የይሖዋ ምሥክሮች ከሃይማኖታቸው የወጣን ሰው የሚይዙት እንዴት ነው?
ሁሉንም ሰው በፍቅር፣ በደግነትና በአክብሮት ለመያዝ ጥረት እናደርጋለን። አንድ የይሖዋ ምሥክርa የአምልኮ እንቅስቃሴዎችን ችላ ማለት ቢጀምር ወይም ቢያቆም ቅድሚያውን ወስደን እናነጋግረዋለን፣ እንደምንወደው እናረጋግጥለታለን እንዲሁም ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለው ፍላጎት እንዲቀጣጠል ልንረዳው እንሞክራለን።—ሉቃስ 15:4-7
አንድ ግለሰብ ባደረገው ነገር የተነሳ ከጉባኤው እንዲወገድ የሚወሰንበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 5:13) ይሁንና የእምነት አጋራችንን በጣም ስለምንወደው እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ልናግዘው ጥረት እናደርጋለን። ግለሰቡ ከጉባኤው ቢወገድም እንኳ ለእሱ ፍቅርና አክብሮት ማሳየታችንን እንቀጥላለን፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያበረታታንም ይህንኑ እንድናደርግ ነው።—ማርቆስ 12:31፤ 1 ጴጥሮስ 2:17
አንድ ግለሰብ ከጉባኤ እንዲወገድ የሚያደርገው ምንድን ነው?
ከባድ ኃጢአት የሠራ አንድ ክርስቲያን አካሄዱን ለማስተካከል ፈቃደኛ ካልሆነ ከጉባኤው ሊወገድ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13) አንድን ሰው ሊያስወግዱት የሚችሉት ኃጢአቶች የትኞቹ እንደሆኑ የሚወስነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ለምሳሌ ያህል እንደ ምንዝር፣ ስካር፣ ነፍስ ማጥፋት፣ በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት መፈጸምና ሌብነት ያሉ ተግባሮችን ይዘረዝራል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ገላትያ 5:19-21፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:9, 10
ይሁንና አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ስለሠራ ብቻ ወዲያውኑ ከጉባኤው ይወገዳል ማለት አይደለም። በመጀመሪያ የጉባኤ ሽማግሌዎችb ግለሰቡ አካሄዱን እንዲያስተካክል ሊረዱት ይሞክራሉ። (ሮም 2:4) በገርነትና በደግነት በማነጋገር ልቡን ለመንካት ጥረት ያደርጋሉ። (ገላትያ 6:1) እንዲህ ማድረጋቸው የስህተቱን ክብደት እንዲረዳና ንስሐ እንዲገባ ሊያነሳሳው ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24-26) ግለሰቡን ለመርዳት ተደጋጋሚ ጥረት ተደርጎም የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንቦች መጣሱን ከቀጠለና ንስሐ ካልገባ ግን ከጉባኤው መወገድ ይኖርበታል። በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎች፣ ግለሰቡ ከዚህ በኋላ የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆነ ለጉባኤው ማስታወቂያ ይናገራሉ።
ሽማግሌዎች ኃጢአት የሠራውን ሰው በገርነትና በደግነት በማነጋገር ልቡን ለመንካት ጥረት ያደርጋሉ
ከኃጢአት ጎዳናው ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆነን ሰው ለማስወገድ የሚደረገው ውሳኔ ምን ጥቅም አለው? በአንድ በኩል አምላክ የሥነ ምግባር ንጽሕናን አስመልክቶ ያወጣቸው መሥፈርቶች ጉባኤው ውስጥ እንዲከበሩ ያደርጋል፤ እንዲሁም ግለሰቡ ከሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ጉባኤውን ይጠብቀዋል። (1 ቆሮንቶስ 5:6፤ 15:33፤ 1 ጴጥሮስ 1:16) በሌላ በኩል ደግሞ ኃጢአት የፈጸመው ሰው የተሳሳተ አካሄዱን እንዲተውና ለውጥ እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል።—ዕብራውያን 12:11
የይሖዋ ምሥክሮች ከጉባኤው የተወገዱ ሰዎችን የሚይዟቸው እንዴት ነው?
