ሲያደርጉ ይታያሉ። አንዳንዶቹ ራስ ወዳዶች፣ ውሸታሞች ወይም ጨካኞች ናቸው። ለትዳር ጓደኛቸው ታማኝ ያልሆኑም አሉ። አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች ሲያዩ ‘በእርግጥ ክርስቲያን መሆን ማለት ምን ማለት ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ።
በእርግጥ ክርስቲያን መሆን ማለት ምን ማለት ነው?
‘ክርስቲያን ነኝ’ ብሎ መናገር ቀላል ነው። እውነተኛ ክርስትና ግን ከዚያ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ክርስቲያን ማለት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ወይም ተከታይ ማለት ነው። ኢየሱስ ራሱ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 8:31) እርግጥ ነው፣ የኢየሱስን ትምህርቶች ፍጹም በሆነ መንገድ መታዘዝ የሚችል ማንም የለም። ሆኖም አንድ ክርስቲያን በዕለት ተዕለት ሕይወቱ የኢየሱስን ትእዛዛት ለመፈጸም የተቻለውን ያህል ጥረት ያደርጋል። እንዲህ የሚያደርግባቸውን አንዳንድ አቅጣጫዎች እስቲ እንመልከት።
ክርስቲያኖች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳያሉ
ኢየሱስ ምን ብሏል? “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐንስ 13:34, 35
ኢየሱስ ምን አድርጓል? ኢየሱስ የሰዎችን የኑሮ ደረጃ ወይም የኋላ ታሪክ ሳይመለከት ለሁሉም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር አሳይቷል። የታመሙትን ፈውሷል፤ የተራቡትን መግቧል፤ አልፎ ተርፎም ሕይወቱን ጭምር ለሌሎች ሰጥቷል።—ማቴዎስ 14:14-21፤ 20:28
ክርስቲያኖች ምን ያደርጋሉ? ክርስቲያኖች ለጋሶች፣ የማያዳሉና ይቅር ባዮች በመሆን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳያሉ። የተቸገሩትን ይረዳሉ፤ እንዲሁም ለሌሎች ሲሉ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ናቸው።—1 ዮሐንስ 3:16
ክርስቲያኖች ሐቀኛ ናቸው
ኢየሱስ ምን ብሏል? ‘እኔ እውነት ነኝ።’—ዮሐንስ 14:6
ኢየሱስ ምን አድርጓል? ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ምንጊዜም ሐቀኛ ነበር። የራሱን ጥቅም ለማስፈጸም ሲል ሰዎችን አጭበርብሮ ወይም አታልሎ አያውቅም። የሚታወቀው ሐቀኛ በመሆኑ ነበር፤ ተቃውሞ እንደሚያስከትልበት እያወቀም በዚህ አቋሙ ቀጥሏል።—ማቴዎስ 22:16፤ 26:63-67
ክርስቲያኖች ምን ያደርጋሉ? ክርስቲያኖች አይዋሹም። ግብር ይከፍላሉ፤ አይሰርቁም፤ እንዲሁም በሥራ ቦታቸው የሚጠበቅባቸውን ያህል በትጋት ይሠራሉ። (ሮም 13:5-7፤ ኤፌሶን 4:28) ሌሎችን አያጭበረብሩም፤ ፈተና ላይ አኮርጁም፤ አሊያም የሥራ ማመልከቻዎችን ወይም ሌሎች ተመሳሳይ ሰነዶችን ሲሞሉ የተዛባ መረጃ አይሰጡም።—ዕብራውያን 13:18
ክርስቲያኖች ደጎች ናቸው
ኢየሱስ ምን ብሏል? “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”—ማቴዎስ 11:28-30
ኢየሱስ ምን አድርጓል? ኢየሱስ ደግና ሰዎች በቀላሉ የሚቀርቡት ሰው ነበር። ልጆች እንኳ ሳይቀሩ ይቀርቡት ነበር። በተጨማሪም የተጨነቁትን አጽናንቷል፤ እንዲሁም የሁሉንም ዓይነት ሰዎች ክብር ይጠብቅ ነበር።—ማርቆስ 10:13-15፤ ሉቃስ 9:11
ክርስቲያኖች ምን ያደርጋሉ? ክርስቲያኖች ሌሎችን የሚያነጋግሩት በደግነት ነው፤ በንቀት ወይም ጨዋነት በጎደለው መንገድ ሰዎችን አያነጋግሩም። (ኤፌሶን 4:29, 31, 32) ለሌሎች ትኩረት በመስጠት እነሱን መርዳት የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ይፈልጋሉ።—ገላትያ 6:10
ክርስቲያኖች ለትዳር ጓደኛቸው ታማኝ ናቸው
ኢየሱስ ምን ብሏል? “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”—ማርቆስ 10:9
ኢየሱስ ምን አድርጓል? ኢየሱስ አግብቶ ባያውቅም ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ መሆን እንዳለባቸው ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:9) ትዳርን አደጋ ላይ ስለሚጥሉ ድርጊቶችም አስጠንቅቋል።—ማቴዎስ 5:28
ክርስቲያኖች ምን ያደርጋሉ? ክርስቲያኖች ለትዳራቸው አክብሮት እንደሌላቸው የሚጠቁም ምግባር ከማሳየት ይቆጠባሉ። (ዕብራውያን 13:4) ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ፍቅርና አክብሮት ያሳያሉ።—ኤፌሶን 5:28, 33