ክርስቲያኖች ከጉባኤው ከተወገደ ሰው ጋር “[መግጠማቸውን እንዲተዉ] አልፎ ተርፎም እንዲህ ካለው ሰው ጋር ምግብ እንኳ [እንዳይበሉ]” መጽሐፍ ቅዱስ ያዝዛል። (1 ቆሮንቶስ 5:11) ስለዚህ ከጉባኤው ከተወገደ ሰው ጋር ማኅበራዊ ግንኙነት እናቆማለን። ይህ ሲባል ግን ጨርሶ እንዘጋዋለን ማለት አይደለም። በአክብሮት እንይዘዋለን። ከፈለገ ሃይማኖታዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ይችላል፤ እዚያ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ሰላምታ ሊሰጡት ይችላሉ።c በተጨማሪም ግለሰቡ ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እገዛ እንዲያደርጉለት መጠየቅ ይችላል።
ከጉባኤ የተወገዱ ሰዎች ከፈለጉ በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ይችላሉ
ከጉባኤ የተወገደው ሰው የይሖዋ ምሥክር የሆነች የትዳር ጓደኛና ትናንሽ ልጆች ካሉት ግንኙነታቸው በምን መልኩ ይቀጥላል? ከቤተሰቡ ጋር የነበረው መንፈሳዊ ልማድ ይቆማል፤ የቤተሰብ ዝምድናቸው ግን ይቀጥላል። የሚኖሩት አንድ ላይ እንደመሆኑ መጠን ከትዳር ጓደኛውም ሆነ ከልጆቹ ጋር የነበረው ቤተሰባዊ ዝምድናና ፍቅር አይቋረጥም።
ከጉባኤ የተወገደ ሰው ሽማግሌዎች መጥተው እንዲጠይቁት ጥያቄ ማቅረብ ይችላል፤ እነሱም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በፍቅር ምክር የሚሰጡት ከመሆኑም ሌላ ንስሐ እንዲገባና ወደ አምላክ እንዲመለስ በደግነት ያበረታቱታል። (ዘካርያስ 1:3) የተሳሳተ አካሄዱን ከተወና የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንቦች አክብሮ ለመኖር ከልቡ እንደሚፈልግ ካሳየ እንደገና ጉባኤውን መቀላቀል ይችላል። በዚህ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ‘በደግነት ይቅር ይሉታል እንዲሁም ያጽናኑታል’፤ ጥንት በቆሮንቶስ ኃጢአት ሠርቶ የነበረ አንድ ሰው አካሄዱን ባስተካከለ ጊዜ በዚያ ያሉት ክርስቲያኖች ያደረጉት ይህንኑ ነው።—2 ቆሮንቶስ 2:6-8
ከጉባኤው ተወግደው የነበሩ ሰዎች ምን ይሰማቸዋል?
ከጉባኤው ተወግደው የነበሩና በኋላ ላይ ወደ አምላክ ለመመለስ የወሰኑ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የሰጡትን ሐሳብ ተመልከት፦
“ወደ ጉባኤው ለመመለስ ስወስን ሽማግሌዎች ተወግጄ በቆየሁባቸው አሥርተ ዓመታት ያደረግሁትን ነገር ሁሉ እንድነግራቸው ይፈልጋሉ ብዬ አስቤ ነበር። እነሱ ግን ‘እኛ የምንፈልገው ከዚህ በኋላ ማድረግ በምትችዪው ነገር ላይ እንድታተኩሪ ነው’ ብቻ ነው ያሉኝ። ይህን ስሰማ ቅልል አለኝ።”—ማሪያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“ጉባኤው የእኔን መመለስ በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። እንደምፈለግ ተሰማኝ። መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ይቅር እንደተባልኩ እንዲሰማኝና ወደፊት እንድቀጥል ረድተውኛል። ሽማግሌዎች እኔ እንዳገግም ለማገዝ ሁሌም ከጎኔ ነበሩ። አጽናንተውኛል እንዲሁም ይሖዋ አሁንም እንደሚፈልገኝና እንደሚወደኝ እንዲሰማኝ ረድተውኛል።”—ማልኮም፣ ሴራ ሊዮን
“ይሖዋ ለሕዝቡ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ ድርጅቱ ንጽሕናው እንዲጠበቅ በሚያደርገው ነገር ደስተኛ ነኝ። ለሌሎች ጭካኔ የሚመስለው ነገር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የፍቅር እርምጃም ነው። የሰማዩ አባታችን አፍቃሪና ይቅር ባይ አምላክ በመሆኑ አመስጋኝ ነኝ።”—ሳንዲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
a በዚህ ርዕስ ላይ በተባዕታይ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም ሐሳቡ ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራል።
b ሽማግሌዎች ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያን ወንዶች ናቸው፤ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር እንዲሁም የይሖዋን ሕዝቦች በመርዳትና በማበረታታት እንደ እረኛ ሆነው የመንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው። ለሚያከናውኑት ሥራ አይከፈላቸውም።—1 ጴጥሮስ 5:1-3
c ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ባይሆንም ከጉባኤ የወጣ አንድ ሰው የጉባኤውን ስም ለማጥፋት ጥረት ሊያደርግ ወይም መጥፎ ሥነ ምግባርን ለማበረታታት ሊሞክር ይችላል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ እንዲህ ያለውን ሰው “ሰላም አትበሉት” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ እናከብራለን።—2 ዮሐንስ 9-11